1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማክሰኞ፤ ሰኔ 4 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ማክሰኞ፣ ሰኔ 4 2016

*«በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ማስመሰልና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር» የተባለ ረቂቅ አዋጅ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ ። *የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዋና ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በዛሬው ዕለት መሰጠት ተጀመረ ። *260 ግድም ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ የየመን የባሕር ጠረፍ አቅራቢያ የአደን ባሕረ ሰላጤ ውስጥ ሰጥማ ቢያንስ 49 ሰዎች መሞታቸው ተገለ ። ጀልባዋ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ስደተኞችን አሳፍራ ከሶማሊያ የባሕር ጠረፍ 320 ኪሎ ሜትሮች ቀዝፋ እንደነበር አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል ።

https://p.dw.com/p/4gvYs

አርዕስተ ዜና

*«በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ማስመሰልና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር» የተባለ ረቂቅ አዋጅ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ ። ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ በዓላትን እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ አዋጅም ዛሬ ፀድቋል ።  

*የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዋና ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በዛሬው ዕለት መሰጠት ተጀመረ ። 

*260 ግድም  ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ የየመን የባሕር ጠረፍ አቅራቢያ የአደን ባሕረ ሰላጤ ውስጥ ሰጥማ ቢያንስ 49 ሰዎች መሞታቸው ተገለ ። ጀልባዋ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ስደተኞችን አሳፍራ ከሶማሊያ የባሕር ጠረፍ 320 ኪሎ ሜትሮች ቀዝፋ እንደነበር አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል ።  

*በአውሮፕላን በረራ ወቅት ትናንት የገቡበት ያልታወቁት የማላዊ ምክትል ፕሬዚደንት መሞታቸው ዛሬ ይፋ ሆነ ።  ከአውሮፕላን አደጋው የተረፈ የለም ።

ዜናው በዝርዝር

አአ፥ ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ የመረጃ ልውውጦች ላይ ክትትል እና ጠለፋ ማድረግ የሚያስችል ረቂቅ አዋጅ ለቋሚ ኮሚቴ ተመራ

በወንጀል የተገኘ ንብረትን ሕጋዊ ማስመሰልና ሽብርተኝነትን በገንዘብ የመርዳት ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር» የተባለ ረቂቅ አዋጅ ዛሬ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀረበ ። ረቂቅ አዋጁ፦ የመረጃ ልውውጦች ላይ «አስቸኳይ ሁኔታ ባጋጠመ ጊዜ» ብሎም በአዋጁ «መርማሪው አካል» ተብሎ የተጠቀሰው አካል «የዐቃቤ ሕግ የበላይ ኃላፊ ሲፈቅድ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ» ክትትል እና ጠለፋ ማድረግን እንደሚፈቅድ ተገልጧል ። ረቂቅ አዋጁ፦ «በባንክ ሒሳቦች እና በሌሎች ተመሳሳይ ሒሳቦች ላይ ክትትል ለማድረግ፣ የኮምፒውተር መረቦችን እና ሰርቨሮችን ለመለየት፣ መገናኛዎችን በክትትል ሥር ለማዋል ወይም ለመጥለፍ ፣ የደብዳቤ ልውውጦችን መጥለፍ እና ለመያዝ» እንዲችል መርማሪ ተብሎ ለተገለፀው አካል ሥልጣን የሚሰጥ ነው ።  ምክር ቤቱ፦ ረቂቅ አዋጁን መርምሮ ለዝርዝር ዕይታ ወደ ሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ መምራቱንም ዐሳውቋል ። በዛሬው መደበኛ ጉባኤ፦ የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅን እና የነዳጅ ውጤቶችን የግብይት ስርዓት ለመደንገግ የቀረበ ረቂቅ አዋጅን ጨምሮ ሦስት ረቂቅ አዋጆች ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መምራታቸው ይፋ ሆኗል ።  

አ.አ፥የሕዝብ በዓላትን እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ዛሬ ፀደቀ

በተያያዘ ዜና፦ ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ በዓላትን እና የበዓላትን አከባበር ለመወሰን የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ዛሬ ፀደቀ ።  የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ጉባኤው፦ የሕዝብ በዓላትን ተከብረው የሚውሉ እና ታስበው የሚውሉ እንዲሁም ሃይማኖታዊ በዓላት በሚል መድቧቸዋል ።  ግንቦት 20፦ በፀደቀው አዋጅ ከሚከበርም ሆነ ከሚታሰብ በዓላት ዝርዝር ውጭ ሆኗል ። የአዋጁን አስፈላጊነት በተመለከተ የጤና ፣ ማኅበራዊ ልማት ፣ ባህል እና ስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ወርቅሰሙ ማሞ ተናግረዋል ።

አዋጁ ተከብረው የሚውሉ ብሔራዊ በዓላት መደበኛ ሥራ ዝግ የሚሆንባቸው ቀናት መሆናቸውን ገልጧል ። እነዚህም የዘመን መለወጫ- እንቁጣጣሽ፣ የአድዋ ድል፣ የሠራተኞች እንዲሁም የአርበኞች የድል ቀን ናቸው ተብሏል ። ሥራ ሳይዘጋ በተለያዩ ሥነ ሥርዓቶች ታስበው የሚውሉ ብሔራዊ በዓላት ከተባሉት ውስጥ ደግሞ የካቲት 12 ቀን የሚከበረው የሰማዕታት ቀን እንዲሁም ሕዳር 29 ቀን የሚከበረው የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ይገኙበታል ። ሃይማኖትን በተመለከተው የአዋጁ ድንጋጌ ውስጥ አምስት የክርስትና እንዲሁም ሦስት የእስልምና እምነት ክብረ በዓላት ተካትተዋል ። መስቀል፣ ገና ፣ ጥምቀት፣ ስቅለት እና ትንሳኤ ወይም ፋሲካ በአዋጁ የተካተቱ የክርስትና እምነት በዓላት መሆናቸው ተጠቅሷል ። የኢድ-አልአድሃ ወይም አረፋ፣ የመውሊድ እና የኢድ-አልፈጥር በዓላት ከእሥልምና ሃይማኖት የተካተቱ በዓላት ናቸው ።  በዜና መጽሄት ተጨማሪ ይኖረናል ።  

አ.አ፥ ኢትዮጵያ የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና መሰጠት ጀመረ

የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ዋና ከተማ አዲስ አበባን ጨምሮ በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በዛሬው ዕለት መሰጠት ተጀመረ ።  የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ዛሬ ይፋ እንዳደረገው፦ በዋና ከተማዪቱ በ182 የመፈተኛ ጣቢያዎች 86,672 የስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች የሚኒስትሪ ፈተናን በመፈተን ላይ ናቸው ። የፈተናውን ሂደት ለመከታተል 700 ተቆጣጣሪዎች(ሱፐር ቫይዘሮች) መሰማራታቸውም ተገልጧል ።  ለስምንተኛ ክፍል ተማሪዎች የአማርኛና የእንግሊዝኛ ቋንቋዎች ፈተና ዛሬ ከቀትር በፊት እንደነበር ቢሮው ዐስታውቋል ። በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የዶቼ ቬለ ዘጋቢዎች እንደገለጹት በያሉበት ከተማዎችና አካባቢዎችም ፈተናው ዛሬ ተጀምሯል ።  በአማራ ክልል ከ350 ሺህ በላይ ፈተናውን የሚወስዱ ተማሪዎች ቢኖሩም በፀጥታ ችግር ምክንያት ግን ሁሉም ለፈተና እንደማይቀመጡ ቀደም ሲል ተጠቅሷል ። በሲዳማ ክልል፤  በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፤ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤  በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ ፈተና እየተሰጠ መሆኑን ዘጋቢዎቻችን ጠቅሰዋል ። በአንጻሩ በትግራይ ክልል የስምንተኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና የሚሰጠው ከሰኔ 11፣ እስከ ሰኔ 13  ባሉት ቀናት መሆኑን የመቀለው ዘጋቢያችን ገልጾልናል ። የፈተናው ጊዜ በቀናት የዘገየውም ከጦርነቱና ከተለያዩ ምክንያቶች ጋር በተያያዘ ትምህርት አቋርጠው የነበሩና ሳይፈተኑ የቆዩ ተማሪዎች በመኖራቸው እንደሆነም ለመረዳት ተችሏል ።

ሠንዓ፥ 260 ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ የመን ጠረፍ አካባቢ ሰጠመች

ከ260 ግድም  ስደተኞችን ያሳፈረች ጀልባ የየመን የባሕር ጠረፍ አቅራቢያ የአደን ባሕረ ሰላጤ ውስጥ ሰጥማ ቢያንስ 49 ሰዎች መሞታቸውን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፍልሰተኞች ተቋም (OM)ዛሬ ይፋ አደረገ ። 71 ስደተኞች በሕይወት መገኘታቸው ተዘግቧል ።  140ዎቹ ግን ያሉበት እንደማይታወቅ ዓለም አቀፍ ድርጅቱ በኤክስ የቀድሞው ትዊተር ማኅበራዊ መገናኛ አውታሩ ላይ ገልጧል ።  ጀልባዋ የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ ስደተኞችን አሳፍራ ከሶማሊያ የባሕር ጠረፍ 320 ኪሎ ሜትሮች ቀዝፋ እንደነበር አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል ።  ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአፍሪቃ ቀንድ ሃገራት በርካቶች ወደ ሣዑዲ ዓረቢያ እና ሌሎች የመካከለኛው ምሥራቅ ሃገራት ለመሻገር ሲሞክሩ በተደጋጋሚ የመስጠም አደጋ እንደሚከሰትባቸው የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዘግቧል ።   ብዙዎች መካከለኛው ምሥራቅ ቢደርሱ እንኳን እዚያም ሌላ መከራ ይጠብቃቸዋል ሲል የዜና ምንጬ አክሏል ።  ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች ተመልካች (Human Rights Watch) የሣዑዲ ዓረቢያ የድንበር ጠባቂዎች ኢትዮጵያውያን ላይ ባለፈው ነሐሴ ወር ግድያ ፈጽመዋል በሚል ያቀረበውንም ክስ አያይዟል ። ድንበር ጠባቂዎቹ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር ከ2022 እስከ 2023 ባሉት ጊዜያት «ቢያንስ በመቶዎች» የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን የመን ድንበር ላይ ስለመግደላቸውም ዘግቧል ። ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ ከአደጋ እና ከሞት ተርፈው የመን የደረሱ ስደተኞች ቁጥር ከ27,000 በሦስት እጥፍ ከፍ ብሎ ወደ 90,000 መድረሱን ዓለም አቀፉ የፍልሰተኞች ተቋም ዐስታውቋል ።

ባላንቲሬ ፥የማላዊ ምክትል ፕሬዚደንት በአውሮፕላን አደጋ መሞታቸው ይፋ ሆነ

በአውሮፕላን በረራ ወቅት የገቡበት ያልታወቁት የማላዊ ምክትል ፕሬዚደንት መሞታቸው ይፋ ሆነ ።  ትናንት ተሰወረች የተባለችው አውሮፕላን ስብርባሪ ዛሬ ቺካንጋዋ ጫካ ውስጥ ተገኝቷል ። የ51 ዓመቱ ምክትል ፕሬዚደንቱ ሳውሎስ ቺሊማን ጨምሮ Dornier 228 በተሰኘችው አውሮፕላን ተሳፍረው የነበሩት ዘጠኙም ተጓዦች በአውሮፕላን መከስከስ አደጋው አጠቃላይ መሞታቸው ተዘግቧል ። አውሮፕላኗ ከበረራ ዕይታ ውጪ መሆኗ የተዘገበው ትናንት ነበር ። በፍለጋው ዩናይትድ ስቴትስ እና የማላዊ ጎረቤት ሃገራት ተካፋለዋል ።

ቤርሊን፥የዩክሬን ፕሬዚደንት በጀርመን ምክር ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተገኝተው ምሥጋና አቀረቡ

የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ጀርመን ለሀገራቸው የፓትሪዮት ሚሳይሎች ድጋፍ በማድረጓ በጀርመን ምክር ቤት ለመጀመሪያ ጊዜ በአካል ተገኝተው ምሥጋና አቀረቡ ። ፕሬዚደንቱ ትናንት ቤርሊን ከተማ ውስጥ ምሥጋናውን በአካል ተገኝተው ያቀረቡት፦ ዩክሬንን መልሶ መገንባት በሚል የ60 ሃገራት ከ2,000 በላይ ተወካዮች በታደሙበት ጉባኤ ነው ። ለዩክሬን ማኅበረሰብ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማሰባሰብ በሚል ጉባኤው የተቋቋመው እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2022 ነው ። ዩክሬን ከሰሞኑ ምሥራቃዊ  የድንበር ግዛቶች  በሆኑት ክሃርኪቭ እና ዶኒዬትስክ በኩል በሩስያ የደረሰባትን ጥቃት ለመከላከል ጥረት እያደረገች መሆኑ ተዘግቧል ። ሩስያ በዶኒዬትስክ በኩል ተጨማሪ መንደር በቁጥጥሯ ስር ማዋሏን ትናንት ዐሳውቃ ነበር ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ኂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።