የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት፤ የህወሓት 50ኛ ዓመት፣የመምሕራን መታገት፣ የጂማ ዞን ጥቃት
ሐሙስ፣ የካቲት 13 2017
ጤና ይስጥልኝ እንደምን አላችሁ።በዛሬዉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት ዝግጅታችን ሳምንቱን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተከታታዮችን ትኩረት ከሳቡ በሶስቱ ርዕሶች ላይ ከተሰጡ አስተያየቶችን ከስድብና ዘለፋ የፀዱትን ቃርመናል።የትግራይ ፖለቲከኞች ዉዝግብ በተካረረበት መሐል በተከበረዉ የህወሓት 50ኛ ዓመት የምሥረታ በዓልን በቃኘዉ ዘገባ ላይ የተሰጡ አስተያየቶች ቀዳሚዎቹ ናቸዉ።አማራ ክልል ጎጃም ዉስጥ መምህራን ሥለ መታገታቸዉ በተሠራጨዉ ዘገባ የተሰጠዉን አስተያየት አስከትለን ኦሮሚያ ክልል ጂማ ዞን አንድ ባለሐብት የመገደላቸዉ መዘዝ በርካታ ሰዎች ማፈናቃሉን ባወሳዉ ዘገባ ላይ በተሰጡ አስተያየቶች እናሳርጋል።ከመጀመሪያዉ እንጀምር።
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የትጥቅ ትግል የጀመረበት 50ኛ ዓመት ባለፈዉ ማክሰኞ መቀሌ ዉስጥ ተከብሯል።በዓሉ የተከበረዉ የህወሓት መሪዎች ለሁለት ተከፍለዉ በሚወዛገቡበት ወቅት ነዉ።የመቀሌዉን ድግሥ ያዘጋጀዉ በዶክተር ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል የሚመራዉ አንጃ ነዉ።የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸዉ ረዳ የሚመሩት አንጃ በዓሉን ለማክበር መዘጋጀቱን ሲያስታዉቅ ነበር።ይሁንና በዓሉ ሊከበር አንድ ቀን ሲቀረዉ ዝግጅቱን ማቋረጡን አስታዉቋል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ አሕመድ ዕለቱን አስመልክተዉ ባስተላለፉት መልዕክት የትግራይ ሕዝብን እንኳን አደረሰሕ ብለዋል።ጠቅላይ ሚንስትሩ «ከየካቲት 11 ዓላማዎች ውጭ ፖለቲካዊ ልዩነቶችን በትጥቅ ትግል የመፍታት ፍላጎት አሁንም አለ» ማለታቸዉም ተጠቅሷል።ጠቅላይ ሚንስትሩ የህወሓት ፖለቲከኞችን ሳይሆን የትግራይ ሕዝብ «እንኳ አደረሰሕ» ማለታቸዉ፣ በተለይ ደግሞ በነፍጥ ለመዋጋት የተመሠረተዉ ቡድን በዓል በሚከበርበት ዕለት «ከየካቲት 11 ዓላማዎች ዉጪ---»ልዩነትን በትጥቅ ትግል የመፍታት ፍላጎት ያላቸዉ---»የማለታቸዉ ተቃርኖ የብዙ ትችት ምክንያት ሆኗል።ጥቂቱን እነሆ።
ኃይለ-እየአሱስ ደሳለኝ እርቅይሁን።በማንጠቅሰዉ ስድብ በጀመረዉ ፅሁፉ--«ትላንት በተንኩት አመድ አረኩት ሲሉት የነበረን ፓርቲ ዛሬ እንክዋን ለምስርታህ አደረሰህ ማለት ምን እሚሉት ቅዥት ነው።» ይላል-በፌስ ቡክ።
ዲቪ ዳዲ---ጠቅላይ ሚንስትሩ «ከየካቲት 11 ዓላማዎች ዉጪ» ማለታቸዉ ይተቻል።እሱም በፌስ ቡክ። «ምነው የዛሬ 50 ዓመት በምርጫ ነበር እንዴ ስልጣን የያዘው?» የተመሠረተዉ።እያለ።
ቴዎድሮስ አሰፋ--በመቀሌዉ ድግስ ላይ የታየዉ ወታደራዊ ትርዒት ትኩረቱን የሳበ መስሏል።«ዘንድሮም ወታደራዊ ትርዒት?» ጠየቀ ቴዎድሮስ።አሰፋ ደምሴ ግን «መንግሥት የማያዉቀዉ የደብረ ፅዮን ሠራዊት ነዉ በሰልፉ ላይ የተሳተፈዉ» ይላል።ኽሳብ ዝሰምር ለአሰፋ ደምሴ መልስ አዘል ጥያቄ ሰንዝሯል።«የት ያለው መንግስት ነው???» በሶስት የጥያቄ ምልክት አሳረገ ኽሳብ።
ግርማይ ብርሐኔ፣ ረጅም አስተያየት አስፍሯል።«ፖለቲካዊ ልዩነቶች በጠረጴዛ ዙርያ እንፍታ ተብሎ የፕርቶርያው ሥምምነት ይተግበር ብሎ አምኖ ነበር-የትግራይ ህዝብ።» አለ ቀጥሎም---ከሥምምነቱ በኋላ የትግራይ ሕዝብ የገጠመዉን ፈተና አትቶ---«ይሕን ሁሉ ተቋቅሞ መፍትሄ ያላገኘው ትግስተኛው ህዝቤ መጨረሻው ምን ይሆን ብየ ሳስብ ቀንም ሌሊትም ስጨነቅ ኣድራሎሁ።» በማለት አሳረገ ግርማይ በርሔ በፌስ ቡክ።
ቴዎድሮስ አበባዉ ግን ምክር ብጤ አለዉ----«ልዩነታችንን ወደ ጎን በመተው ለአንዲት ትግራይ በጋራ ልንቆም ይገባል!!» የሚል በሁለት ቃል አጋኖ ያሳረገ-ምክር።»
አማራ ክልል ጎጃም ዉስጥ መምሕራን መታገታቸዉየሚያወሳዉ ዘገባ ለብዙዎች አሳዛኝ፣አስቆጪ የኢትዮጵያን የሕግና ሥርዓት እንዴትነትም አጠያያቂ ያደረገዉ መስሏል።መስሏል ነዉ ያልነዉ።እና መምሕራኑ ጎንጂ ቆለላ ወረዳ «ኮሬ ገረገራ» የተባለ ትምህርት ቤት ያስተምሩ ነበር።14 ናቸዉ።ባልደረቦቻቸዉ እንዳሉት ታጣቂዎች መምሕራኑን ያገቱት ባለፈዉ የካቲት 5 ቀን 2017 ነዉ።እስከ ትናንት ድረስ ያሉበት አይታወቅም።
ፎጊ ዴይ -የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ ወይም ያላት አስተያየት ሰጪ «አንድ የፖለቲካ ድርጅት መንግስትን ሊጠላ ይችላል። ነገር ግን ሓኪሞችን ፣መምህራንን፣ ገበሬና ተማሪን እየገደለ ነጋዴዎችን እየዘረፈ ለእናንተ እታገላለሁ የሚል የፖለቲካ ድርጅቶች ያሉት ኢ/ያ ውስጥ ብቻ ነው።» እያለ ይቀጥላል።ወይም ትቀጥላለች።»
አፈወርቅ ደግነዉ ራሱም መምሕርን መሆኑን ጠቅሷል።አስተያየቱ ቁጭት ብጤ ነዉ።---«መምህራን የማንም መቀለጃ መሆናችን ያሳዝናል። በተለይ ጎጃም ላይ መምህር በመሆኔ ወላጅ እናት አባቴን ሳላይ ይሄዉ ሁለት አመቴ።» ይላል አፈወርቅ ደግነዉ-በፌስ ቡክ።
ሲቲና ወሎ «እንደዚሕ አይነት ጀብዱ እየተለመደ መጣ። ኢትዮጵያ ሁሉ አይመስልም የሚደረገው ነገር» ትላለች።ፅዮን ኢትዮጵያ የሲቲናን አስተያየት ሳትጋራ አትቀርም።እንዲያዉም አጋጥሞኝ ነበር ትላለችም-እገታዉ «ይህ ጉዳይ ከዜና በላይ ነው። እኔም ደርሶብኝ ነበር። ከ4ወር በፊት በጣም ደግሞ በመምሕራን ላይ ይከብዳል።-----» አለች ፅዮን።
ማጀስቲክ ማጀስቲ የሚል የፌስ ቡክ ስም ያለዉ ወይም ያላት ጣጣዉን ለጊዜ ሒደት ትታዋለች ወይም ትቶታል።«ጊዜ ይፍታዉ።መምህራን ከፖለቲካ አመለካከት ነፃ ናቸው።ይፈቱ» የማስቲክ ማጀስቲ አስተያየት ነዉ።
የንጉሴ ፋንታ አስተያየት ብዙ የተለመደ አይደለም።ከተለመደዉ ወጣ ብሎ ጎጂ ያለዉን የማሕበረሰቡን ባሕልና አስተሳሰብ ይተቻል።ንጉሴ ፈንታ።«ካልጠፋ ግጥምና ዘፈን ገዳይ እወዳለሁ እያለ ለገዳይ የሚዘፍነው ይሄኔ ከበሮውን አዘጋጅቶ እየጠበቀ ነው» ይላል ንጉሴ በፌስ ቡክ።«የታገቱትን ፈጣሪ ያውጣቸው» ብሎ አሳረገ።ሰማነዉ? ግን ተርድተነዉ ይሆን?
ሶስተኛዉም ርዕስ እንዳለመታደል ሆኖ የግድያ፣ የጥቃትና መፈናቃል ዘገባ ነዉ።ነገሩ የሆነዉ ኦሮሚያ ክልል ጂማ ዞን ጌራ ወረዳ ነዉ።ዘኪር አባዓሊ የተባሉ አንድ ታዋቂ ባለሐብት ባለፈዉ ሳምንት ኀሙስ በሰዉ እጅ ተገደሉ።የገዳዩ ማንነት በትክክል አልታወቀም።ይሁንና ግድያዉ ያስቆጣቸዉ ወገኖች በተለይ ወጣቶች የጠረጠሩትን ሠላማዊ ሰዉ ማጥቃታቸዉ ተዘግቧል።የጎሳ መልክና ባሕሪ ባለዉ ጥቃት ቢያንስ አንድ ተጨማሪ ሰዉ ተገድሏል።በሺ የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
አባዬና ጤና--- ብዙ ነገር ያስፈራኛል ትላለች ወይም ይላል።«እኔ አሁንም የህግ መከበር ጉዳይ ሳይ፣ የኦሮሚያ የሚዲያ ሰዎች ያ ስተላለፉትን ሳይ በቃ የአገራችንን ጉዳይ ሳይ ያስፈራኛል። ኦሮሚያ ዉስጥ መንግስ ያደራጀዉ የደቦ ሀይል ያለ ይመስለኛል፣ ሰዉ ያልቃል።አገራችን ዉስጥ በርካታ ሰዎች ሞተዋል፤ እየሞቱምነዉ ።» አስተያየቱ ረጅም ነዉ።እኛ በቃን።
አኪያ ኪያ «ንጹሃን ምን አደረጉ?» ይጠይቃል። የሰውየውን ገዳይ ብቻ ይዞ ለህግ ማቅረብ በቂ ነው! አዋቂነት አስተዋይነት የሚለካው በዚህ ነው እባካችሁ የኦሮሞን ህዝብ እንደ ጅል አትዩት!» እያለ ቀጠለ በፌስ ቡክ።
ዮሴፍ አዌሕስ አጭር መልዕክት አለዉ።»አሰልቺ የማይም ፖለቲካ» የሚል።
መልካም ጊዜ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ