1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

ዓርብ፣ ሚያዝያ 1 2013

ኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ የሚደረገውን ድርድር ለማስቀጠል በኪንሻሳ ያደረጉት ስብሰባ ያለውጤት ከተበተነ በኋላ የማሕበራዊ ድረ ገፆች ተጠቃሚዎች አስተያየታቸውን እየገለጹ ነው። በአፋር እና በሶማሌ ክልል አዋሳኝ አካባቢዎች የሚከሰተው ግጭት አገርሽቶ በርካታ ሰዎች ከተገደሉ በኋላ በፌስቡክ የተለያዩ ስሜቶች ተንጸባርቀዋል

https://p.dw.com/p/3rnNV
Icons von Facebook und Twitter
ምስል Imago Images/Eibner

የማሕበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በአፍሪካ ኅብረት አሸማጋይነት በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ በሳምንቱ መገባደጃ በኪንሻሳ የተደረገው ድርድር ያለ ፍሬ ከተበተነ በኋላ ሱዳን እና ግብጽ በኢትዮጵያ ላይ በተለያየ መንገድ ጫና ለማሳደር ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛሉ። ትናንት ሐሙስ እንኳ ሱዳን በታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ "በማናቸውም መንገድ ጥቅሟን እና የዜጎቿን ደሕንነት በዓለም አቀፍ ሕግጋት መሠረት" እንደምታስጠብቅ የአገሪቱ የመስኖ ሚኒስትር ያሲር አባስ በትዊተር ባሰፈሩት አጭር ጽሁፍ አስታውቀዋል። ምኒስትሩ አገራቸው የአፍሪካ ኅብረት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ የአውሮፓ ኅብረት እና አሜሪካ አደራዳሪ እንዲሆኑ ያቀረበችውን ምክረ-ሐሳብ ኢትዮጵያ ውድቅ በማድረግ ሥምምነት ሳይደረስ ሁለተኛ ዙር ውኃ ለመሙላት ጊዜ እየገዛች ነው ሲሉ ከሰዋል።

“የግብጽን ጠብታ ውኃ አትንኩ” ያሉት ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታኅ አል-ሲሲ በበኩላቸው ረቡዕ ዕለት በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ውዝግብ ረገድ “ሁሉም አማራጮች ክፍት ናቸው” ሲሉ ተደምጠዋል። አገራቸው የኪንሻሳው ድርድር ያለ ውጤት ከመበተኑ በፊት በወቅቱ የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበር በኩል መፍትሔ ለማበጀት የሚደረገው ጥረት የመጨረሻው ዕድል ሊሆን እንደሚችል ገልጻ ነበር። 

በዕለተ እሁድ ድርድሩ ሲጀመር የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበርነትን ከደቡብ አፍሪካው ፕሬዝዳንት የተረከቡት የዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ መሪ ፌሊክስ ሼሴኬዲ ሶስቱ አገራት “አንድ ወይም ብዙ የተስፋ መስኮቶች ለመክፈት እና ዕድሉን ለመጠቀም እንደ አዲስ እንዲጀምሩ” ጥሪ አቅርበው ነበር። 

ይሁንና ከጅማሮው ልዩነቶች መታየታቸውን የኢትዮጵያ የውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ምኒስትር ስለሺ በቀለ (ዶ/ር) በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። የኢትዮጵያ ተደራዳሪዎች “ድርድሩ እንዲቋጭ የሚያስችሉ፤ መተማመን የሚያመጡ ሐሳቦች አፅንዖት” ቢሰጡም ሱዳን እና ግብጽ “የአፍሪካ ኅብረት በነፃነት ጉዳዩን ለመምራት እንዳይችል እና የተሰጠውን ኃላፊነት በሚያኮስስ መልኩ ሌሎች ተዋናዮች ይኸን ጉዳይ አብረው እንዲመሩ” የድርድሩን ቅርጽ ለመለወጥ ሐሳብ ማቅረባቸውን ስለሺ ተናግረዋል። የተፋረሰው ድርድር እና ከግብጽ በኩል የተሰሙ ማስፈራሪያዎች በማሕበራዊ ድረ-ገጽ ተጠቃሚዎች ዘንድ መወያያ ሆነዋል። 

አምሳለ ተክሉ “ግብጽ ሁልጊዜም አማራጭ ሲቀርብላት ነገሮችን ወደ በቅኝ ግዛት ዘመን ወደ ተፈረመ የውኃ ክፍፍል ሥምምነት ለመለወጥ በመሞከር አለመስማማት ትፈጥራለች። ይኸ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ተቀባይነት የለውም” የሚል ተቃውሟቸውን በትዊተር አስፍረዋል። እንዲህ አይነት ተመሳሳይ መልዕክቶች በበርካታ የትዊተር ተጠቃሚዎች ዘንድ ሲዘዋወሩ እየታዩ ነው። 

Äthiopien Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
በድርድሩ ከሥምምነት ባይደረስም ኢትዮጵያ ግድቡን ውኃ መሙላት እንደምትቀጥል አስታውቃለችምስል AFP/Maxar Tech

“70 በመቶ ኢትዮጵያውያን የኤሌክትሪክ ኃይል አያገኙም። ታላቁ የኅዳሴ ግድብን የምንገነባው የሕዝባችንን ሕይወት ለመቀየር ነው” ያሉት ደረጄ የተባሉ ሌላ የትዊተር ተጠቃሚ ደግሞ “እኛ ኢትዮጵያውያን በታቀደው መሠረት መንግሥት ግድቡን በውኃ እንዲሞላ እንደግፋለን። ያን ከማድረግ የሚያቆመን የለም” ሲሉ ጽፈዋል። 

"ግብጽ የአፍሪካ ኅብረትን ገሸሽ በማድረግ በታላቁ የኅዳሴ ግድብ ላይ ከኢትዮጵያ ጋር በሚደረገው ድርድር አሜሪካ እና የአውሮፓ ኅብረትን እንዲሳተፉ ግፊት ማድረጓ አጠራጣሪ እና አፍሪካዊ ስሜትን ክብር የሚያዋርድ ነው" ያሉት ይበቃል መኮንን በትዊተር ባሰፈሩት አጭር ጽሁፍ የአልሲሲ አገር ለአኅጉሩ ያላትን ስሜት አጠይቀዋል። 

ወንድሙ ፉፋ በፌስቡክ በሰጡት አስተያየት “አባይ ግድብ አልቆ ለማየት እንኳን እኔ የ7 ዓመቷ ልጄም ባቅሟ ዋጋ እየከፈለች ነው።  አል ሲሲ ከአባይ አንዲት ጠብታ ውሀ የነካ ምናምን እያለ ይጃጃላል። መብቱ ነው። ግን ግብፃውያን ወንድሞቻችን የሚያለሙት መስኖ እ ና ግብርናውስጥ ደግሞ የ115 ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ላብ አለበት። ይህን ግብፃውያን ወንድሞቻችን ይገነዘቡታል። ማንም አስፈራራ ማንም ጮኸ አባይ ተገምብቶ ያልቃል፤ ኢትዮጵያም በክብር ከፍ ትላለች” ብለዋል።

Äthiopien Addis Abeba | Report | Grand Ethiopian Renaissance Dam
ግብጽ እና ሱዳን ኢትዮጵያ ላይ ጫና ማሳደራቸውን ቀጥለዋልምስል DW/N. Desalegen

ከግብጽ በኩል ከተሰጠው አስተያየት በኋላ በማሕበራዊ ድረ-ገፆች ማስጠንቀቂያ እና ማስፈራሪያ የመለሱ ኢትዮጵያውያንም ይገኛሉ። ይኸን የታዘቡት ታፍ ጂ ከበደ “ይሄ ለጦርነት በፉከራ ማቆብቆብ በልክ ቢሆን ጥሩ ነው። በጦርነት ላይ ወኔ ያለው ሚና ኢምንት ነው። ዋናው ጉዳይ የኃይል አሰላለፍ ሚዛን እና የጦር ስትራተጂና ታክቲክ አጠቃቀም ነው። ጦርነት የእጅ በእጅ ፍልሚያ አይደለም” ሲሉ ጽፈዋል። እኚሁ የፌስቡክ ተጠቃሚ “ለጦርነት ዝግጅት ወሳኝ ነው። በዝግጅቱ በሰለጠነ የሰው ኃይል፣ በዘመን አፈራሽ ጦር መሳሪያ መታጠቅ ብቻውን በቂ አይደለም። በዲፕሎማሲው መስክ በቂ ደጋፊና አጋር ሀገራትን ከጎን ማሰባሰብ ወሳኝ ነው። ከሁሉ ባልተናነሰ ጦርነቱን የሚሸከም አስተማማኝ ኢኮኖሚ መኖሩን ማረጋገጥ ግድ ይላል” ብለዋል። 

በነገራችን ላይ ፌስቡክ በዚሁ ሳምንት በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ቱርክ ላይ ያነጣጠሩ መረጃዎች ያሰራጩ ነበር ያላቸውን 17 የፌስቡክ አካውንቶች፣ ስድስት ገፆች እና ሶስት የኢንስታግራም አካውንቶች መዝጋቱን አስታውቋል። ኩባንያው እንዳለው ቢ ኢንተርአክቲቭ ከተባለ የግብጽ ኩባንያ ጋር ግንኙነት የነበራቸው ሲሆን እውነተኛ ባልሆነ ዘመቻ መሳተፋቸው በምርመራ ተደርሶበታል። 

የአፋር እና ሶማሌ ግጭት እንደገና

በሳምንቱ መገባደጃ እንደገና ያገረሸው የአፋር እና የሶማሌ ግጭት የበርካቶችን ሕይወት እንደቀጠፈ ተሰምቷል። አንዳንድ ዘገባዎች የሟቾችን ቁጥር እስከ 100 አድርሰውታል። ከሁለቱ ክልሎች የማሕበራዊ ድረ ገፅ ተጠቃሚዎች በፌስቡክ እና ትዊተር ስለ ግጭቱ ጽፈዋል። የዛኑ ያክል ተወነጃጅለዋል። ግጭት እና ኹከቱን የሚያባብስ ጥሪ ያቀረቡም አልጠፉም። ሥጋታቸውን አጋርተው መፍትሔ እንዲፈለግለት የሚወተውቱም ጥቂት አይደሉም። 

አሎ ያዮ ረቡዕ ዕለት በፌስቡክ ባሰፈሩት ጽሁፍ “ጦርነቱ ዛሬም በአዳይቱ መውጪያ አካባቢ እንደቀጠለ ነው። በትናንትናው ጥቃት በሀንሩካ ወረዳ የአርብቶ አደሮች ሴቶችና ህፃናት ሳይቀሩ የጥቃቱ ስለባ ሆነዋል። ዛሬ ደግሞ የከባድ መኪኖች አሽከርካሪዎች ሳይቀሩ እየተመቱ ነው። ትናንትና የሱማሌ ክልል አንታገስም ወደ እርምጃ እንገባለን የሚል መግለጫ አውጥቷል።  በአጭሩ መወነጃጀሉና መግለጫ መውጣት ለህዝቦች ሰላም የሚጠቅመው አይደለም። ይባስ ብሎ ወደ ጦርነቱ ግለት የሚያመራ ነው። ችግሮችን ወደለየለት ጦርነት እያመራ ነው። የምስራቁ ችግር በአፋርና በሱማሌ ብቻ ሳያበቃ ለሌላው ይተርፋል። ይሄ ሁሉ የፌዴራል መንግስት ቸለተኝነት ነው። አሁንም ቢሆን በጎረቤት ሀገራት ላይ ቁርጠኛ አቋም በመውሰድ በአፋርና በሱማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስታት መሃል አፋጣኝ ውይይት እንዲፈጠር በማድረግ ችግሮች በሰላም በጠረጴዛ ዙሪያ እንዲፈቱ የማድረግ ሥራ የፌዴራል መንግስት መስራት መቻል አለበት። ይህ ካልሆነና ነገሮች በዚህ ከቀጠሉ  ግን የአሰብ የጋላፊ የዳዋሌ የባቡር የየብስ መንገዶች ተዘግተው የንግዱ መስመሩ በስላም እስጦት ትራንስፖርት መቋረጡ እንደማይቀር የፌዴራል መንግስት ሊረዳ ይገባል። ያኔ ችግሩ የአፋርና የሱማሌ ህዝቦች ጉዳት ብቻ ሳይሆን ለመላው ኢትዮጵያ ይተርፋል። ነገሮች ከቁጥጥር ቁጭ ከመሆኑ በፊት የፌዴራል መንግስት አይቶ እንዳላየ ከመሆን ብነቃ ጥሩ ነው እላለሁ።” ብለው ነበር። 

በፌስቡክ ባሰፈሩት ጽሁፍ “በአፋርና ሶማሌ ክልል መካከል ያለው ግጭት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል” የሚሉት ሙሳብ ኢብኑ “የሶማሌ ክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሙስጠፌ ኡመር ይህን ግጭት የሚያስቆምበት ፖለቲካዊ እውቀትም ሆነ ብስለት ከሌለው የእርሱ አዋቂነት፣ ብስለት የእርሱ መሪነት ለሌላ ለምንም አይሆንም። የአፋር ክልል ፕሬዚዳንት አቶ አወል አርባ ይህንን ብዙ ወገኖችን እየቀጠፈ ያለ ግጭት የሚያስቆምበት ፖለቲካዊም ሆነ ግለሰባዊ እውቀት ከሌለው የእርሱ ደግነት፣ የእርሱ መሪነት ለመቸ ይሆናል?” ሲሉ ይጠይቃሉ።  ሙሳብ “ይህ የሁለቱ ክልል ህዝብ እስከ አሁን የተለያዩ ሴራዎችና ደባወች ሲሰራበት የቆየ መሆኑ ይታወቃል። "አርብቶ አደር" እየተባለ ወደ ሀገራዊ መሪነት እንዳይመጣ እርስ በርሱ ጠላት ተደራርጎ እንዲታኮስ የተደረገው ዛሬ አይደለም። ቢሆንም ሁለቱ መሪዎች እስካሁን ይህን ግጭት በባህላዊውም ይሁን ፖለቲካዊ ጥበብ አስታርቀው አንድ ላይ ሊያቆሙት ይገባ ነበር።” ሲሉ ሞግተዋል።  “የትኛውም ግጭት ከጀርባው የፖለቲከኞችንና የፖለቲካን አጀንዳ አድርጎ ነው የሚነሳው። ግጭቱ የማህበረሰብ ወይም የግለሰቦች ከሆነ አፍታ አይቆይም። በሀገሩ፣ በባህሉ፣ በወጉ መሰረት ህክምና አግኝቶ የተጋደለ ሕዝብ ወዲያው አብሮ ሲቆም በኑረታችን ያየነውና የምናውቀው ሀቅ ነው። ስለዚህ ይህን የፖለቲካ አጀንዳ አዝሎ የሚንቀሳቀስ ፖለቲከኛ ሰራሽ የሆነ ግጭት የክልሉ መሪዎች ከማንኛውም አካል በፊት የማስቆምና መፍትሄ የመፈለግ ግደታ አለባቸው” ብለዋል። 

ሙስጠፋ በርክት የተባሉ ሰው የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን እና የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ በአዳኢቱ፣ ገርቦ ኢሴ እና ኡንዱፎ በተባሉ ቀበሌዎች ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ገለልተኛ በሆነ መንገድ እንዲመረምሩ በፌስቡክ ባሰራጩት መልዕክት ጥሪ አቅርበዋል። የሰላም ሚኒስቴር ትናንት ማምሻውን በፌስቡክ ገጹ ባሰራጨው መረጃ በምኒስትሯ "ወይዘሮ ሙፈሪሃት ካሚል ሰብሳቢነት የሁለቱ ክልሎች ከፍተኛ አመራሮችና የፌደራል መንግስት የጸጥታ አካላት በተገኙበት የተከሰቱ ግጭቶችን በአፋጣኝ ለማስቆምና በቀጣይ ችግሮችን ለመፍታት ተስማምተዋል" ብሏል።

እሸቴ በቀለ

ኂሩት መለሰ