1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የማህሌት ተኽላይ አሳዛኝ መጨረሻ፤ የጅጋ ግድያ እና የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ውግዘት

Eshete Bekele
ዓርብ፣ ሰኔ 14 2016

በአድዋ ከተማ ታግታ የነበረችው የማህሌት ተኽላይ አሳዛኝ ሞት እና በምዕራብ ጎጃም ዞን በምትገኘው ጅጋ ከተማ በመከላከያ ሠራዊት አባላት ተፈጽሟል የተባለ ግድያ በሳምንቱ በማኅበራዊ ድረ-ገጾች መነጋገሪያ ከነበሩ መካከል ናቸው። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት እየተደረገበት የሚገኘው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ኃይለኛ ውግዘት ገጥሞታል።

https://p.dw.com/p/4hKVc
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያዘጋጀው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያዘጋጀው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ኃይለኛ ውግዘት እያስተናገደ ነው። ምስል Eshete Bekele/DW

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት፦ የማህሌት ተኽላይ አሳዛኝ መጨረሻ፤ የጅጋ ግድያ እና የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ውግዘት

በትግራይ ክልል አድዋ ከተማ ለወራት ታግታ የቆየችው የ16 ዓመት ታዳጊ ማህሌት ተኽላይ ሕይወቷ እንዳለፈ ፖሊስ ሲያረጋግጥ ጉዳዩ ሐዘንም ቁጭትም ፈጥሯል። በመጋቢት ወር የታገተችው ማህሌት የ10ኛ ክፍል ተማሪ እንደነበረች የዶይቼ ቬለው ሚሊዮን ኃይለሥላሴ ዘግቧል። ታዳጊዋ ወደ ቋንቋ ትምህርት ቤት በማምራት ላይ ሳለች የታገተች ሲሆን ተጠርጣሪዎች “በራሷ ስልክ ወደ አባቷ ደውለው ገንዘብ ጠይቀው” እንደነበር የትግራይ ማዕከላዊ ዞን ወንጀል ምርመራ ኃላፊ ኮማንደር ፀጋይ አስፈሃ ተናግረዋል።

ማህሌት ከታገተች ከሶስት ወራት በኋላ ግን የተሰማው መርዶዋ ነው። ተጠርጣሪዎች ማህሌትን እንደገደሏት ማመናቸውን፣ የቀበሩበትንም ቦታ መርተው ማሳየታቸውን ፖሊስ ገልጿል። የማህሌት ተኽላይ የቀብር ሥነ ሥርዓት በአድዋ ከተማ ተፈጽሟል።

ሞንታና በፌስቡክ “የማህሌትን ሞት የመጨረሻው ካላደረግነው ችግሩ ወደ እያንዳንዳችን ቤት ይመጣል። በየቀኑ በአስር የሚቆጠሩ ሴቶች እየተገደሉ ሊጣሉ ይችላሉ። ለሽብር እና ለሞት የማይደነግጥ ማህበረሰብ እየፈጠርን ነው። ወንጀለኞች የማያዳግም እና ትምህርታዊ ቅጣት ካልተፈረደባቸው ወደየማንወጣው ማህበራዊ ቀውስ ውስጥ እንገባለን” የሚል አስተያየት ጽፈዋል።

“ፍትኅ ለትግራይ ሴቶች…ፍትኅ…ፍትኅ። ከዚህ በላይ ልብ የሚሰብር አሳዛኝ ነገር የለም” ያሉት ደግሞ መሠረት ሐዱሽ ናቸው። “ይህች ወጣት እስከሞተችበት ጊዜ ድረስ ያሳለፈችውን አስቸጋሪ ጊዜ መገመት ከባድ አይደለም። ልጃቸውን ሲጠብቁ የነበሩ ወላጆች መሞቷ ተነግሯቸዋል። የሐዘን ድንኳን ተተክሏል።” ያሉት መሠረት “ትግራይ ዋስሽ ማነው?” ሲሉ ጠይቀዋል።

መድህን ገብረሥላሴ “ሴቶች የሚታፈኑባት እና የሚገደሉባት፤ ሌቦች እንዳሻቸው የሚንቀሳቀሱባት ትግራይን ማየት ያስደነግጣል። በዓድዋ ታፍና ወደ ሶስት ወራት አካባቢ ጠፍታ የነበረችው ህፃን ማህሌት ተኽላይ በሕይወት አለመኖርዋ ለቤተሰብ መርዶ ደርሷል” ሲሉ በፌስቡክ ጽፈዋል።

“የዜጎቹን ደሕነት የማያስጠብቅ የመንግሥት አካል አለሁ ማለት አይችልም!” ሲሉ የተቹት መሠረት “ትላንት በዘውዱ ላይ፤ ዛሬ በማህሌት ላይ የተፈጸመው ነገ በእያንዳንዳችን ላይ ይደርሳል። የሚያስፈራ ነው። መፅናናት ለሰለባ ቤተሰቦች ከማለት ውጭ ምን እንናለን?” ብለዋል።

በመላ ሀገሪቱ የሚታየው የጸጥታ መጓደል እና የፖለቲካ ቀውስ በሴቶች፤ ሕጻናት እና አረጋውያን ላይ የሚፈጸመውን ግድያ፣ ጾታዊ ጥቃት እና በደል አባብሶታል። ባለፈው ሣምንት በአማራ ክልል ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በታጋቾች የታፈነ ወጣት ሞቶ መገኘቱን አባቱ ለዶይቼ ቬለ ተናግረው ነበር። ወጣቱ ሞቶ የተገኘው 3 ሚሊዮን ብር ለጠየቁ አጋቾች በድርድር 500 ሺሕ ብር ከተከፈለ በኋላ ነው።

በአማራ ክልል ጅጋ ከተማ የተፈጸመው ግድያ

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎጃም ዞን በምትገኘው ጅጋ ከተማ የመከላከያ ሠራዊት አባላት ፈጽመውታል የተባለው ግድያ በሣምንቱ ከተሰሙ አሳዛኝ ዜናዎች አንዱ ነው። በፍኖተ ሰላም እና በደምበጫ መካከል በምትገኘው ጅጋ ግድያው የተፈጸመው ባለፈው እሁድ እንደሆነ ዶይቼ ቬለ ለመረዳት ችሏል። ግድያው የተፈጸመው ከደምበጫ ወደ ጅጋ በመጓዝ ላይ በነበሩ የመከላከያ ሠራዊት ተሽከርካሪዎች ላይ የፋኖ ታጣቂዎች ፈጽመውታል ከተባለ ጥቃት በኋላ ነው።

ኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ የዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲዎች በጋራ ባወጡት መግለጫ በጅጋ ከተማ ጎህ በተባለ ሆቴል ውስጥ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት “ምግብ በመመገብ ላይ የነበሩ አስራ ሁለት ልታጠቁ ንጹሃን ሰዎችን ከምግብ ቤቱ አስወጥተውና አምበርክከው መረሸናቸውን ለመረዳት ችለናል” ብለዋል። ፓርቲዎቹ በፌስቡክ ባሰራጩት የጋራ መግለጫ “በአሰቃቂ ሁኔታ” ተገድለዋል ካሏቸው መካከል የባንክ ቤት ሰራተኞች፣ መምህራን፣ የጉልበት ሰራተኞች እና አንዲት የአዕምሮ ሕመምተኛ ይገኙበታል።

በዕለቱ ከተገደሉት መካከል የአቢሲኒያ ባንክ የጅጋ ቅርንጫፍ ሥራ አስኪያጅ የነበሩት አቶ ዘመኑ አስማረ እና በቅርንጫፉ ጁኒየር ኦፊሰር የነበሩት አቶ ሐብታሙ ዓለማየሁ እንደሚገኙበት ዶይቼ ቬለ ለመገንዘብ ችሏል።

የኢትዮጵያ ወታደሮች
በአማራ ክልል ጅጋ ከተማ ተፈጽሟል የተባለውን ግድያ “አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ” ያሉት ኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ የዐማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲዎች “ጉዳዩ በአስቸኳይ በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ” ጠይቀዋል።ምስል Minasse Wondimu Hailu/AA/picture alliance

ግድያውን “አሰቃቂ የጅምላ ጭፍጨፋ” ያሉት አራቱ ፓርቲዎች “ጉዳዩ በአስቸኳይ በገለልተኛ አካላት ተጣርቶ በአጥፊዎች ላይ እርምጃ እንዲወሰድ” ጠይቀዋል። “የመከላከያ ሠራዊትም ሆነ በተቃራኒ ወገን የቆሙ ታጣቂ ኃይሎች ዓለም አቀፍ የጦር ሕግን እንዲጠብቁ” አሳስበዋል።

የአማራ ማኅበራ በአሜሪካ በበኩሉ በጃቢ ጠህናን ወረዳ በምትገኘው ጅጋ የመንግሥት ኃይሎች “በተለይም የአድማ ብተና ኃይሎች በአካባቢው በሚገኝ ሆቴል ውስጥ ሰላማዊ ሰዎች” ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን በፌስቡክ ባሰራጨው መግለጫ አስታውቋል። “ወጣቶችን ከሆቴሉ እየጎተቱ መግቢያው ላይ ተኩሰው ገድለዋቸዋል” ያለው የአማራ ማኅበር በአሜሪካ “ቢያንስ 11 ሰዎች የተገደሉ ሲሆን ነገርግን አንዳንድ ምንጮች 20 እና ከዚያ በላይ ሰዎች መሞታቸውን ገልፀዋል” ብሏል።

እስካሁን በጅጋ ተፈጸመ ስለተባለው ግድያ የመከላከያ ሠራዊት የሰጠው ማረጋገጫም ሆነ ማስተባበያ የለም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመሩት የፌድራል መንግሥት እና የአማራ ክልል ዝምታን መርጠዋል።

ማምና በረሀ “ንፁሀንን መግደል የባሰ ችግር ውስጥ ይከተናል። መከላከያ ይሄን ማስተዋል አለበት” ሲሉ ጽፈዋል። ተስፋዬ ወልደሚካኤል “እርስ ርስ በራስ መገዳደል እና መወነጃጀሉ ይብቃን። በቃ ማንም ይሁን አይሙት፤ የወንድምህን ደም እጅህ ላይ መቀባት ከባድ ነው!” የሚል ማሳሰቢያ ሰጥተዋል።

በአማራ ክልል በመንግሥት ኃይሎች እና በፋኖ ታጣቂዎች ውጊያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ ፍኖተ ሰላምባሕር ዳር እና መርዓዊን ጨምሮ በበርካታ አካባቢዎች የሰላማዊ ሰዎች ግድያዎች በተደጋጋሚ ተፈጽመዋል።

የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ውግዘት

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ያዘጋጀው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ኃይለኛ ውግዘት እያስተናገደ ነው።  ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ካቢኔ ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራው ረቂቅ “ዐቃቤ ሕግ ምንጩ ያልታወቀ ነው ብሎ የጠረጠረውን ማንኛውንም ንብረት ዝርዝር እና የተገኘበትን አግባብ የሚያሳይ መግለጫ እንዲያቀርብ በፅሁፍ ጥያቄ የቀረበለት ማንኛውም ሰው ጥያቄው በደረሰው በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ለዐቃቤ ህግ ዝርዝር ማስረጃዎችን በማያያዝ በፅሁፍ ማቅረብ ይኖርበታል” የሚል አንቀጽ ይዟል።

ይኸ ረቂቅ “ማስረጃ እንዲያቀርብ የተጠየቀ ማንኛውም ሰው በተሰጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ካላቀረበ ንብረቱ ምንጬ ያልታወቀ ነው የሚል ግምት ተወስዶበት ዐቃቤ ህግ ንብረቱ እንዲወረስ ክሱን ለፍርድ ቤት ያቀርባል” ሲል ይደነግጋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
የኢትዮጵያ መንግሥት ያዘጋጀው እና ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራው የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ኃይለኛ ትችት ገጥሞታል። ምስል Solomon Muche/DW

የኢትዮጵያ መንግሥት ረቂቁን እንዳዘጋጀ ከተሰማ በኋላ ጳውሎው ወንድሙ በፌስቡክ “ደርግ ባቋራጭ ከች” ሲሉ ጽፈዋል። “አደገኛ ህግ ነው” የሚሉት ደግሞ አሮን ናቸው። “የስንቱን ሰው ወርሶ ይችለዋል?” ሲሉ የሚጠይቁት አሮን “በአረብ ሀገር ጨምሮ ያልፍልኛል ብሎ የተንከራተተው፤ እሳት ላይ ተጥደው የሠሩት ቤት እና ንብረት ማስረጃ የለም ብሎ መውረስ የግፍ ግፍ ነው” ሲሉ ተችተዋል።

ስጦታው ደለለኝ “ከመንግሥት ከሁሉም የመዋቅር አመራር ይጀምር” የሚል ሐሳብ አላቸው።  ፈቃደ ሥላሴ ተስፋዬ “መንግሥት እጁን ሲያስገባ ነገሮች ይባባሳሉ እንጂ ለውጥ አይመጣም። ይልቁኑ ለመንግሥት ካድሬ ህዝብን መበዝበዣ መሳርያ ነው እየፈበረካችሁ ያላችሁት” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

እታፈራሁ ካሳሁን “የጉድ ሀገር አዳሜ አፈር ከድሜ ግጣ፣ ዕንቅልፍ አጥታ፣ ሀገር አለኝ ብላ ያፈራችውን ንብረት በደረሰኝ ሰበብ ለመንጠቅ፤ አረ ግፉ ይብቃ አረ ተውት ይህንን ህዝብ” ብለዋል። መሐመድ አብድረሕማን “መንግሥት ይሔን ጉዳይ በደንብ ቢያጤንበት ጥሩ ነው። ካልሆነ ግን በጣም አደገኛ ውሳኔ ነው” ሲሉ አስጠንቅቀዋል። ቢሉ ሉሊት “ዜጎች ያፈሩትን ንብረት የገዛ አገርህ ምቀኛ ሆና አንተን ለማደህየት 10 ዓመት ወደኋላ ስትጓዝ” ሲሉ ጽፈዋል።

ናትናኤል ተረፈ “ያው መጽደቁ አይቀርም። ፖርላማ ገብቶ የማይፀድቅ ነገር የለም” ይላሉ። “ ̍የፖርላማ አባል በተገኙበት ይገደሉ ̍ የሚል አዋጅ ቢቀርብ አጨብጭበው እንደሚያፀድቁ ጥርጥር የለኝም” የሚሉት ናትናኤል “አዋጁ ህግ ሆኖ ከፀደቀ በኋላ ግን ፊልም ላይ የምናያቸውን የመኒ ላውንደሪ ትሪኮች እኛ ሀገር ላይ መለመድ ይጀምራሉ” የሚል ጠጠር ያለ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። ፋሲል ጌቱ “ከውጪ በተላከው ብቻ ሳይሆን ፖለቲከኞች በአጭር ጊዜ ሀብት የፈጠሩበት አካሄድም ይመርመር፤ በቤተሰቦቻቸው ስም ያካበቱት ሀብት ይጣራ” ብለዋል። ተካልኝ ኦርማሌ “ተወርሶ ደመወዝ ልጨመር ነው? ወይ ሌላ ፓርክ እና የጫካ .....ለሚባለው ነገር ግንባታ?” ሲሉ ጠይቀዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ