1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአውሮጳ

የመስከረም 8 ቀን 2017 ዓ.ም የዓለም ዜና

Shewaye Legesseረቡዕ፣ መስከረም 8 2017

በደቡብ ምዕራብ ዳርፉር ውስጥ የሱዳን ጦር ባካሄደው የአየር ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ። ዩናይትድ ስቴትስ የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች በአስቸኳይ ለውይይትም እንዲቀመጡ ጠይቃለች። የዩናይትድ ስቴትስ ሰው አልባ አውሮፕላን የመን አቅራቢያ መከስከሱን ፔንታገን አረጋገጠ። የየመን ሁቲ ሚሊሺያዎች ባለፉት ቀናት በርካታ አውሮፕላኖችን መትተው መጣላቸውን አስታውቀው ነበር። ሊባኖስ ውስጥ በድምፅና መልእክት መቀበያ መሣሪያ ፍንዳታ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ማሻቀቡ እየተነገረ ነው። ማዕከላዊ አውሮጳን ከሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ያጥለቀለቀው አስከፊ የጎርፍ አደጋ ከሮማንያ እስከ ፖላንድ ከባድ ውድመት አስከትሏል።

https://p.dw.com/p/4koFE

ኻርቱም፤ ሱዳን ውስጥ በአውሮፕላን ጥቃት ከ40 በላይ መገደላቸው

በደቡብ ምዕራብ ዳርፉር ውስጥ የሱዳን ጦር ባካሄደው የአየር ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ። በተጠቀሰው የሱዳን ግዛት ኒያላ ከተማ ጥቃቱ የደረሰው ሰኞ ዕለት እንደነበር የአካባቢው የመረጃ ምንጮች ገልጸዋል። የአየር ጥቃቱ ኢላማ ያደረገው በከተማዋ የሚገኝ እስር ቤት እንደሆነና በርካቶች መገደላቸውም ተመልክቷል። ኒያላ ከተማን የተቆጣጠረው ፈጥኖ ደራሹ ታይል በኤክስ ገጹ እንዳመለከተው፤ የሱዳን ጦር በአየር ጥቃቱ የማኅበራዊ ደህነት ሚኒስቴር ሕንጻና በአካባቢው የሚገኙ መኖሪያ ቤቶችን አውድሟል። የሱዳን መንግሥት ጦር ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ በአብዛኛው በፈጥኖ ደራሹ ኃይሎች ቁጥጥር ስር በሚገኘው ምዕራባዊ የዳርፉር ግዛት የሚያደርሰውን የአየር ጥቃት አጠናክሯል። የመነግሥት ጦር በጅምላ ሲቪሎች ላይ ጥቃት በማድረስ እየተከሰሰ ነው። ይህ በእንዲህ እንዳለም፤ ዩናይትድ ስቴትስ የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይሎች ወደ ድርድር እንዲመለሱ ጠይቃለች። ፕሬዝደንት ጆሴፍ ባይደን «ለሱዳናውያን ስቃይ ተጠያቂ የሆኑት የሱዳን ጦር እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ሠራዊታቸውን ወደኋላ በመሳብ እንቅፋት የሌለበት የሰብአዊ እርዳታ መንገድ እንዲከፍቱ እና ይህን ጦርነት ለማቆም ለድርድር እንዲቀመጡ ጥሪ አቅርባለሁ» ብለዋል።

 

 

ዱባይ፤ ሊባኖስ ውስጥ በደረሰው ፍንዳታ የሟቾች ቁጥር ጨመረ

ሊባኖስ ውስጥ በድምፅና መልእክት መቀበያ መሣሪያ ፍንዳታ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ማሻቀቡ እየተነገረ ነው። ዛሬ ከቀትር በኋላም በደቡባዊ ቤይሩት በርካታ ፍንዳታ ደርሷል።  ፍንዳታው የደረሰው ይህን የመገናኛ መሣሪያ በተጠቀሙ በኢራን የሚደገፈው ሂዝቦላህ አባላት እና ቤተሰቦች ላይ መሆኑ ተገልጿል። በፍንዳታው እስካሁን 12 ሰዎች መሞታቸው የተገለጸ ሲሆን የተጎዱት ደግሞ 2,800 ይሆናሉ ተብሏል። በተጠቀሰው መሣሪያ አማካኝነት ፍንዳታው በመላ ሊባኖስ እና በከፊል ሶርያ ውስጥ ነው የደረሰው። ሂዝቦላህና የሊባኖስ መንግሥት ለድርጊቱ እስራኤልን ተጠያቂ አድርገዋል። በዋሽንግተኑ የመካከለኛው ምሥራቅ ፖሊሲ ጥናት ተቋም የፀረ ሽብር እና ስለላ ባለሙያ ማቲው ሌቪት ለዶቼ ቬለ እንደተናገሩት ይህ ፍንዳታ የተፈጸመው ከፍተኛ ደረጃ በሚሰጠው የስለላ ተግባር ነው።

 «እንዲህ ያለ አይቼ አላውቅም፤ ከውጭ የተገዙ የኢራንን የኒኩሊየር ማብላያ ስልቶች በፍጥነት እንዲሽከረከሩና እንዲሞቁ ያደረጋቸውን የምዕራባውያንን ጥሶ የገባ ስልት ያስታውሳል። ሆኖም ግን በተለይ እንዲህ ባለ የተከሰከለ ቦታ፤ ለመንቀሳቀስም ለምዕራባውያንም ሆነ ለእስራኤል አስቸጋሪ በሆነ ስፍራ እንደዚህ ያለ ነገር የለም። ሂዝቦላ ውስጥ የገባ ከፍተኛ የስለላ ተግባር ነው።»

አያይዘውም ከድርጊቱ ጀርባ የእስራኤል እጅ ሊኖር ይችል ይሆናል የሚለውን ጠቁመዋል። ወታደራዊ ኃይሏ በተጠንቀቅ እንዲቆም ያዘዘችው እስራኤል ግን ምላሽ አልሰጠችም። የአውሮጳ ኅብረት ሊባኖስ ውስጥ በመገናኛ መሣሪያዎች የደረሰውን ፍንዳታ አውግዟል።

 

ዋሽንግተን፤ የዩናይትድ ስቴትስ ሰው አልባ አውሮፕላን የመን አቅራቢያ መከስከሱ

የዩናይትድ ስቴትስ ሰው አልባ አውሮፕላን የመን አቅራቢያ መከስከሱን ፔንታገን አረጋገጠ። ቀደም ብለው የየመን ሁቲ ሚሊሺያዎች ባለፉት ቀናት በርካታ አውሮፕላኖችን መትተው መጣላቸውን አስታውቀው ነበር። የፑንታገን ቃል አቀባይ ሜጀር ጀነራል፤ ፓት ራይደር ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት ትናንት ኤም ኪው 9 የተሰኘው ሰው አልባ አውሮፕላን የመን አቅራቢያ ወድቋል። ስለሁኔታው ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው የገለጹት ቃል አቀባዩ፤ ጉዳዩ እየተመረመረ መሆኑንም አመልክተዋል። የሁቲ አማጽያን፤ ሰኞ ዕለት ሦስት ኤም ኪው አውሮፕላኖችን መትተን ጥለናል ብለዋል። የፔንታገን ቃል አቀባይ ግን ስንት ሰው አልባ አውሮፕላን የሚለውን አልገለጹም።

 

ዋርሶው፤ ማዕከላዊ አውሮጳን ያጥለቀለቀው ጎርፍ

ማዕከላዊ አውሮጳን ከሁለት አስርት ዓመታት ወዲህ ያጥለቀለቀው አስከፊ የጎርፍ አደጋ ከሮማንያ እስከ ፖላንድ ከባድ ውድመት አስከትሏል። ከተሞችን በጭቃና ፍርስራሾች በመዝጋት፤ ድልድዮችን አውድሟል፤ መኪናዎችን አስጥሟል። ባለሥልጣናትና ባለቤቶችንም በቢሊየን የሚቆጠር ዶላር ለጉዳት ክፍያ እንዲያወጡ አድርጓል። እንዲያም ሆኖ አሁንም ውኃው ሊጨምር እንደሚችል ነው የሚገለጸው።

በዛሬው ዕለትም በፖላንድ፤ በቼክ ሪፐብሊክ እንዲሁም በሀንጋሪ በወንዝ ዳርቻ አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ራሳቸውን ከጎርፍ ለመከላከል እየሞከሩ ነው። ፖላንዳዊው አርቲስት አልበር ዎሮቶኖቭስኪ ያለውን ሁኔታና የሕዝቡን ስሜት እንዲህ ነው የገለጸው።

«ብሩህ ተስፋ ያላት ይህቺ ፀሐይ እኛንም ትረዳናለች። ሰዎች እንዲህ ያለ እምነት እና ተስፋ አላቸው ብዬ አስባለሁ። እናም ማየት ትችላለህ። ሁሉም፤ እዚህ ያለው ሁሉም ይህን ለማድረግ ጥንካሬው አለው። እንደእኔ ለማድረግም ሰዎች እንደውም ከሥራ ሁሉ ፈቃድ ወስደዋል፤ ለምሳሌ እኔም ከረባቴን አውልቄያለሁ። »

«ወንዙ ድንበሩን አልፎ ላይመጣ ይችላል በሚል፤ እንዲሁም የጎርፍ መከለያዎቹ ያግዱት እንደሆነ፤ የተከፋፈለ አስተያየት ነው ያለው። ከ1997 ወይም ከ2010ሩ በተሻለ ተዘጋጅተናል፤ ሆኖም ያንንም አልፎ ጎርፍ ይመጣል የሚል ስጋትም አለ። እናም የሚሆነውን ሁሉንም እየጠበቅን ነው። መከላከል እንፈልጋለን።»

ጣሊያን ውስጥም አንድ የአደጋ ጊዜ ሠራተኛ በጎርፍ ሊወሰድ የነበረ መኪናን ለማዳስ ሲሞክር በውኃው ተወስዶ ሕይወቱን ማጣቱ ተዘግቧል። የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ አባላት በማዕከላዊ አውሮጳ በጎርፍ ለተጎዱ አካባቢዎች አስቸኳይ የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ ጠይቀዋል።  

 

አንካራ፤ ተርክዬ ምዕራቡንም ሳትተው ከምሥራቁ ዓለም ጋር ግንኙነቷን ለማጠናከር መፈለጓ

የቱርክ ፕሬዝደንት ሀገራቸው ከምሥራቁ ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት እንደምታጠናክር አስታወቁ። ፕሬዝደንት ረሲፕ ጠይብ ኤርዶኻን ዛሬ እንደተናገሩት ቱርክ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላትን ትስስር እያስቀጠለች፤ ቻይናን ጨምሮ ከብሪክስ አባል ሃገራት ጋር ያላትን ግንኙነት ታጠናክራለች ብለዋል። የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ኔቶ አባል የሆነችው ቱርክ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቻይና እና ሩሲያ በአባልነት የሚገኙበት የብሪክስ አባል ለመሆን እንደምትፈልግ ይፋ አድርጋለች። የአንካራ ፍላጎት አሜሪካ እና የአውሮጳ ሃገራት፤ በተለምዶ በመልክአ ምድራዊ አቀማመጥ ከምትዛመደው ከምዕራቡ ዓለም ለመገለል መንገድ እያመቻቸች ነው የሚል ስጋት እንዲያድርባቸው ማድረጉን ሮይተርስ በዘገባው አመልክቷል። ኤርዶኻን ዛሬ አንካራ ላይ እንደተናገሩት፤ የሀገራቸው ከምሥራቁ ዓለም ጋር ያላትን ትስስር ማጠንከሯ፤ ከምዕራቡ ዓለም ለመነጠል በመፈለግ አይደለም የሚለውን አጽንኦት ሰጥተዋል።

 

ዋሽንግተን፤ ዩናይትድ ስቴትስ ወታደሮቿን ከኒዠር አወጣች

ዩናይትድ ስቴትስ ኒዠር የነበሩ ወታደሮቿን አጠቃላ አወጣለች። የኒዠር የዜና አውታር እንዳመለከተው የአሜሪካ ወታደሮቿምን አጠናቃ ማስወጣቷን የሁለቱም ሃገራት የመከላከያ ሚኒስቴር ትናንት ባወጡት የጋራ መግለጫ ይፋ አድርገዋል። የወታደሮቹ መውጣት ሂደት የተጀመረው ባለፈው ግንቦት ወር ነበር። ከወታደሮቹ በተጨማሪ በዋና ከተማ ኒያሚና አጋዴዝ ከነበረው የጦር አውሮፕላን ጣቢያም የአሜሪካ ወታደራዊ ቁሳቁሶች ተነስተዋል። የኒዠር ወታደራዊ አገዛዝ ከአሜሪካ ጋር የነበረው ወታደራዊ ስምምነት ባለፈው መጋቢት ወር ነው ያቋረጠው። የኒዠር ወታደራዊ ኹንታ ውሉን ፍትሃዊ አይደለም በሚል ነው እንዲቋረጥ የጠየቀው። ዋሽንግተንም በግንቦት ወር ነበር በስምምነቱ መቋረጥ መስማማቷን ገልጻ ወታደሮቿን ማስወጣት የጀመረችው። እንደማሊ እና ቡርኪና ፋሶ ሁሉ ኒዠርም ከጎርጎሪዮሳዊው 2023 ሐምሌ ወር ጀምሮ ከሩሲያ ጋር ወታደራዊና ኤኮኖሚያዊ ግንኙነቷን አጥብቃለች።

 

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።