1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመንግስት አማካይ የዋጋ ግሽበትን ወደ 12 በመቶ የማውረድ ዕቅድ እና ተግዳሮቱ

ዓርብ፣ ሰኔ 14 2016

የዜጎችን ህይወት ክፉኛ እየፈተነ ያለውን የዋጋ ንረት ምጣኔ በሚቀጥለው ዓመት በእጥፍ ለመቀነስ ማቀዱን የኢትዮጵያ መንግስት አሳውቋል፡፡የመንግስት ዕቅድ ዘንድሮ በአማካይ 25.5 በመቶ ገደማ የሆነውን የዋጋ ንረት ምጣኔ በሚቀጥለው ዓመት ወደ 12 በመቶ ለማውረድ ነው።የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ግን ዕቅዱን ለመተግበር አስቻይ ሁኔታ ስለመኖሩ ይጠራጠራሉ።

https://p.dw.com/p/4hLpm
Äthiopische Währung
ምስል Eshete Bekele/DW

የመንግስት አማካይ የዋጋ ግሽበትን የመቀነስ ዕቅድ እና ተግዳሮቱ

 

የኢትዮጵያ መንግስት በተደጋጋሚ ይፋ በሚያደርገው የኢኮኖሚ እድገት ውጥኖቹ በግብርና፣ በኢንደስትሪ፣ በማዕድን፣ በቱሪዝምና ቴክኖሎጂ ዘርፎች ላይ ለማተኮር መወጠኑን ይገልጻል፡፡ በዚህም በተያዘው ዓመት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከ7-9 በመቶ እድገት ስለማሳየቱ ተመላክቷል፡፡ በቀጣይ ዓመትም ኢኮኖሚው በ8.3 በመቶ እንዲያድግ ማቀዱን የሚግልጸው ኢትዮጵያ መንግስት ኢኮኖሚውን አሁን ላይ በብርቱ የሚፈትነውን የዋጋ ግሽበት አሁን ካለበት የ25.5 በመቶ አማካይ ምጣኔ በእጥፍ ቀንሶ ወደ 12 በመቶ ለማውረድ ስለማቀዱም እየተገለጸ ነው፡፡

ስለመንግስት እቅድ የባለሙያ ምልከታ

ባለሙያዎች ግን ይህን ገቢራዊ ማድረግ ቀላል አይመስል ይላሉ፡፡ መቀመጫቸውን በለንደን ያደረጉ የምጣኔ ሃብት እና ፋይናንስ ተንታኝ አቶ አብዱልመናን መሃመድ ምክንያታቸውንም ከባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ መንግስት እቅድና ትግበራው ጋር አያይዘው ነው የቃኙት፡፡ “የኢትዮጵያ መንግስት ባለፈው ዓመትም በተመሳሳይ ሁኔታ የዋጋ ግሽበቱን ከ30 በመቶ ገደማ ወደ ከ20 በታች አወርዳለሁ የሚል እቅዱን ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ ግን ያንን ማድረግ አልቻለም፡፡ አምስት በመቶ ህሉን ብቻ ነው መቀነነስ የቻለው፡፡ በዚያው በአምናው እቅዱ የሚቀጥለውን የ2017 በጀት ዓመት የግሽበት ምጣኔን ደግሞ ከአንድ ዲጂት በታች አወርዳለሁ ብሎ ነበር፡፡ አሁንም በእጥፍ ለመቀነስ ማቀዱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ሚጣጣም አይመስልም፡፡ ሰላምና ጸጥታው ባልተረጋገጠበትና መንግስት በስፋት ገንዘብ በሚያትምበት አገር ይህ በዚህ ደረጃ የሚሳካ አይመስል” ሲሉም ባለሙያው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡፡ ስለኢትዮጵያ ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት የጥናት ውጤት

የተረጋጋ ኢኮኖሚን ለመገንባት የተረጋጋ የፀጥታ ዞታ ሚና

የኢትዮጵያ መንግስት በሚቀጥለው ዓመት የኦኮኖሚ እድገት እቅዱና በዋጋ ግሽበት ቅነሳ ውጥኑ በርግጥ ሰላምን የማረጋጋት ሚና የጎና ቦታ ሊኖረው እንደሚገባ ያነሳል፡፡ በሁሉም የአገሪቱ አከባቢዎች ይህንኑን ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ደጋግሞ ጠቁሟል፡፡ የውጥኑ አተገባበር እቅዱ ላይ ግን የተቀመጡ ዝርዝር ጉዳዮች ሲነገሩም በይፋ ሲገለጹ አይታዩም፡፡

የምጣኔ ሃብት እና ፋይናንስ ተንታኙ አቶ አብዱልመናን በፊናቸው በተለይም ፈተናው ከባድ የሆነውን የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሰላም ሁኔታውን ማረጋጋት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው ይላሉ፡፡ “የዋጋ ግሽበቱን ለመቆጣጠር የሰላም ሁኔታውን ማረጋጋት ላይ መተኮር አለበት፡፡ ምንም ጥርጥር የሌለው ነገር ሰው ተረጋግቶ ካላመረተ፤ በተለይም በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች የሚስተዋለው ግጭት እልባት ካላገኘ መንግስት አሳካዋለሁ ያለው የዋጋ ግሽበት ማረጋጋት እቅዱ አይሳካም” ብለዋል፡፡"የዋጋ ግሽበቱ ከቁጥጥር ውጭ ሊሆን ይላል"

የምጣኔ ሃብት እና ፋይናንስ ተንታኙ አቶ አብዱልመናን እንዳሉት፤ በተለይም ፈተናው ከባድ የሆነውን የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሰላም ሁኔታውን ማረጋጋት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነው
የምጣኔ ሃብት እና ፋይናንስ ተንታኙ አቶ አብዱልመናን እንዳሉት፤ በተለይም ፈተናው ከባድ የሆነውን የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የሰላም ሁኔታውን ማረጋጋት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ ነውምስል MICHELE SPATARI/AFP

መሰራት ያለበት መሰረታዊ ጉዳይ

ባለሙያው መንግስት ግቡን እውን ለማድረግ እንደሚቸገር ያብራሩትም የእቅዱን መለጠጥ እንደ ዋነኛ ምክንያት በማንሳት ነው፡፡ ሆኖም ኢኮኖሚውን የተረጋጋ አለት ላይ ለማስቀመጥ ሊሰሩ ይገባል ያሏቸው አበይት ጉዳዮች፡ “አንደኛው ምንም ትያቄ የሌለው የሰላም ሁኔታውን ማረጋጋት ነው፡፡ ከዚያን ኢኮኖሚውን አንቆ የያዘውን የፖሊሲ ጉዳዮችን በቀጣይነት ተመልክቶ ትክክለኛ የፖሊሲ አማራጭን ማስቀመጥ ኢኮኖሚውን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ሊወስዱት ይችላሉ” የሚለውን እምነታቸውንም አጋርተዋል፡፡የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የዋጋ ግሽበትን ለመቆጣጠር የወሰደው እርምጃ በእርግጥ ለውጥ እያመጣ ነው?

በኢትዮጵያ በተለይም ከግጭቶች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ከጊዜ ወደ ጊዜ የተባባሰው የዋጋ ንረትና የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በተለይም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ ያሉትን ዜጎች በብርቱ ስለመፈተቱ በተደጋጋሚ ተዘግቧል፡፡

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ስዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ፀሀይ ጫኔ