1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችአፍሪቃ

የሐምሌ 5 ቀን 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

Shewaye Legesseዓርብ፣ ሐምሌ 5 2016

ኻርቱም፤ የሱዳን ፖሊስ የውጪ ዜጎች ከኻርቱም እንዲወጡ ማዘዙ ናይሮቢ፤ የኬንያ ፖሊስ አዛዥ ሥራቸውን ለቀቁ ናይሮቢ፤ የኬንያ ወጣቶች ተቃውሟቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ማስጠንቀቃቸው ጄኔቫ፤ የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይላት ለውይይት ጄኔቫ ሞስኮ፤ ሩሲያ በኔቶ ጉባኤ የባይደንን ስህተት ዓለም ልብ ይበልልኝ ማለቷ ካታማንዱ፤ ኔፓል ውስጥ የደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ

https://p.dw.com/p/4iEqZ

ኻርቱም፤ የሱዳን ፖሊስ የውጪ ዜጎች ከኻርቱም እንዲወጡ ማዘዙ

የሱዳን የጸጥታ ኃይሎች የውጪ ዜጎች ከዋና ከተማዋ ኻርቱም እና በዙሪያ ካሉ አካባቢዎች እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጡ። ፖሊስ ባወጣው ማሳሰቢያ መሠረት የውጪ ዜጎች ከተባለው የሱዳን አካባቢ ለመውጣት የሁለት ሳምንት ጊዜ ብቻ ነው የተሰጣቸው። በመንግሥት ወታደሮችና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል የሚካሄደው ውጊያ ተጠናክሮ በመቀጠሉ የውጪ ዜጎች ለራሳቸው ደህንነት ሲሉ አካባቢውን ለቀው መውጣት እንዳለባቸው ፖሊስ አሳስቧል። ሮይተር መገናኛ ብዙሃንን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ውስጥ የሌላ ሀገር ቅጥር ነፍሰገዳዮች የመኖራቸው ዘገባ ይፋ ከሆነ በኋላ፤ በተለይ ከሌሎች የአፍሪቃ ሃገራት በመጡ የውጪ ዜጎች ላይ ጥላቻ ይስተዋላል። ከቀናት በፊት ሕጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ከ150 በላይ የውጪ ዜጎች መታሰራቸውንም አመልክቷል።    

 

ናይሮቢ፤ የኬንያ ፖሊስ አዛዥ ሥራቸውን ለቀቁ

የኬንያ ፖሊስ አዛዥ ሥራቸውን ለቀቁ። በሀገሪቱ በተቀጣጠለው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ በርካቶች መሞታቸውን ተከትሎ ጠንካራ ትችት የተሰነዘረባቸው የፖሊስ አዛዥ ጃፌት ኮሜ በዛሬው ዕለት የስንብት ደብዳቤ አስገብተዋል። የኬንያ ፕሬዝደንት ጽሕፈት ቤት የኮሜን የስንብት ደብዳቤ ፕሬዝደንት ዊልያል ሩቶ መቀበላቸውን አረጋግጧል። ጽሕፈት ቤቱ አክሎም በቦታቸው ምክትል የኬንያ ፖሊስ አዛዥ የነበሩት ዳግላስ ካንጃ መተካታቸውን አስታውቋል። በሀገሪቱ የተካሄደውን ፀረ መንግሥት ተቃውሞ ያደራጀው ጀነሬሽን Z በአጭሩ ጄን Z የተሰኘው የኬንያ ወጣቶች ስብስብ በሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ የኃይል እርምጃ ወስዷል ያሉት የኬንያ ፖሊስ አዛዥ ሥልጣናቸውን እንዲቀቁ ግፊት ሲያደርግ ነበር።

 

ናይሮቢ፤ የኬንያ ወጣቶች ተቃውሟቸውን ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ማስጠንቀቃቸው

የኬንያ ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ ምንም እንኳን ትናንት ሚኒስትሮቻቸውን ቢያሰናብቱም የሀገሪቱ ወጣቶች እሳቸውም ከሥልጣን ካልወረዱ ዳግም ለተቃውሞ አደባባይ እንደሚወጡ አስጠነቀቁ። ሩቶ በግብር ጭማሪ ምክንያት በመላ ሀገሪቱ የተቀጣጠለውን ተቃውሞ ለማብረድ እየታገሉ ነው። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች አማካኝነት ጄን ዚ በሚል ስያሜ በተሰባሰቡ ወጣቶች የሚመራው ተቃውሞ የሩቶን አስተዳደር እጅግ የከፋ ቀውስ ውስጥ ከቶታል። ሩቶ የገነፈለገው የኬንያን ሕዝብ ቁጣ ለማብረድ ትናንት ከጥቂቶች በስተቀር ዋና አቃቤ ሕጉን ጨምሮ አብዛኞቹን ሚኒስትሮቻቸውን አሰናብተዋል። ምንም እንኳን እርምጃቸው በአንዳንዶች ተቀባይነት ቢያገኝም፤ አንዳንድ ወጣቶች ግን አሁንም ሩቶ የዛሬ ሁለት ዓመት ወደ ሥልጣን ሲመጡ ቃል የገቡትን ተግባራዊ አላደረጉም የሚለው ቁጣቸው የበረደ አይመስልም።

 

ጄኔቫ፤ የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይላት ለውይይት ጄኔቫ

የሱዳን ተቀናቃኝ ኃይላት ተወካዮች ከተመድ ልዑክ ጋር ለመነጋገር ጄኔቫ ስዊዘርላንድ መግባታቸው ተነገረ። ምንም እንኳን የሱዳን መንግሥት ጦር እና የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ወኪሎች ጄኔቫ ቢገቡም ከመንግሥታቱ ድርጅት የሱዳን ልዩ መልእከተኛ ራምታኔ ላምማራ ጋር ለመነጋገር እስካሁን አንደኛው ወገን ወደ መሰብሰቢያው ስፍራ አለመሄዱ ተገልጿል። እንዲያም ሆኖ የመንግሥታቱ ድርጅት ቃል አቀባይ አሌሳንድራ ቬሉቺ የየትኛው ወገን እንዳልተገኘ መግለጽ አልፈልግም ነው ያሉት። ላማምራ የየቡድኑን ተወካዮች በተናጠል የማነጋገር እቅድ እንደነበራቸው አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ከስፍራው የላከው ዜና ያስረዳል። ጄኔቭ በሚገኘው የድርጅቱ ጽሕፈት ቤት ዛሬ የተጀመረው ድርድር፤ ምን ያህል ጊዜ ሊወስድ እንደሚችል አልተነገረም።

 

ሞስኮ፤ ሩሲያ የኔቶ እርምጃ አደገኛ ነው ማለቷ

ሩሲያ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ኔቶ አባል ሃገራት ለዩክሬን የጦር መሣሪያ መላካቸው ውጥረቱን የሚያባብስ አደገኛ እርምጃ ነው ስትል አስጠነቀቀች። የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ዛሬ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ ለዩክሬን የሚሰጡት መሣሪያዎች ሩሲያ ላይ ጥቃት ለማድረስ እየዋሉ እንደሆነ አመልክተዋል።

«አስቀድመን እንደተናገርነው ከኔቶ ጉባኤ የሚወጡ መረጃዎችን በሙሉ በቅርብ እየተከታተልን ነበር፤ እና ደግሞ ይህ ርዕሰ ጉዳይ በጣም ተንኳሽ ነው። ከአንዳንዶቹ ዋና ከተሞች ማለትም ከለንደንና ከመሳሰሉት የሚተላለፉ መግለጫዎችን ተመልክተናል፤ አንዳንዶቹ ምን ገደብ የላቸውም። እንዲህ ያሉ የረዥም ርቀት ሚሳኤሎችን የመጠቀም ነጻነትን በተመለከተ የተወሰነ ሚዛናዊነትን ለመጠበቅ የሚሞክሩ ሃገራትንም እናያለን። ሆኖም ግን በመጨረሻ እነዚህ ሚሳኤሎች የእኛን ግዛቶች ሊመቱ ይችሉ ይሆናል። ሉዋንስክ፤ ዶንትስክ፤ ኬሄርሶን እና ሴፖሬዢያ የሩሲያ ፌዴሬሽን ግዛቶች መሆናቸውን አንዘንጋ። ርቀቱን መጨመሩ፤ አዲስ ውጥረቱን የሚያባባስ፤ በጣም አደገኛ ግልፅ ትንኮሳ ነው።»

ከዚህም ሌላ ሩሲያ በኔቶ ጉባኤ ላይ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንትን የምላስ ወለምታ ዓለም ልብብ ይበልልኝ ብላለች።  በኔቶ ጉባኤ ላይ በኋላ ቢያስተካክሉትም ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፤ የዩክሬኑን ፕሬዝደንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪን ሲያስተዋውቁ፤ በስህተት የሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ማለታቸው የክሬምሊንን ትኩረት ስቧል። የተፈጠረውን ስህተት ባስተካከሉበት ንግግራቸው ባይደን የዘለንስኪን ስም የዘነጉት« ፑትንን ማጥቃት ላይ በማተኮራቸው መሆኑን ተናግረዋል። ከዚህም ሌላ ባይደን ተቀናቃኛቸው ዶናልድ ትራምፕን ምክትሌ ማለታቸውን የጠቀሰው ክሬምሊን፤ ዞሮ ዞሮ ጉዳዩ የአሜሪካን መራጮች ኃላፊነት እንጂ የሩሲያ አይሆንም ነው ያለው። ዲሚትሪ ፔስኮቭ እንዲህ ያለው የምላስ ወለምታ ክብረነክ በመሆኑ ሀገራቸው አትቀበለውም ነው ያሉት።

 

ካታማንዱ፤ ኔፓል ውስጥ የደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ

በዛሬው ዕለት ኔፓል ውስጥ የደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ ሰዎች የጫኑ ሁለት አውቶብሶችን ሞልቶ የደፈረሰ ወንዝ ውስጥ ከተተ። በዚህ አደጋም በትንሹ 62 ሰዎች እስካሁን የደረሱበት አልታወቀም። ባለሥልጣናት የጦር ኃይልና ፖሊሶችን በማስተባበር ፍለጋ እያካሄዱ መሆኑን ቢገልፁም የወንዙ ሙላት ባለመጉደሉ ፍለጋውን አዳጋች እንዳደረገው አመልክተዋል። በአውቶብሶቹ ከተሳፈሩት ሦስት ሰዎች አደጋው እንደደረሰ ጭቃ እና የድንጋይ ናዳ መኪናውን ከፍተው ወደሞላው ወንዝ ውስጥ ሳይከቱት አስቀድመው ዘለው በመውጣት ቢጎዱም ሕይወታቸው መትረፉን ሮይተርስ ዘግቧል። በአደጋው ከጠፉት መካከል የሕንድ ዜጎችም መኖራቸው ተገልጿል። በሌላ የሀገሪቱ ክፍልም እንዲሁ በተመሳሳይ የመሬት መንሸራተት አደጋ የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉም ተገልጿል። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ካማል ዳሃል በደረሰው አደጋ የተሰማቸውን ሀዘን በመግለጽ የጠፉትን ወገኖች ፍለጋው ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ገጻቸው መልእክት አስተላልፈዋል።

ሸዋዬ ለገሠ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።