1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የመስቀል በዓል በጉራጌ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ዓርብ፣ መስከረም 17 2017

መቼም ጉራጌና መስቀል ያላቸው ቁርኝት እንዲህ በቀላሉ የሚገለጽ አይደለም ፡፡ ጉራጌዎች የአዛውንቶች ምርቃት የሚቀበሉት የትዳር ጓደኛቸውን የሚያጩት በመስቀል ሰሞን ነው ፡፡ በዘንድሮው የመስቀል የበዓል ድባብ ጥሩ ቢሆንም፤አንዳንዶች ከመሀል ከተማ ወደ ጉራጌ በስጋት መጓዛቸውን ገልፀዋል።

https://p.dw.com/p/4l9wh
Äthiopien I Meskel-Fest
ምስል Gurage zone Cultural office

የመስቀል በዓል አከባበር በጉራጌ

«ጉራጌ መስቀል ሲገባ፤ ጭር አለች አዲስ አበባ» ይባላል። እንደዛሬ ያለው የመስቀል በዓል ለጉራጌዎች ልዩ ነው ይባላል ፡፡ ዓመቱን በሥራ ሲባትሉ የከረሙት ጉራጌዎች ዛሬ በየአጥቢያቸው ወይም በእነሱ አጠራር  “ በጆፈረ “ የሚሰባሰቡበት ዕለት ነው ፡፡
በጾታና በዕድሜ ተከፋፍሎ የሚከበር የጉራጌ መስቀል በተለይ ለወላጆች ምርቃት  ልዩ ሥፍራን ይሰጣል ፡፡ምርቃት ለጉራጌእንደሥንቅ ነው ፡፡ ቀጣይ ህይወቱ ያማረ ፣ ሀሳቡና ህልሙ የሰመረ የሚሆነው የግል ጥረቱ በምርቃት ሲታገዝ እንደሆነ ይታመናል ፡፡ ለዚህም ነው ጉራጌ በመስቀል ወላጆቹን ጋቢ እና ኩታ በማልበስና  አናታቸው ላይ ቅቤ በማስቀመጥ ምርቃቱን የሚሰበስበው  ፡፡

ለ2017 መስቀል ወደ ገጠር የተመሙት የጉራጌ ብሄርተወላጆች በዓሉን እንደየአቅማቸው እያከበሩ እንደሚገኙ ይናገራሉ ፡፡ በዓሉ ዓርብ ላይ ማረፉ ግን ቄቤን እንደውሃ ከሚጠጣው የጉራጌ ክትፎ እንዳንገናኝ አድርጎናል ይላሉ ፡፡
በቤተ ጉራጌ መስቀል ለአንድ ቀን ብቻ ተከብሮ የሚያልፍ በዓል  አይደለም። በዓሉ እስከመጪው ጥቅምት 5 ድረስ በተለያዩ ዝግጅቶች መከበሩን ይቀጥላል ። በእነኝህ ቀናት ተራርቀው የቆዩ  ቤተዘመድ ይጠያየቃሉ ፡፡ ወጣቶችም ከወደፊት የትዳር አጋራቸው ጋር ይተጫጫሉ ፡፡ አጋር የሌላቸው ደግሞ አይናቸው የገባችውን የሚመርጡት በዚሁ የመስቀል ሰሞን ነው ፡፡

የመስቀል በዓል አከባበር በጉራጌ
የመስቀል በዓል አከባበር በጉራጌምስል B. Haile

ከጉራጌ በተጨማሪ በማዕከላዊና ደቡብ ኢትዮጵያክልሎች ለሚገኙ አብዛኞቹ ህዝቦች የመስከረም ወር አጋማሽ በዋነኛ የበዓል ወርነቱ ይታወቃል  ፡፡ ፡፡ በዎላይታ ጊፋታ በከምባታ መሰላ በጋሞና ዶርዜ ዮዮ መስቀላ አሁን ድረስ የበዓል ድባባቸው እንዳለ ነው  ፡፡ እነኝህ ህዝቦች ከያዝነው ሳምንት መግቢያ አንስቶ የአዲስ ዘመን ሽግግር ማብሰሪያዎቻቸው እንደባህልና ወጋቸው  እያከበሩ ይገኛሉ ፡፡


ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ
ፀሐይ ጫr