1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 12፤2017 የዓለም ዜና

Yohannes Gebreegziabherእሑድ፣ መስከረም 12 2017

https://p.dw.com/p/4kx5H

የአንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማሪያም  የ30ኛ ዓመት ህልፍተ ህይወት መታሰብያ

የአንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማሪያም  የ30ኛ ዓመት ህልፍተ ህይወት መታሰብያ ዛሬ ተካሄደ።  አዲስ አበባ በ ወምዘክር ቤተ መጻህፍት በተካሄደው የጋዜጠኛው ዝክረ ህይወት መታሰቢያ  ላይ የስራ ባልደረቦቹና ቤተሰቦቹ  ተገኝተዋል። አንጋፋው ጋዜጠኛ ጌታቸው ኃይለማርያም፣ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥንና ሬድዮ  ከሪፖርተትነት እስከ ፕሮግራም ክፍል ሀላፊ በመሆን አአልግሎዋል።

ጋዜጠኛ  ጌታቸው ሀይለማሪያም ዛሬም ድረስ ስሙ በሙያው ዘርፍ የሚታወስ ሲሆን  በሙያው ከ 22 ዓመታት በላይ ያገለገለ እውቅ ጋዜጠኛ እንደነበር በዝግጅቱ ተገልጿል፡፡

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሀይለማሪያምን የዘጋቢ ፊልም ባለሞያ ከመሆኑም ባሻገር አለም እንደምን ሰነበተች በሚል የሚያዘጋጀው ፕሮግራም የሚታዋቅበት ስራዎቹ ናቸው።

ጋዜጠኛ ጌታቸው ሙያውን አክባሪ እና በዘርፍ አዳዲስ ነገርን ለመጀመር  ደፉር እንደነበር በስነስርዓቱ ከታደሙት የሥራ አጋሮቹ ለ DW ገልፀዋል። ጋዜጠኛ ጌታቸው ሃይለማሪያም በ 1938 ተወልዶ 1987 በ49 አመቱ ይህወቱ ማለፉን ይታወሳል ስትል ስነስርአቱን የተከታተለችው ሃና ደምሴ ዘግባለች።

የቻድ ተቃዊ ፓርቲ መሪው በሃገሪቱ የደህንነት ሃይሎች መጠለፋቸውን

የቻድ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪው በሃገሪቱ የደህንነት ሃይሎች መጠለፋቸውን አስታወቀ። ፓርቲው እንዳለው መሪው ታፍነው የተወሰዱት ከሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር ስብሰባ ተካፍለው ሲወጡ ነው።

ድንበር የለሽ የሕብረተሰብአዊነት ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ሮበርት ጋም አሁን በስልጣን ላይ ያለው ወታደራዊ ሁንታ የጠለፈውን ትግል በማስተባበር ይታወቁ እንደነበር ዜናው አክሏል።

የፓርቲው ምክትል ሊቀመንበር ፋቲም አዶም ዩሱፍ ለጋዜጠኞች እንዳሉት ስብሰባው በሚካሄድበት ቦታ ላይ ታርጋ የሌላቸው ወደውስጥ ያማያሳይ ሽፍን መስተዋት ያላቸው 3 መኪኖችና በርካታ ሞተርሳይክሎች ሲንቀሳቀሱ ታይቷል። ይህ ደግሞ በደህንነት ሃይሎች መጠለፋቸውን ግልጽ ነው ማለታቸውንም አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ዘግቧል።

ሒዝቦላህ 150በላይ ሮኬቶች፣ ሚሳይሎችና ድሮኖች ወደ እስራኤል ሰሜናዊ ግዛት ማስወንጨፉን

በሊባኖስ የሚንቀሳቀሰው ሒዝቦላህ ከ150 በላይ ሮኬቶች፣ ሚሳይሎችና ድሮኖች ወደ እስራኤል ሰሜናዊ ግዛት ማስወንጨፉን የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት አስታወቀ። በጥቃቱ ቢያንስ 3 ሰዎች ላይ ጉዳት ደርሷል። የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ የሂዝቦላህ ጥቃትን አንታገስም ሲሉ ተደምጧል።

ሂዝቦላህ ዛሬ ያስወነጨፋቸው ሚሳይሎች ኪርያት ቢያሊክ ወደተባለች የሃይፋ ግዛት ሲሆን የስቪል መኖሪያ ቤቶች ላይ ያነጣጠሩ ነበሩ ተብሏል። ሚሳይሎቹ በአብዛኛው የከሸፉ ቢሆንም አንድ በከተማዋ አካባቢ የወደቀ ሚሳይል ግን 3 እስራኤላውያን ስቪሎች ማቁሰሉንና በቁጥር ያልተገለጹ መኖሪያ ቤቶችንንና መኪኖችን ማቃጠሉን ታውቋል።

ሂዝቦላህ በአካባቢው በሚያደርሰው ተደጋጋሚ ጥቃት ምክንያት በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ተፈናቅለዋል ነው የተባለው።

ሒዝቦላህ በበኩሉ ይህን የበቀል እርምጃ የወሰድኩት እስራኤል በአለፈው አርብ በቤይሩት ላካሄደችውና የቡድኑ መሪዎች የሚገኙባቸው ቢያንስ 45 ሰዎች የሞቱበትን ጥቃት ምላሽ ነው ብሏል።

በሌላ ዜና እስራኤል ባለፉት 24 ሰዓታት የሒዝቦላህ ይዞታዎች ናቸው ባለቻቸው በሊባኖስ በሚገኙ 400 ኢላማዎችን መምታቷን የሃገሪቱ የመከላከያ ሰራዊት አስታወቀ።

ኢላማዎቹ የሒዝቦላህ የሮኬት ማስወንጨፊያዎችና ሌሎች ወታደራዊ ተቋማትን ያካተቱ እንደሆኑ የእስራኤል መከላከያ ሰራዊት ቃል አቀባይ ኮለኔል ናዳቭ ሾሻኒ መግለጻቸውን አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል። የሊባኖስ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ግን  እስራኤል በደቡብ ሊባኖስ ባካሄደችው ጥቃት 3 ስቪሎች መገደላቸውን ገልጿል።

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ በበኩላቸው "ሒዝቦላህ እየፈጸመ ያለውን ጥቃት አንታገስም፤ በሚገባው ቋንቋ መልእክታችን እናደርስለታለን" ማለታቸውን የዘገበው ደግሞ ሮይተርስ ነው።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የአውሮፓ ህብረትና ዩናይትድ ስቴትስ በእስራኤልና ሒዝቦላህ መካከል የተፈጠረውን ውጥረት እጅጉን እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል።

የመሬት ሥር ሆስፒታል በእስራኤል

በሰሜን እስራኤል የሚገኙ ሆስፒታሎች ታካሚዎቻቸውን ከመሬት ሥር ወዳሉ ምሽጎች እንዲያዛውሩ ትዕዛዝ ተሰጠ። የእስራኤል መንግስት ይህን ያዘዘው ከሊባኖስ በኩል ከሂዝቦላሕ የሚወነጨፉ ሮኬቶች በህሙማኑ ላይ ጉዳት እንዳይደርስ ነው ተብሏል።

በዚሁም መሰረት ሃይፋ ውስጥ የሚገኘው ግዙፉ የራምባም ሆስፒታል ህሙማኑን ከምድር ስር 16 ሜትር ጠልቆ ወደተገነባው የአደጋ ጊዜ ሆስፒታል ማዛወር መጀመሩን ታውቋል። የምድር ሥር ሆስፒታሉ 1,400 ስቪሎችና ወታደሮች የሆኑ ህሙማንን የማስተናገድ አቅም አለው ተብሏል።

በሰላም ጊዜ የመኪና ማቆሚያ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ይህ የምድር ውስጥ ሆስፒታል የኬሚካልና ባዮሎጂካዊ ጥቃቶችን ለመከላከል በሚያስችል መልኩ እንደተገነባ የጀርመን ዜና አገልግሎት (DPA) ዘገባ ያመለክታል።

በኢራን በጋዝ ፍንዳታ ከ50 በላይ ሞቱ

በኢራን በአንድ የከሰል ማዕድን ማውጫ በተፈጠረ የጋዝ ፍንዳታ ከ50 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ተሰማ። በአደጋው 20 ሰዎች ላይም ጉዳት ደርሷል።

የደቡብ ኮራሳን ግዛት ገዢ አሊ አክባር ራሂሚ ለሃገሪቱ መንግስታዊ ቴሌቪዥን እንደገለጹት አደጋው የደረሰው በሁለት የማዕድን ማውጫ አካባቢዎች በተፈጠረ የጋዝ ፍንዳታ ምክንያት ነው። በአደጋው ቢያንስ 51 ሰዎች ሲሞቱ 20 ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል ነው ያሉት።

ይህ ደቡባዊ ግዛት የኢራን የከሰል ማዕድን ፍላጎት 76 በመቶ የሚመረትበት ሲሆን ከ8 እስከ 10 የሚሆኑ የከሰል ማዕድን አውጪ ኩባንያዎች በአካባቢው እንደተሰማሩ ሮይተርስ ዘግቧል።

በሩስያ የአየር ድብደባ 21 ዩክሬይናውያን ተጎዱ

ሩስያ በሰሜን ምስራቅ ዩክሬይን በምትገኘው የካርካይቭ ጋዛት ባካሄደችው የአየር ድብደባ 21 ስቪሎች መቁሰላቸውን የግዛቷ ባለስልጣናት አስታወቁ። ድብደባው የተከናወነው በስቪል መኖሪያ ቤቶች መሆኑን የገለጹት ባለስልጣናቱ በድብዳባው ከተጎዱት ውስጥ ህጻናትና የዕድሜ ባለጸጎች ይገኙበታል ብለዋል።

በሼቭቼንኪቭስኪ በሌሊት በተፈጸመው ድብደባ በርካታ መኖሪያ ቤቶች መውደም- መጎዳታቸውን የወረዳዋ ገዥ ኦሌህ ሲኒዬሁቦቭ ለአሶሽየትድ ፕረስ ገልጸዋል።

በአለፈው አርብ ሩስያ በአካባቢው በፈጸመችው ተመሳሳይ ጥቃትም 15 ሰዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ይታወቃል።

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።