1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

የመንግሥት 47 ዩኒቨርሲቲዎች ሚና ከኢትዮጵያ ፍላጎት ምን ያህል የተጣጣመ ነው?

Eshete Bekele
እሑድ፣ ግንቦት 25 2016

አየር መንገድ፣ መከላከያ ሠራዊት እና ፌድራል ፖሊስ ያቋቋሟቸውን ሳይጨምር ኢትዮጵያ 47 የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች አሏት። የዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ሲጨምር ሀገሪቱ ምን አተረፈች? የትምህርት ተቋማቱ ከገዢው ፓርቲ ምን ያክል ነጻ ናቸው? በዚህ ውይይት አቶ ኮራ ጡሹኔ፣ ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ እና ዶክተር ሰይፈ ታደለ ተሳትፈዋል።

https://p.dw.com/p/4gW9F
በዎላይታ ዩኒቨርሲቲ የተሰለፉ ተማሪዎች
የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ወደ 47 ከፍ ሲል ባለሙያዎች በተማሪዎች ቁጥር እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ረገድ ዕድገት ቢኖርም ውጤቱ ለመንግሥትም ሆነ ለዜጎች አመርቂ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ። ምስል privat

ውይይት፦ የመንግሥት 47 ዩኒቨርሲቲዎች ሚና ከኢትዮጵያ ፍላጎት ምን ያህል የተጣጣመ ነው?

የኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር የሚያስተዳድራቸው ዩኒቨርሲቲዎች ቁጥር ባለፉት ሦስት አስር ዓመታት ገደማ ከሁለት ወደ አርባ ሰባት አድጓል። ይኸ ቁጥር የኢትዮጵያ አየር መንገድ፣ መከላከያ ሠራዊት እና ፌድራል ፖሊስ ያቋቋሟቸውን ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት አይጨምርም። በኢትዮጵያ ወደ 360 የሚደርሱ የግል ኮሌጆች እና ዩኒቨርሲቲዎችም ይገኛሉ። 

የመንግሥት የዩኒቨርሲቲዎቹ ቁጥር ሲጨምር ከፍተኛ ትምህርት የማግኘት ዕድል ቢያድግም በጥራት ጉዳይ ኃይለኛ ትችት ይቀርብባቸዋል። ተቋማቱ ስኬታማ፣ በራሳቸው የሚተማመኑ እና አቅም ያላቸው ዜጎች ለማፍራት ሥርዓተ ትምህርታቸው ከሀገር በቀል የእውቀት ሥርዓት ጋር የተሳሰረ ሊሆን ይገባል የሚል ሙግት ይቀርባል።

ባለሙያዎች በተማሪዎች ቁጥር እና በመሠረተ ልማት ግንባታ ረገድ ዕድገት ቢኖርም ውጤቱ ለመንግሥትም ሆነ ለዜጎች አመርቂ አይደለም ሲሉ ይተቻሉ። 

ባለፉት ዓመታት የሕክምና ባለሙያዎችን ጨምሮ በርካታ የዩኒቨርሲቲ ምሩቃን ሥራ ለማግኘት ተቸግረዋል። ይኸ ተቋማቱ የሚሰጡት ትምህርት እና ሥልጠና ከኢትዮጵያ ፍላጎት ጋር ምን ያክል የተጣጣመ ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል። ኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎችን በከፍተኛ ወጪ ስታስፋፋ ምን አተረፈች? የትምህርት ተቋማቱ ከገዢው ፓርቲ ምን ያክል ነጻ ናቸው? የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ሚና እና የሀገሪቱ ፍላጎት ምን ያክል የተጣጣመ ነው? 

በዚህ ውይይት በኢትዮጵያ ትምህርት ሚኒስቴር የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ኮራ ጡሹኔ፣ በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና የኅትመት ዳይሬክተር ዶክተር ኤፍሬም ተክሌ እና በደቡብ አፍሪካ ጁሐንስበርግ ዩኒቨርሲቲ ከፍተኛ ተመራማሪ የሆኑት ዶክተር ሰይፈ ታደለ ኪዳኔ ተሳትፈዋል። 

ውይይቱን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ 

እሸቴ በቀለ