1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማክሰኞ ሰኔ 25 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ማክሰኞ፣ ሰኔ 25 2016

https://p.dw.com/p/4hmyg

አርዕስተ ዜና

*ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አሸማጋይነት በመካከላቸው ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አንካራ ውስጥ ንግግር ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዐስታወቀ ። የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ቱርክ አንካራ ውስጥ ትናንት ማሸማገል መጀመሯን በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ይፋ አድርጋለች ።

*ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ቢኒያም ግርማይ ኢጣሊያ እና ፈረንሳይ ውስጥ በሚካሄደው የዘንድሮ ቱር ደ ፍሯንስ ሦስተና ዙር የብስክሌት እሽቅድምድም ትናንት አሸነፈ ። የ24 ዓመቱ ብስክሌት ጋላቢ ቢኒያም ከአንድ ክፍለ ዘመን ወዲህ በመሰል ትልቅ ውድድር ላይ በማሸነፍ ከአፍሪቃ ሦስተኛው ሰው ሆኖ ተመዝግቧል ።

*ሰሜናዊ ሕንድ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በተሰባሰቡበት የሐይማኖታዊ ዝግጅት ወቅት  በተከሰተ መረጋገጥ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 60 መድረሱ ተዘገበ ። ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው ተብሏል ። በርካቶች መቁሰላቸውም ተገልጧል ።

ዜናው በዝርዝር

*ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በቱርክ አሸማጋይነት በመካከላቸው ያሉ አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት አንካራ ውስጥ ንግግር ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዐስታወቀ ። ኢትዮጵያ ከሶማሌላንድ ጋር በተፈራረመችው የወደብ ስምምነት ሰበብ የተቃቃሩትን የሁለቱን ሃገራት ንግግር ያመቻቹት የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚንሥትር ሐካን ፊዳን መሆናቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል ።  የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምበሳደር ነቢዩ ተድላ በበኩላቸው በሁለቱ ሃገራት መካከል ንግግር መደረጉን  ዛሬ ለዶይቸ ቬለ አረጋግጠዋል ። 

«ትናንትና በቱርክ መንግሥት ጋባዥነት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀሥላሴ እና የሶማሌው አቻቸው አህመድ ሞዓሊም ፊቂ አንካራ ውስጥ ተገናኝተው ምክክር አድርገው ነበር እንግዲህ ይሄ ምክክር በሁለቱ መንግሥታት መካከል ያሉ አለመግባባቶችን መፍትኄ ለመስጠት ያለመ ነበር »

የኢትዮጵያ እና የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮችን ቱርክ አንካራ ውስጥ ትናንት ማሸማገል መጀመሯን በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቷ በኩል ይፋ አድርጋለች ። የሁለቱ ሀገራት ባለሥልጣናት «አለመግባባቶችን በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት ቁርጠኝነታቸውን የገለጹ» እንደሆኑ የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጧል ።  ቀጣይ ንግግር ነሐሴ መጨረሻ ላይ እንደሚኖር አምበሳደር ነቢዩ ተድላ ለአዲስ አበባባ ወኪላችን ሰለሞን ሙጬ ነው ተናግረዋል ።

«እንግዲህ ይሄ ውይይት ያው የመጀመሪያ ነው ትናንት የተደረገው በቀጣይ ነሐሴ መጨረሻ ላይ ከተቻለ 27 ለመቀጠል በመስማማት የውይይቱ ማብቂያ ሆኗል »

ሁለተኛው ዙር ውይይት ሰኞ ነሐሴ 27 የቱርክ ዋና ከተማ አንካራ ውስጥ እንደሚደረግ የተለያዩ የዜና ምንጮችም ጠቅሰዋል ። ኢትዮጵያ፤ ሶማሊያ የሉዓላዊ ግዛቷ አንድ አካል አድርጋ ከምትቆጥራት ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ጋር የወደብ አገልግሎት መጠቀም የሚያስችላትን የመግባቢያ ስምምነት ከተፈራረመችበት ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ እና ሞቅዲሾ መካከል የተካረረ ውዝግብ እና አለመግባባት መከሰቱ ይታወቃል ።

*ኤርትራዊው ብስክሌተኛ ቢኒያም ግርማይ ኢጣሊያ እና ፈረንሳይ ውስጥ በሚካሄደው የዘንድሮ ቱር ደ ፍሯንስ ሦስተና ዙር የብስክሌት እሽቅድምድም ትናንት አሸነፈ ። የ24 ዓመቱ ብስክሌት ጋላቢ ቢኒያም ከ121 ዓመታት ወዲህ በመሰል ትልቅ ውድድር ላይ በማሸነፍ ከአፍሪቃ ሦስተኛው ሰው ሆኖ ተመዝግቧል ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ1903 ደቡብ አፍሪቃውያኑ ብስክሌተኞች ዳሪል ኢምፔይ እና ሮብ ሐንተር ነበሩ በመሰል ውድድሮች ላይ ማሸነፍ የቻሉት ። ቢንያም ግርማይ በቱር ደ ፍሯንስ ሦስተኛ ዙር ሽቅድምድም ላይ በማሸነፍ ታሪክ በመሥራቱ «ታላቅ እና የማይረሳ ቀን ነው» ሲሉ የኤርትራ ማስታወቂያ ሚንስትር የማነ ገብረመስቀል ደስታቸውን መግለጣቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP) ዘግቧል ።  

*ድሬደዋ ውስጥ ዛሬ ንጋት በግምት አንድ ሰዓት ጀምሮ በተለምዶ አሸዋ ተብሎ በሚጠራው የንግድ ስፍራ የተነሳው የእሳት ቃጠሎ ከሰዓታት ብርቱ ጥረት በኋላ በቁጥጥር ስር መዋሉን አስተዳደሩ ዐስታወቀ ። ዛሬ ጠዋት ጀምሮ እስከ ቀትር የዘለቀው የእሳት ቃጠሎ አሸዋ በተባለው የንግድ ስፍራ ልባሽ ጨርቆች መሸጫዎችን ጨምሮ ማሽላ ተራ የሚባሉ የንግድ ቦታዎችን አውድሟል ። ከባድ ቁሳዊ ውድመት ያስከተለውን የዛሬውን የእሳት ቃጠሎ መንስኤም ሆነ በአደጋው የደረሰውን ውድመት አስመልክቶ በፖሊስ በኩል የተባለ ነገር የለም ። የአደጋውን አካባቢ የተመለከቱት የመስተዳድሩ ከንቲባ ከድር ጁሀር እሳቱን በቁጥጥር ስር ለማዋል አስተዋፅኦ አድርገዋል ላሏቸው የአካባቢው ኅብረተሰብ፣ የፀጥታ እና ሌሎች በእሳት ቃጠሎው ቁጥጥር ላይ አስተዋፅኦ ላደረጉ አካላት ምስጋና አቅርበዋል ። የአደጋው መንስኤም ሆነ የደረሰውን ውድመት አስመልክቶ ተጣርቶ መረጃ እንደሚሰጥም ከንቲባው ዛሬ ከሰዓት ዐስታውቀዋል ። የተነሳውን የእሳት ቃጠሎ በቁጥጥር ስር ለማዋል ከድሬደዋ በተጨማሪ ሌሎች የእሳት አደጋ መከላከል ተሽከርካሪዎች እና ባለሞያዎች መሳተፋቸውን የድሬዳዋ ወኪላችን መሳይ ተክሉ ዘግቧል ።

*ምዕራባውያን ለዩክሬን ድጋፍ መስጠታቸውን በጥብቅ የሚቃወሙት የሐንጋሪ ጠቅላይ ሚንስትር ለመጀመሪያ ጊዜ ኪዬቭን ዛሬ ጎበኙ ። ጠቅላይ ሚንስትር ቪክቶር ዖርባን የዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ ዛሬ በመገኘት የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ መክረዋል ። የሩስያ እና ዩክሬን ጦርነት ከጀመረ ወዲህ የሐንጋሪ ጠቅላይ ሚንስትር ዩክሬንን ሲጎበኙ ይህ የመጀመሪያቸው ነው ። ጦርነቱ ለአውሮጳ «እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው» ያሉት ቪክቶር ዖርባንበአስቸኳይ የተኩስ አቁም ይደረግ ብለዋል ። ቪክቶር ዖርባን ከአውሮጳ ኅብረት መሪዎች በተለየ መልኩ ከሩስያ ፕሬዚደንት ቭላድሚር ፑቲን ጋ ጥብቅ ግንኙነት አላቸው ተብሎ በሰፊው ይታመናል ።  ሐንጋሪ በዙር የሚደርሰው የአውሮጳ ኅብረት ሊቀመንበርነትን በተረከበችበት ማግስት  የተደረገው  የቪክቶር ዖርባን ጉዞ ከሩስያ ዩክሬን ጦርነት ወዲህ የመጀመሪያው ነው ። ይህ በእንዲህ እናዳለ የዩክሬን መከላከያ ሚንሥትር ከዩናይትድ ስቴትስ አቻቸው ጋ ለመወያየት ወደ ዋሽንግተን አቅንተዋል ።

*ሰሜናዊ ሕንድ ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ምእመናን በተሰባሰቡበት የሐይማኖታዊ ዝግጅት ወቅት በተከሰተ መረጋገጥ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ቢያንስ 60 መድረሱ ተዘገበ ። ከሟቾቹ መካከል አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕጻናት ናቸው ተብሏል ። በርካቶች መቁሰላቸውም ተገልጧል ። የሟቾች ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል ። ምእመናኑ ብሆሌ ባባ የተሰኘው የሒንዱ ምስል ባለበት ቦታ ከነበረው ስነስርዓት በኋላ እንደነገሩ ከተቀለሰው ድንኳን ለመውጣት ሲጣደፉ አደጋው መከሰቱ ተገልጧል ። የዛሬ አደጋ የተከሰተው ፕራዴሽ ከተባለው ግዛት ዋና ከተማ ሉክኖው 350 ኪሎ ሜትር ደቡብ ምዕራብ አቅጣጫ ላይ በምትገኘው ሐትራስ መንደር   ምዕምነናኑ እጅግ በመጨናነቁ ነው ሲል ፖሊስ ዐስታውቋል ።   በሐይማኖታዊ ስነስርዓቶ ወቅት በመረጋገጥ የሚደርስ ሞት ሕንድ ውስጥ በተደጋጋሚ ይከሰታል ።

*ጀርመን ውስጥ በሚካሄደው 17ኛው የአውሮጳ እግር ኳስ ጨዋታ ወደ ሩብ ፍጻሜ ለመግባት የመጨረሻዎቹ ሁለት ውድድሮች ዛሬ ይደረጋሉ ። በሩብ ፍጻሜው ከሚፋለሙ ስምንት ሃገራት ሁለቱን ለመለየት ዛሬ በሚካሄደው ፉክክር ለዋንጫ ግምት ከተጣቸው ሃገራት አንዷ የሆነችው ኔዘርላንድ ከሮማኒያ ጋ እየተጋጠመች ነው ። ጨዋታው በተጀመረ 20ኛው ደቂቃ ላይ ኮዲ ጋክፖ ባስቆጠረው ግብ ኔዘርላንድ 1 ለ0 እየመራች ነው ። የመጀመሪያው አጋማሽ ተጠናቆ ረፍት ላይ ናቸው ። ከሦስት ሰአታት ግድም በኋላ ደግሞ ኦስትሪያ እና ቱርክ ይጋጠማሉ ። እስካሁን በተደረጉ ጨዋታዎች ስድስቱ የሩብ ፍጻሜ አላፊዎች ተለይተዋል ። በዚህም መሠረት፦ የፊታችን ዐርብ አስተናጋጁ ጀርመን እና ስፔን ወደ ማሽ ፍጻሜ ለማለፍ ሽቱትጋርት ከተማ ውስጥ ይጋጠማሉ ። ከሁለቱ ጨዋታ ሦስት ሰአት ዘግየት ብሎ ደግሞ ፖርቹጋል ከፈረንሳይ ጋ ትፋለማለች ። በነጋታው ቅዳሜ እንግሊዝ እና ስዊትዘርላንድ ይጫወታሉ ። ዛሬ አሸናፊ የሚሆኑ ሁለት ቡድኖችም ቅዳሜ ዕለት ለግማሽ ፍጻሜ ይጋጠማሉ ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።