1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

የመካከለኛውን ዘመን የሰው ልጅ አመጣጥ የሚያሳይ አዲስ ግኝት በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ መጋቢት 18 2016

ኢትዮጵያ ሉሲ ወይም ድንቅነሽን ጨምሮ በርካታ ቅሪተ አካላትና በዓለም ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ የድንጋይ መሣሪያዎች መገኛ በመሆን፤በጥንታዊ የሰው ልጅ አመጣጥ ላይ በሚደረገው ምርምር ጉልህ ስፍራ አላት።በቅርቡ የወጣ አንድ የጥናት ግኝት ደግሞ የሰዉ ዘር መገኛ ብቻ ሳትሆን በመካከለኛው ዘመን የሰው ልጅ አመጣጥ ምርምርም ቀዳሚ መሆኗን የሚያሳይ ነው።

https://p.dw.com/p/4eCO2
ጥንታዊ ሰው የድንጋይ መሳሪያዎችን በመጠቀም በአካባቢው ይገኙ የነበሩ እንስሳትን አድኖ በመመገብ በረሃማ የአየር ንብርትን ተቋቁሞ ይኖር እንደነበረ ጥናቱ ያሳያል
ጥንታዊ ሰው የድንጋይ መሳሪያዎችን በመጠቀም በአካባቢው ይገኙ የነበሩ እንስሳትን አድኖ በመመገብ በረሃማ የአየር ንብርትን ተቋቁሞ ይኖር እንደነበረ ጥናቱ ያሳያልምስል Dr.Mulugeta Fisseha

የመካከለኛውን ዘመን የሰው ልጅ አመጣጥ የሚያሳይ አዲስ ግኝት


የሰው ልጆችን ዝግመተ ለውጥ እና አመጣጥን በተመለከተ  የዘርፉ ሊቃውንት በሶስት ደረጃ ይከፍሉታል። የመጀመሪያው ከ40,000 እስከ 50,000 ዓመት ዕድሜ ያለው የቅርቡ ዘመናዊ ሰው ፣ሁለተኛው ደግሞ ከ50,000 እስከ 280,000 ዓመት ዕድሜ ያለው የመካከለኛ ዘመን ሰው፣ ሶስተኛው ደግሞ ከ280,000 ጀምሮ እስከ ሚሊዮን ዓመታት ያለው ጥንታዊ ሰው ነው።ስለ ጥንታዊ የሰው ዘር አመጣጥ ሲነሳ  ኢትዮጵያ  የሰዉ ዘር መገኛኛነቷን የሚያረጋገጡ በርካታ ቅሬተ አካላትና ጥንታዊ ሰው ይገለገልባቸው እንደነበረ የሚያስረዱ የድንጋይ መሳሪያዎች የተገኙባት እና በዘርፉ ጉልህ ስፍራ ያላት ሀገር ነች።

ሳይንሳዊ ግኝቶችን በዓለም አቀፍ ደረጃ በመዘገብ በሚታወቀው ኔቸር መፅሄት በቅርቡ ያወጣው አንድ ጥናት ደግሞ ኢትዮጵያ በጥንታዊው ዘመን ብቻ ሳይሆን በመካከለኛው ዘመን የሰው ልጅ አመጣጥ ላይም ላቅ ያለድርሻ እንዳላት የሚያሳይ ነው። 
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ እና በአሜሪካው ቴክሳስ አት ኡስቲን ዩንቨርሲቲ/University of Texas at Austin/  በትብብር የተካሄደው ይህ ጥናት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በሽንፋ እና መተማ ረባዳ ቦታዎች ላይ ሰፊ ምርምር አድርጓል።

በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ እና በአሜሪካው ቴክሳስ  ዩንቨርሲቲ በትብብር የተካሄደው ይህ ጥናት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በሽንፋ እና መተማ ረባዳ ቦታዎች ላይ ሰፊ ምርምር አድርጓል
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ እና በአሜሪካው ቴክሳስ ዩንቨርሲቲ በትብብር የተካሄደው ይህ ጥናት በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ በሽንፋ እና መተማ ረባዳ ቦታዎች ላይ ሰፊ ምርምር አድርጓልምስል Dr.Mulugeta Fisseha

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ  መምህር እና የሰው ልጅ አመጣጥ እና አካባቢ /paleoanthropology and paleoenvironment/ተመራማሪ የሆኑት ዶ/ር ሙሉጌታ ፍስሃ  ከአሜሪካዊው ተመራማሪ  ዶ/ር ጆን ካፕልማን ጋር  የጥናት ቡድኑን መርተዋል።ዶክተር ሙሉጌታ እንደሚሉት ጥናቱ  የመካከለኛውን ዘመን ሰው በተመለከተ የነበረውን መላምት የሚቀይር አዲስ ግኝት ይፋ አድርጓል።

እንደ ዶክተር ሙሉጌታ ገለፃ ከኢትዮጵያ በተጨማሪ አፍሪካ እንደ አህጉር በተለይ ምስራቅና ደቡባዊ የአፍሪቃ ክፍል  የሰዉ ዘር አመጣጥን የሚያስረዱ የቅሬተ አካላት  መረጃ /The first modern human fossil evidence/ የተገኘባት አህጉር በመሆኗ  አህጉሪቱ የዘመናዊ ሰዉ መገኛ ተብላ ትጠራለች፡፡ ነገር ግን ዘመናዊ ሰዉ ከአፍሪካ አህጉር ወደ ሌሎች አህጉራት መቼና እንዴት ተሻገረ የሚለውን የሚገልፁ አሳማኝ የጥናት መረጃዎች አልነበሩም ይላሉ።

ዶክተር  ሙሉጌታ ፍስሃ ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ መምህር እና ተመራማሪ.
ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ መምህር እና ተመራማሪ.ምስል privat

«ዘመናዊ ሰው ከ200,000 ዓመት ጀምሮ በምስራቅ እና ደቡብ አፍሪቃ እንደተገኘ ጥናቶች ያሳያሉ።ነገር ግን  ከአፍሪካ ወደ ዓረቡ ዓለምና ወደ አውሮጳ መቼ እና እንዴት ሄዱ የሚለው ላይ ብዙ አወዛጋቢ ጥያቄዎች ነበሩ። ምክንያቱም በአንድ በኩል ሲታይ ከአፍሪቃ ወጥቶ መሻገሪያ ወይም /land bridges/የምንላቸው፤ ወይ ቀይ ባህር ወይ ሜድቴራንያን ባህር ናቸው ወደ ሌላኛው ዓለም መውጫ።በሌላ በኩል ከሄድን ደግሞ ውቅያኖስ ነው።መውጣታቸውን የጄኔትክ ጥናት ያሳያል።ኢሮጵም እስያም ሌሎችም ሀገሮች መውጣታቸውን ያሳያል።ነገር ግን  ከአፍሪቃ ወደ ሜዲተራንያን እና ወደ ቀይ ባህር  የሚያሻግረው ደረቃማ መሬት በመሆኑ፤የጥንታዊ ሰው ደግሞ  አዳኝ እና የሚመገባቸዉ የምግብ ዓይነቶችም ፍራፍሬ፣ ቅጠላቅጠል እና ስራስር በመሆናቸው እነዚህ የሚገኙት ደግሞ በጫካዎችና ዛፎች በበዙበት መልካዓ ምድር ብቻ ስለሆነ  መሻገር አይችሉም።» የሚል ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ነበሩ ብለዋል።
ይህንን ጥያቄ ለመመለስም  ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የጥናት ፍቃድ በማግኘት ከጎርጎሪያኑ 2002 ዓም ጀምሮ ለ22 ዓመታት ጥናቱ  ሲካሄድ  መቆየቱንም ተመራማሪው ገልፀዋል። ነገር ግን የጥናቱ ግኝት ነባሩን መላምት ከመሰረቱ የሚቀይር በመሆኑ የጥናቱ ጊዜ ብቻ ሳይሆን ተቀባይነቱም ብዙ ጊዜ ወስዷል።የሰው ዘር አመጣጥ አዲስ ግኝት

ጥናቱ  የመካከለኛውን ዘመን ሰው በተመለከተ የነበረውን መላምት የሚቀይር አዲስ ግኝት ይፋ አድርጓል
ጥናቱ የመካከለኛውን ዘመን ሰው በተመለከተ የነበረውን መላምት የሚቀይር አዲስ ግኝት ይፋ አድርጓልምስል Dr.Mulugeta Fisseha

ከዚህ በተጨማሪ አዲሱ ጥናት ቅሬተ አካል በምስራቅ አፍሪቃ ሰምጥ ሸለቆ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ረባዳማ የኢትዮጵያ ቦታዎችም እንደሚገኝ አሳይቷል። 
የጥናት ቡድኑ ይህንን ለየት ያለ ሳይንሳዊ  መረጃ ይፋ ያደረገው፤ በርካታ የመካከለኛ ዘመን የድንጋይ መሳሪያዎች እና የእንስሳትን ቅሬተ አካልን እንዲሁም መካነ ቅርሱ የሚገኝበትን ስፍራ ሥነ- ምህዳር  በማጥናት መሆኑንም ዶክተር ሙሉጌታ ገልፀዋል። 
በዚህ መሰረት ጥንታዊ ሰው የድንጋይ መሳሪያዎችን በመጠቀም በአካባቢው ይገኙ የነበሩ እንስሳትን አድኖ በመመገብ በረሃማ የአየር ንብርትን ተቋቁሞ ይኖር እንደነበረ ያሳያል ብለዋል፡፡ለዚህም የተለያዩ ማስረጃዎች መገኘታቸውን አስረድተዋል።

ተመራማሪው እንደሚሉት ጥንታዊ ሰው ይኖርበት የነበረዉ ቦታ ሥነ ምህዳር /Ancient environment or paleo environment/ ሊታወቅ የቻለዉ  በአካባቢው በተገኙ የእንስስሳት ቅሬተ አካላት በተለይም በአጥቢ እንስሳት ጥርስ እና በሰጎን እንቁላል ቅርፊት ላይ በተገኙ የኦክስጅንና የካርቦንዳይኦክሳይድ ንጥረ ነገሮች አማካኝነት ሲሆን፤ በዚህም ጥንታዊ ሰው ይኖርበት የነበረዉ የአየር ንብረት ሞቃታማ እንደነበረ ለማወቅ ተችሏል።
ሌላዉ የዚህ ጥናት ትልቁ ግኝት ደግሞ ከሽንፋና መተማ ከ7000 ኪሜ በላይ ርቆ በሚገኘዉ ከ74000 ዓመታት በፊት በኢንዶኖዥያ ሰማትራ የፈነዳዉየእሳተ ገሞራ አመድ በቦታዉ ባሉት ንብርብር አለቶች መገኘቱ ነዉ፡፡

ጥናቱ  የመካከለኛውን ዘመን ሰው በተመለከተ የነበረውን መላምት የሚቀይር አዲስ ግኝት ይፋ አድርጓል
ጥናቱ የመካከለኛውን ዘመን ሰው በተመለከተ የነበረውን መላምት የሚቀይር አዲስ ግኝት ይፋ አድርጓልምስል Dr.Mulugeta Fisseha

ይህ የሚያሳየዉም በሽንፋና መተማ ረባዳ ቦታዎች በዚያ ዘመን ይኖሩ የነበሩ  ሰዎች ይህ እሳተ ጎመራ የፈጠረዉን የአየር ንብረት ጫና ለመቋቋም  በኩሬዎች የሚያገኙ አሳን  የመሳሰሉ የውሃ ውስጥ እንስሳትን  በምግብነት ይጠቀሙ እንደነበር እና በአካባቢያቸዉ የነበረው ምግብ ሲያልቅም ወንዞችን እየተከተሉ ከቦታ ቦታ ይንቀሳቀሱ እንደነበረ  ዶክተር ሙሉጌታ አመልክተዋል። የተገኘው የእስተ ገሞራ አመድም የእድሜውን ለመገመት አግዟል።
ተመራማሪው እንደገለፁት ጥናቱ በጥቅሉ ሲታይ ጥንታዊ ሰው የመካከለኛዉ የድንጋይ ዘመን መሳርያዎች በመጠቀም እና ከኩሬዎች የሚያገኙዋቸዉን ምግቦች በመመገብ በረሃማዉን የአየር ንብረት የመቋቋም ባህሪይ እንዳዳበረ እንዲሁም በእሳተገሞራ ፍንዳታ ምክንያት የመጣዉን የአየር ንብረት ለውጥ ለመቋቋም ሲል  ከአፍሪቃ ወደ ሌላ አህጉራት ወንዞችን ተሻግሮ  እንደተጓዘ ያሳያል፡፡

የጥናቱ  ውጤት  የመጀመርያዉ የሳይንስ ግኝት በመሆን በኔቸር  መፅሄት በጎርጎሪያኑ መጋቢት 20 ቀን 2024 ታትሞ ለንባብ የበቃ ሲሆን፤በዚህም ጥንታዊ ሰው ከአፍሪካ ወደ ሌላ አህጉራት ለመሻገር በፊት ይታሰብ እንደነበረው ለምለምና በዛፍ የተሸፈነ መሬት ተከትሎ ሳይሆን ደረቅ የአየር ንብረት ተቋቁሞ መሻገሩን አመልክቷል።

ጥናቱ የጥንታዊ ሰው የመካከለኛዉ የድንጋይ ዘመን መሳርያዎችን በማስረጃነት ተጠቅሟል
ጥናቱ የጥንታዊ ሰው የመካከለኛዉ የድንጋይ ዘመን መሳርያዎችን በማስረጃነት ተጠቅሟልምስል Dr.Mulugeta Fisseha

ይህ አዲስ ዕይታም ዶክተር ሙሉጌታ እንደሚሉት የነበረዉን የምርምር አቅጣጫ በማስፋት የአባይ ሸለቆን ተከትሎ ወደ ሜዲተራኒያን ባህር በሚወስዱ ረባዳ ቦታዎች፣ ወደ ሰሜን ምስራቅ ኢትዮጵያ በሚፈሱ ወንዞች እና ረባዳ ቦታዎች ጭምር አዳዲስ ምርምር እንዲካሄድባቸዉ መንገድ ይከፍታል።ለተጨማሪ ጥናቶችም መነሻ ሆኖ ያገለግላል። ድንቅነሽ (ሉሲ) የተገኘችበት 40ኛ ዓመት መታሰቢያ በዓል በሊዮ
ከዚህ በተጨማሪ ሉሲ ወይም ድንቅነሽ በጎርጎሪያኑ በ1974 ዓም ከተገኘች ጊዜ ጀምሮ በርካታ ቅሬተ አካላት እና በዓለም ረጅም ዕድሜ ያስቆጠሩ የድንጋይ መሳሪያዎች መገኛ በመሆን፤ ለሳይንሱ ከፍተኛ  አስተዋፅኦ ማድረጓን የሚናገሩት ተመራማሪው ይህ አዲስ ግኝትም፤ኢትዮጵያም የሰዉ ዘር መገኛ ብቻ ሳትሆን ዘመናዊ ሰዉ ለመጀመርያ ጊዜ ሞቃታማ የአየር ንብረት ተቋቁሞ ከአፍሪካ ወደ ዓረቡ ዓለምና ወደ አዉሮፓ መሻገሩን የሚያሳይ የመጀመርያ የሳይንስ ግኝት የተገኘባትና የቀጣይ ዘመናት መካነ ቅርስ እንድትሆን ያደርጋታል ብለዋል፡።
በዚህ ምርምር የጎንደር እና የባህርዳር ዩንቨርሲቲ እንዲሁም ሌሎች በርካታ ኢትዮጵያውያን ባለሞያዎች በጥናቱ መሳተፋቸውንም ተመራማሪው ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሀ ተናግረዋል። የምርምሩ መርሃ ግብርም ቀጣይነት እንዳለው ዶክተር ሙሉጌታ ፍስሃ ጨምረው ገልፀዋል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ማንተጋፍቶት ስለሺ