1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ/ም የዓለም ዜና

Tsehay Filatieረቡዕ፣ ሐምሌ 24 2016

DW Amharic -በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የሟቾችን አስክሬን የማፈላለጉ ሥራ ማብቃቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት አስታወቀ ፡፡-የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የህወሃት አመራሮችን ኮነነ። ጊዚያዊ አስተዳደሩ የህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ /ህወሓት/ አመራሮችን የኮነነው፤ በሙስና እና በተደራጀ የማዕድን የመሬት ዘረፋ ፣ በመሳሪያ ንግድ እና በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ነው።-የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የግድያ ሙከራ ተፈጸመባቸው።-የሃማስ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ ኢራን ውስጥ ከጠባቂያቸው ጋር ተገደሉ።

https://p.dw.com/p/4iydj

ዓርዕስተ  ዜና 

-በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ  የሟቾችን አስክሬን የማፈላለጉ  ሥራ ማብቃቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት አስታወቀ ፡፡

-የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የህወሃት አመራሮችን ኮነነ። 
ጊዚያዊ አስተዳደሩ የህዝባዊ ወያነ ሀርነት ትግራይ /ህወሓት/ አመራሮችን የኮነነው፤ በሙስና እና በተደራጀ የማዕድን የመሬት ዘረፋ ፣ በመሳሪያ ንግድ እና በህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ነው።

-የሱዳን ወታደራዊ መሪ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን የግድያ ሙከራ ተፈጸመባቸው።በዚህ የግድያ ሙከራ አል-ቡርሃን ላይ የደረሰ ጉዳት የለም ሲሉ ቃል አባያቸው ገልፀዋል። 


-የሃማስ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ ኢራን ውስጥ ከጠባቂያቸው ጋር ተገደሉ። ግድያውን ተከትሎ በፍልስጤም አንጃዎች  በዌስት ባንክ የተቃውሞ ሰልፍ እና አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማ ተጠርቷል።የሀማስ ተቀናቃኝ የሆነው የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት የማሕሙድ አባስ፣ ፋታህም ግድያውን አውግዟል።

-ሩሲያ ኪየቭን  በሰው አልባ አውሮፕላኖች ስትደበድብ መዋሏን  የዩክሬን ባለስልጣናት ገለፁ ።ጥቃቱ ሩሲያ በታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መዘርጋት ላይ ያተኮረ ሶስተኛውን ልምምድ መጀመሯን ተከትሎ  ነው ተብሏል። 


በጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ በደረሰው የመሬት መንሸራተት አደጋ የቀሪ ሰዎችን አስክሬን የማፈላለጉ  ሥራ ማብቃቱን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት አስታወቀ ፡፡
የክልሉ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ እንዳስታወቀው ያልተገኙ ሟቾችን የመፍልጉ ሥራ ያበቃው አደጋው ከተከሰተበት ከባለፈው ሐምሌ 15 ጀምሮ እስከ ትናንት ድረስ የቁፋሮ ሥራው ሲካሄድ ከቆየ በኋላ ነው ፡፡
በፍለጋው 243 አስክሬን በማግኘት በክብር እንዲያርፍ ሲደረግ የ6 ሰዎች እስክሬን ግን እስከ ትናንት ተፈልጎ አለመገኘቱን ነው የቢሮው ሃላፊ ወይዘሮ ሠናየት ሰሎሞን ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የተናገሩት ፡፡
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸውን ለመለየት በአካባቢው ነዋሪዎች የቤት ለቤት መረጃ የማሰባሰብ ሥራ መከናወኑን የጠቀሱት የቢሮ ሃላፊዋ አስክሬናቸው ሊገኝ ያልቻሉ የአደጋው ሰለባዎችን ለመዘከር በቦታው መታሰቢያ ለማኖር መታቀዱን ገልፀዋል።
በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው 15 ሰዎች ህክምና እየተደረገላቸው እንደሚገኙና አብዛኞቹም በጥሩ ጤንነት ላይ መሆናቸው የቢሮ ሃላፊዋ ተናግረዋል ፡፡
አደጋው ከደረሰበት ጊዜ አንስቶ ኢትዮጵያውያን ከሀገር ውስጥና ከውጪ የሚያደርጉት ድጋፍ እሁን ድረስ መቀጠሉን የጠቀሱት ወይዘሮ ሠናየት እስከአሁን በጥሬ ገንዘብ 50 ሚሊዮን ብር ፤ በዓይነት ደግሞ ከ70 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት የቁሳቁስ ድጋፍ ተገኝቷል ብለዋል ፡፡
.
የትግራይ ክልል ጊዚያዊ አስተዳደር የህወሃት አመራሮችን ኮነነ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር እና የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አቶ ጌታቸው ረዳ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለክልሉ ቴሌቪዥን ጣቢያ በሰጡት ቃለመጠይቅ፥ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች የጊዚያዊ አስተዳደሩን ሥራዎች ሆን ብሎ በማደናቀፍ እና በማጥላላት ላይ መሰማራታቸውን ተናገሩ።
አቶ ጌታቸው አያይዘውም በየደረጃው ያሉ አመራሮች እና የአስተዳደር መዋቅርም በሕገወጥ የማዕድናት ዝርፊያ፣ ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በመሬት ወረራ፣ በጦር መሳርያዎች ሽያጭ እና በሌሎች ሕገወጥ ተግባራት ተሳትፎ እንዳለው ገልፀዋል። 
ህወሓት በየጊዜው የሚያካሂዳቸው ረዣዥም ስብሰባዎች የትግራይን ወቅታዊ ሁኔታ ገምግሞ የመፍትሔ አቅጣጫ የሚያስቀምጡ ሳይሆኑ የሥልጣን ሽኩቻ መድረኮች መሆናቸውም አቶ ጌታቸው አመልክተዋል።
በሌላ በኩል በትግራይ የሚንቀሳቀሱ ሦስት የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች በጋራ በሰጡት መግለጫ ፣ ህወሓት የውስጥ ሽኩቻው ወደ ህዝብ ለማስገባት እየሠራ ነው በማለት የወቀሱ ሲሆን፥የፌደራል መንግሥቱም አለመግባባት ሲፈጠር በትግራይ ህዝብ ላይ ማስፈራሪያ ከመሰንዘር እንዲቆጠብ ጥሪ አቀርበዋል። 
ፓርቲዎቹ ከዚህ ቀደም በጋራ ባወጡት መግለጫም የትግራይ ህዝብን ችግር በወጉ እየፈታ አይደለም በሚል ጊዚያዊ አስተዳደሩን ተችተዋል።

የሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ላይ የግድያ ሙከራ ተፈጸመ።
የሱዳን ጦር ኃይሎች አዛዥ ጄኔራል አብደል ፋታህ አል-ቡርሃን ላይ የግድያ ሙከራ መደረጉን ሮይተርስ የዜና ምንጭ  የዐይን እማኞችን ጠቅሶ ዘግቧል።በአል-ቡርሃን ላይ የግድያ ሙከራ የተፈጸመው በድሮን ጥቃት መሆኑንም የዜና ምንጩ ገልጿል። 
 ጥቃቱ የተፈጸመው የአገሪቱ ጦር ዋና መቀመጫው ካደረጋት ፖርት ሱዳን በ100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኝ ጊቤት በተባለ የጦር ሰፈር ውስጥ ሲሆን፤ የግድያ ሙከራው በሱዳን ጦር ሠራዊት እና በአማፂው የፈጥኖ ደራሽ ሀይል  መካከል ስዊዘርላንድ ውስጥ የሰላም ድርድር ከመጀመሩ በፊት ነው ።
 አምስት ሰዎች ከተገደሉበት  የሰው አልባ አውሮፕላን  ጥቃት አልቡርሃን አንዳችም ጉዳት ሳይደርስባቸው መውጣታቸውን የጦር ሠራዊቱ የጦር ሠራዊቱ ቃል አቀባይ ሀሰን ኢብራሂም ዛሬ አረጋግጠዋል ። 
የግድያ ሙከራው የተፈጸመው ጄኔራል አል-ቡርሃን በምሥራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በሠራዊት የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ታድመው በነበረበት ወቅት፤ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ነው ተብሏል።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ግን እስካሁን ያለው ነገር የለም።
በሱዳን በጄኔራል አል-ቡርሃን በሚመራው የሀገሪቱ ጦር እና  በጄኔራል ሞሐመድ ሐምዳን ዳጋሎ /ሔምቲ/ በሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል ላለፉት 15 ወራት በርካቶችን ለሞት እና ለመፈናቀል የዳረገ   ደም አፋሳሽ ጦርነት እየተደረገ ይገኛል።

የሃማስ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ ኢራን ውስጥ ከጠባቂያቸው ጋር ተገደሉ።
የሃማስ እና የኢራን አብዮታዊ ዘብ ዛሬ  እንደተናገሩት የሃማስ መሪ እስማኤል ሃኒዬ በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን ተገድለዋል። እስራኤል፤ ዩናይትድ ስቴትስ፣ የአዉሮጳ ኅብረት፣ ብሪታንያና ተከታዮቻቸዉ በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤሙ ታጣቂ ቡድን ሐማስ  የፖለቲካ መሪ ሃኒዬ የተገደሉት ቴህራን በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤታቸው በተፈጸመ ጥቃት ሲሆን፤ ግድያው ምርመራ እየተደረገበት መሆኑም ተገልጿል።
የሀማሱን መሪ  መገደላቸውን ተከትሎ ፤ሐማስ  ባወጣው መግለጫ መሪው የተገደሉት ከአንድ ጠባቂያቸው ጋር በእስራኤል በተፈጸመ ጥቃት መሆኑን አሳውቋል።
አንድ የሀማስ ከፍተኛ ባለሥልጣን በበኩላቸው እስማኤል ሃኒዬህ በእስራኤል ጥቃት መገደላቸውን በመግለጽ ሀማስ ለዚህ ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
እንደ ሮይተርስ ዘገባ በዌስት ባንክ የሚገኙ ፍልስጤማውያንም ግድያውን አውግዘው በእስላማዊ ንቅናቄው ላይ  ብዙም ተፅዕኖ እንደሌለው ገልፀዋል።
ግድያውን ተከትሎ በፍልስጤም አንጃዎች  በዌስት ባንክ የተቃውሞ ሰልፍ እና አጠቃላይ የስራ ማቆም አድማ ተጠርቷል።የሀማስ ተቀናቃኝ የሆነው የፍልስጤሙ ፕሬዝዳንት የማሕሙድ አባስ፣ ፋታህም ግድያውን አውግዟል።
የሃማስ መሪ እስማኤል ሃኒዬህ መገደልን ተከትሎ በእስራኤል እና በፍልስጤም መካከል ለወራት የዘለቀው ግጭት ይባባሳል የሚል ስጋት አሳድሯል።
በቴህራን ለተፈፀመው የሃኒዬ ግድያ የእስራኤል ባለስልጣናት እስካሁን  ሃላፊነቱን አልወሰዱም።የአዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዜሽኪያን መንግስት በኩልም ስለግድያው 
የተሰጠ ይፋዊ አስተያየት የለም።ሟቹ በቅርቡ በአዲሱ የኢራን ፕሬዝዳንት  በዓለ ሲመታት ላይ ተገኝተው ነበር።

ሩሲያ ኪየቭን  በሰው አልባ አውሮፕላኖች ስትደበድብ መዋሏን  የዩክሬን ባለስልጣናት ገለፁ ።
የዩክሬን አየር ሃይል እንዳስታወቀው የሩስያ ጦር ሃይሎች አንድ የክሩዝ ሚሳኤል እና 89 የኢራን ሰራሽ  ሰው አልቫ አውሮፕላን ጥቃቶችን  በኪዬቭ በአንድ ጀምበር መሞከራቸውን የዩክሬን አየር ሃይል አስታወቋል።ነገር ግን በጥቃቱ ምንም አይነት ጉዳት እንዳልደረሰ ባለስልጣናቱ ተናግረዋል። 
ጥቃቱ ሩሲያ በታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ መዘርጋት ላይ ያተኮረ ሶስተኛውን ልምምድ መጀመሯን ተከትሎ  መሆኑ ታውቋል።
ሩሲያ በታክቲካል የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ዝርጋታ ላይ ያተኮረ ሶስተኛውን ልምምድ ጀምራለች ሲል የሀገሪቱ መከላከያ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።
የሩሲያ የመከላከያ ሚኒስቴር በቴሌግራም ገፁ እንዳሰፈረው «በሩሲያ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ውሳኔ መሠረት ስትራቴጂክ ያልሆኑ  የኑክሌር ኃይሎች ሦስተኛው ልምምድ ተጀምሯል»ብሏል ።
ወታደራዊ ልምምዱ ወታደሮችን በሚሳይሎች  እና ሌሎች የጦር መሳሪያዎች አጠቃቀም ላይ  ለማሰልጠን ነው።
የመጀመሪያው  ደረጃው የኒውክሌር ልምምዶድ   በግንቦት ወር የተጀመረ ሲሆን፤ ሁለተኛ ደረጃው ደግሞ ቤላሩስ በተሳተፈችበት በሰኔ ወር  ተካሂዷል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በየካቲት 2022 የሩስያ የዩክሬን ወረራ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ አስቸጋሪ ሁኔታ ከገጠማቸው የኒውክሌር ጦር መሳሪያዎችን እንደሚጠቀሙ ጠቅሰዋል። 
እንደ ክሪሚሊን ፑቲን እነዚህን ልምምዶች በግንቦት ወር መጀመሪያ ላይ ያስጀመሩት  ከምዕራባውያን ሀገራት ለሚሰነዘሩ ዛቻዎች ምላሽ ነው ። በተለይም የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን  ወታደሮቻቸውን  ወደ ዩክሬን ለመላክ ዕቅድ እንዳላቸው  ከጠቀሱ በኋላ።

19ኛው የአውሮፓ የስፖርትና የባህል ውድድር በቤልጅየም መካሄድ ጀመረ 
ከትናንት ማክሰኞ ሀምሌ 23 ቀን ጀምሮ በቤልጅየም ጌንት የሮንሰ የስፖርት ማእዕከል በመካሄድ ላይ የሚገኘው 19ኛው የአውሮፓ የስፖርትና የባህል ውድድር አውሮፓ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት ነው።
በውድድሩ በተለያዩ ያውሮፓ አገሮች የሚገኙ፤ የትውልደ ኢትይጵያውያን የእግር ኳስ ቡድኖች የሚሳተፉ መሆኑን የፌዴሬሺኑ ፕሬዝድናት አቶ አሳየኸን ጥላሁን  በተለይ ለዶቼቬለ ገለጸዋል።
በጎርጎሪያኑ በ2002 ዓ/ም የተቋቁመው የአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርት ፌዴሬሺን ዋና ዓላማው ትውልደ ኤትዮጵያውያንን ማገናኛነትና ኢትዮጵያዊነትን ማክበር መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ ፤ፊዴሬሽኑ ፊዴሬሽኑ በኦሎምፒክ ቻርተር የሚመራ በመሆኑ ከዘር ፣ከሀይማኖት እና  ከፖለቲካ  ወገንተኝነት የፀዳ ነውም ብለዋል።
 ለአራት ቀናት በሚዘልቀው በዚህ ዝግጅት በክቡር ይደንቃቸው ተሰማ የተሰየመውን የአንደኛ ዲቪዚዮን ዋናጫና  በወጣት አበበ ገብረመድህን የተሰየመውን የሁለተኛ ዲቪዮን ዋንጫ  አሸናፊዎችን ለመለየት ከሚደረጉት የእግር ኳስ ውድድሮች በተጨማሪ፤ በርካታ ታውቂ የጥበብ ሰዎች የሚሳተፉባቸው የባህል ዝግጅቶች መኖራቸውን አቶ አሳየኸኝ አክለው ገልጸዋል

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።