1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስከረም 11 ቀን 2017 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tamirat Geletaቅዳሜ፣ መስከረም 11 2017

https://p.dw.com/p/4kvoH

ዕራብ አፍሪቃዊቷ ኒጀር መጠነ ሰፊ የወባ በሽታ መከላከያ ክትባት ዘመቻ ጀመረች ።

ሀገሪቱ ከቅርብ አመታት ወዲህ በምዕራብ አፍሪቃ የመጀመሪያው መጠነ ሰፊ የክትባት ዘመቻ ያካሄደች ሃገር የሚያደርጋትን ዘመቻ በሽታዉ ብርቱ ጉዳት አድርሶባታል በተባለላት በጋያ ከተማ መጀመሩን የሀገሪቱ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።  

በጎርጎርሳዉያን 2022 የወባ በሽታ በመላዉ ዓለም ከ660 ሺ ባላይ ለሚሆኑ ሰዎች ህልፈት ምክንያት ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 95 በመቶ የሚሆነው ሞት የተመዘ,ገበው አፍሪቃ ውስጥ ነው ተብሏል።

በዩናይትድ ኪንግደም የፋርማሲዩቲካል ቡድን ጂ ኤስ ኬ የተፈበረከው  የፀረ-ወባ መድሀኒት የዓለም የጤና ድርጅት በጎርጎሪዎሱ 2022 ተግባራዊ እንዲሆን ባጸደቀው መደበኛ የክትባት መርኃ ግብር መሰረት ኒጀር ውስጥ ተግባራዊ መሆን መጀመሩን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ክትባቱ ትኩሳት፣ ራስ ምታትና ብርድ ብርድ ማለትን ከሚያስከትሉ ከባድ የወባ ዓይነቶች ለመከላከል 75 በመቶ ውጤታማ እንደሚሆን መገመቱን ዘገባው አመልክቷል።

 

እስራኤል በሊባኖስ መዲና ቤሩት ባደረሰችው የአየር ጥቃት የሟቾች ቁጥር 37 ደረሰ ።

ከሟቾቹ ሶስት ህጻናት መሆናቸውን የሊባኖስ የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል። እስራኤል በበኩሏ በትናንቱ ጥቃት የሄዝቦላ የሬድዋን ኃይል አዛዥ ኢብራሂም አቂል እና ምክትሉን ጨምሮ 16 የጦር አዛዦችን መግደሏን አስታውቃለች።

ህዝብ ተጨናንቆ በሚኖርበት ደቡባዊ ቤሩት በአንድ ህንጻ የምድር ክፍል በስብሰባ ላይ በነበሩ የሄዝቦላ ወታደራዊ አመራር ላይ እስራኤል ባደረሰችው በዚሁ የአየር ጥቃት በ,ፈረሰው ህንጻ ውስጥ የነበሩ እና እስካሁንም ያልተገኙ በርካታ ሰዎች መኖራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

የሊባኖስ ጤና ሚኒስቴር ሚንስትር ፊራስ አባያድ እንዳሉት የህይወት አድን ሰራተኞች ሌሊቱን ሙሉ በፍርስራሽ ውስጥ የተቀበሩ ሰዎችን ሲያፈላልጉ አ,ድረዋል።

የእስራኤል ጦር በበኩሉ ምንም እንኳ ዝርዝር መረጃ ባይሰጥበትም ሊባኖስ ውስጥ የሚገኙ የሄዝቦላ ወታደራዊ ዒላማዎችን በተከታታይ ማጥቃት መጀመሩን አስታውቋል።

ከትናንቱ የእስራኤል የአየር ጥቃት አስቀድሞ አብዛኞቹ የሄዝቦላ አባላት በሆኑ ሰዎች በደረሰ የፔጀርስ ፍንዳታ 37 ሰዎች ሲገደሉ ከ2800 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቆስለዋል። ጥቃቱን ተከትሎ ቤሩትን ጨምሮ ሊባኖስ ዉስጥ ውጥረቱ ሲያይል  የታጣቂ ቡድኑን የደህንነት ዝግጅት ጥያቄ ውስጥ ማስገባቱ ተነግሯል። በተጨማሪም በሄዝቦላ ተዋጊዎች ላይም ብርቱ የስነ ልቦና ጉዳት ሳያደርስ እንዳልቀረ ዘገባው አመልክቷል።

 

በተያያዘ የእስራኤል ጦር ጋዛ ዉስጥ በአንድ ለመጠለያነት በሚያገለግል ትምህርት ቤት ላይ ባደረሰችው ጥቃት 22 ፍልስጥኤማዉያን መገደላቸውን የጋዛ የሲቪል መከላከያ ተቋም አስታውቋል። እስራኤል በበኳሏ በጥቃቱ ዒላማ ያደረግኩት የሃማስ ታጣቂዎችን ነው ብላለች።

በሺዎች የሚቆጠሩ ፍልስጥኤማዉያን ተፈናቃዮችን ባስጠለለ አልዛይቱን ትምህርት ቤት ላይ በደረሰው በዚሁ ጥቃት ከተገደሉት ውስጥ ስምንቱ ህጻናት መሆናቸውን የሲቭላዉያን ተከላካይ ቡድኑ ቃል አቃባይ መሀመድ ባሳል ተናግረዋል። ሌሎች 30 ያህል ሰዎች ደ,ግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል።

የእስራኤል ጦር በመግለጫው የአየር ኃይሉ “በጋዛ ከተማ በሚገኘው የሃማስ ማዘዣ እና መቆጣጠሪያ ማእከል ውስጥ ሲንቀሳቀሱ በነበሩ  አሸባሪዎች ላይ ትክክለኛ ጥቃት አድርሷል” ብሏል። ነገር ግን ጦሩ በጥቃቱ ስለተገደሉ ሰዎች ቁጥር እና ማንነት ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ተቆጥቧል።

በእስራኤል ሃማስ ጦርነት አብዛኞቹ ሲቪላዉያን የሆኑ የተገደሉ ፍልስጥኤማዉያን ቁጥር 41,391 መድረሱን የጋዛ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። በጋዛ ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ፍልስጥኤማዉያን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋል።

 

ዩክሬን በሞዕራባዊ ሩስያ ክራስኖዳር ግዛት ከፍተኛ ፍንዳታ ያስከተለ የድሮን ጥቃት ካደረሰች በኋላ ሩስያ ከ1,200 በላይ ነዋሪዎችን ከአካባቢው አስወጣች።

ዩክሬን ባደረሰችው በዚሁ የድሮን ጥቃት ተጨማሪ የፈንጂ ፍንዳታ ስጋት ሊከሰት ይችላል የሚል ስጋት ማደሩን የግዛቲቱ አስተዳደር አስታውቋል።

በማህበራዊ መገናኛ ገጾች ላይ ሲንሸራሸሩ የታዩ የቪዲዮ ምስሎች በጨለማ ውስጥ ርችት መሳይ ግዙፍ ፍንዳታ ሲከሰት ያሳያሉ ።  

የግዛቲቱ አስተዳዳሪ ኮንድራቲየቭ ድርጊቱን “በኪየቭ አገዛዝ የተፈጸመ የአሸባሪዎች ጥቃት” በማለት ገልጸዉታል። በዚህም ፍንዳታው በተከሰተበት አካባቢ የምትገኝ እና ስሟ ባልተጠቀሰ መንደር ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ መደረጉን ገልጸዋል።

በማህበራዊ መገናኛ ገጾች ላይ የተለቀቁ የፍንዳታ ቪዲዮዎች በትክክል ከጥቃቱ ጋር ስለመገናኘታቸው ግን ማረጋገጫ አላገኘም።

የሩስያ መከላከያ ሚኒስቴር ቀደም ሲል 101 የዩክሬን ሰው አልባ አውሮፕላኖች አብዛኛውን በብራያንስክ ክልል እና ሌሎች 18 ድሮኖችን በክራስኖዳር ክልል ውስጥ መትቶ መጣሉን አስታውቋል።

      ሩሲያ በየቀኑ ማለት በሚቻል መልኩ የዩክሬን ድርኖችን መትታ እየጣለች መሆኑን አስታውቃለች

 

ኢራን አዳዲስ የባለስቲክ ሚሳኤል እና የሰው አልባ አውሮፕላን አስተዋወቀች ።

ኢራን ወታደራዊ መሳሪያዎቹን ያስተዋወቀችው ዛሬ ቴህራን ውስጥ በቀረበ ወታደራዊ ትርኢት ላይ ነው። በመካከለኛው ምስራቅ እስራኤል በምዕርባዉያን በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ታጣቂ ቡድኖች ጋር እያደረገች ባለው ጦርነት ስሟ በተደጋጋሚ የሚነሳው ኢራን በወታደራዊ ትርዕኢቱ  ለዕይታ ያቀረበቻቸው  የጦር መሳሪያዎች ዉጥረቱን እንዳያባብሰው አስግቷል።

በኢራን አብዮታዊ ዘብ የተፈበረከው  ጂሃድ የሚል መጠሪያ የተሰጠው እና ጠጣር ነዳጅ የሚጠቀመው ሚሳኤል ከአንድ ሺ ኪሎ ሜትሮች በላይ ተምዘግዝጎ ዒላማዉን መምታት ይችላል ተብሎለታል።

ሻሂድ 136B  የሚል መጠሪያ የተሰጠው የሰው አልባ አውሮፕላኑ በበኩሉ በአንድ ጊዜ ከ4 ሺ በላይ ኪሎ ሜትሮችን ተጉዞ የተላከበትን ኢላማ መምታት እንደሚችል ነው ከወደ ኢራን የወጡ ዘገባዎች ያመለከቱት ።

ሩስያ በዩክሬን እያደረገች ላለው ጦርነት ኢራን ሜሳኤሎችን እና የሰው አልባ አውሮፕላኖችን ታቀርባለች ሲሉ ምዕራባዉያን ሃገራት ይከሳሉ ። ምንም እንኳ ኢራን የሚቀርብባትን ክስ ብታስተባብልም።

አዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን በጎርጎርሳዉያኑ በከ1980-88 ከሳዳም ሁሴን ኢራቅ ጋር የተደረገውን ጦርነት በማሰብ በቴህራን የተካሄደውን አመታዊ ወታደራዊ ትርዒት ታድመዋል።

ታምራት ዲንሳ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።