1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐምሌ 21 ቀን 2016 የዓለም ዜና

Yohannes Gebreegziabherእሑድ፣ ሐምሌ 21 2016

https://p.dw.com/p/4iq2J

በተከዘ ወንዝ ጀልባ በመስጠሟ የ12 ሰዎች ሕይወት አለፈ

በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ከሳህላ ሰየምት ወረዳ ወደ ዝቋላ ወረዳ 26 ሰዎችን አሳፍራ በተከዘ ወንዝ ላይ ስትጓዝ የነበረች ጀልባ በመስጠሟ 12 ተሳፋሪዎች ለህልፈት ተዳረጉ።  
ጀልባዋ በድምሩ 26 ሰዎች አሳፍራ የነበረች ሲሆን ሰባቱ በዋና ሲወጡ 7ቱ ደግሞ በአካባቢው ነዋሪዎች እገዛ በሕይወት ቢተትፉም በአደጋው በመዳከማቸው ወደ ሕክምና ተወስደዋል። እስከአሁን የ2 ሰዎች አስከሬን መገኘቱንና ፍለጋው መቀጠሉን ታውቋል።

ህወሓት ሕጋዊነቱ እንዲመለስለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡ

ህወሓት ሕጋዊነቱ እንዲመለስለት ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጥያቄ ማቅረቡ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ተናገሩ።  ሰሞኑን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር በተወያዩበት ወቅት ህወሓት ያቀደው ሕገወጥ ያሉት ድርጅታዊ ጉባኤ  ወደ ጦርነት ሊያመራ እንደሚችል መግለጻቸውን ተከትሎ ወደ አዲስአበባ በማምራት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መነጋገራቸው አስታውቀዋል። 

ትላንት በትግራይ ለሚገኙ መንግስታዊ እና የፓርቲው ሚድያዎች ማብራሪያ የሰጡት የህወሓት ሊቀመንበር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል ህወሓት ለምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስለት ጥያቄ ማቅረቡንና በሁለት ሳምንት ውስጥ ምላሽ እንደሚጠብቅ ተናግረዋል። ህወሓት የነበረው ሕጋዊ ሰውነቱ እንዲመለስ እንጂ እንደአዲስ ፓርቲ መመዝገብ እንደማይፈልግ ደብረፅዮን ጨምረው ገልፀዋል። 

ዶክተር ደብረጽዮን አክለውም በቅርቡ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ህወሓት ከምርጫ ቦርድ ሕጋዊ ሰውነት ሳያገኝ ወደ ጉባኤ የሚያመራ ከሆነ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል ማለታቸው ተገቢ አለመሆኑ እና በዚሁ ጉዳይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተገናኝተው መነጋገራቸው ጠቁመዋል። 

በሌላ በኩል የትግራይ ኮምኒኬሽን ጉዳዮች ፅሕፈት ቤት ባወጣው መግለጫ  "የግዚያዊ አስተዳደሩ ዋነኛ ተግባር ዘላቂ ሰላምና  መረጋጋት ማስፈን ነው" ብሏል። ከዚህ ውጭ የሚደረግ "ሰላም የሚያውኩ፣ ሕገወጥነት የተላበሱ" ብሎ የገለፃቸው ተግባራት ግን አይታገስም ሲል ማስጠንቀቁን የመቐለው ወኪላችን ሚልዮን ሃይለስላሴ ዘግቧል።

በቤኒን 12 የመንግስት ታጣቂዎች ተገደሉ

በቤኒን ብሔራዊ ፓርክ 7 የመንግስት የጸጥታ ሐይል አባላትና ሌሎች 5 ሬንጀርስ በመባል የሚታወቁ የጥብቅ ደን ጠባቂዎች መገደላቸውን ከአካባቢው የወጡ መረጃዎች አመላከቱ። ገዳዮቹ ጽንፈኛ የእስልምና ሃይማኖት አክራሪዎች ሳይሆኑ እንዳልቀረ ተነግሯል።
ከማክሩ ወንዝ ብዙም በማይርቀውና ወደ 10,000 ስኬር ኪሎሜትር ስፋት ባለው ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ስለተፈጸመው ግድያ የሐገሪቱ መንግስት እስከ አሁን ያለው ነገር የለም። ይሁንና ጥብቅ ደኑ ከቡርኪናፋሶና ኒጀር በሚዋሰነው በዚሁ አካባቢ ከአልቓኢዳ ጋር ግኑኝነት አላቸው ተብለው የሚጠረጠሩ ጽንፈኛ ታጣቂዎች በስፋት እንደሚንቀሳቀሱበትና ወደ ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ ሐገራት ሰርገው ለመግባት እንደወታደራዊ መቀመጫ እንደሚጠቀሙበት አሶሽየትድ ፕረስ ዘግቧል። 

በሳይበሪያ ሰደድ አሳት ከ1 ሚልዮን ሄክታር በላይ ደን እየነደደ ነው።

በሰሜን የሩስያ ግዛት በሚገኘው ሳይበሪያ በተነሳው ሰደድ አሳት ከ1 ሚልዮን ሄክታር በላይ ደን እየነደደ ነው። የእሳት አደጋ መከላከያና በጎ ፈቃደኞች እሳቱን በአውሮፕላኖች ጭምር እየታገዙ ለማጥፋት ጥረት እያደረጉ ነው ተብሏል።
የሩስያ ባለስልጣናት በቃጠሎው  52 የሚሆኑ አካባቢዎች በጭሱ የተሸፈኑ ሲሆን እስከ አሁን በጭሱ ላይ በተካሄደ ምርመራ ግን መርዛማነት እንደሌለው መረጋገጡን አስታውቀዋል። እሳቱን ለማጥፋት ከ130 በላይ የእሳት አደጋ መከላከያ አባላትና ወደ 2,000 የሚሆኑ የአካባቢው ነዋሪዎች እየተሳተፉ እንደሆነና ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ድረስ እሳቱ በቁጥጥር ሥር አለመዋሉን የጀርመን ዜና አገልግሎት (DPA) ዘግቧል።

የእስራኤል ማስጠንቀቂያ

እስራኤል ትላንት በጎላን ተራራ አካባቢ በምትገኘው ድሩዘ በተባለች ከተማ በእግር ኳስ ሜዳ ሲጫወቱ በነበሩ አዳጊ ሕጻናት ላይ ለደረሰው ጥቃት ቴህራንን ተጠያቂ አድርጋለች። በጥቃቱ ዕድሜያቸው ከ10 እስከ 16 የሚገመት 12  እስራኤላውያን ተገድለዋል። የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ በሰጠው መግለጫ ጉዳዩ  ቀጠናውን ወደ ሙሉ ጦርነት ሊያመራው ይችላል ሲል አስጠንቅቋል።
የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኦረን ማርሞርተን በዛሬው መግለጫቸው "ህጻናቶቻችንን የገደለው  ሚሳይል ኢራን ሰራሽ ነው" ብለዋል። ይህ ዓይነት መሳሪያ ያለው ደግሞ "አሸባሪ" ያሉት ሒዝቦላህ መሆኑን አክሏል። እስራኤል እራሷን የመከላከል መብትና ሃላፊነት እንዳላትና ለዚህ አሰቃቂ ግድያ አጸፋዊ ምላሽ እንደምትሰጥም ዝተዋል።
 ዓለም ኢራንና "ወኪሎቿ" ያሏቸውን ሒዝቦላህ፣ ሐማስና የየመን ሁቲ ዓማጽያን ለዚህ ቀጠናዊ ብጥብብጥ ሙሉ ሐላፊነት እንደሚወስዱ ማወቅ አለበትም ብለዋል። በቀጠናው ሙሉ ጦርነት እንዳይቀሰቀስ  ከተፈለገ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክርቤት በሒዝቦላህ ላይ ያስተላለፈው ውሳኔ 1701 መተግበር አለበት ብሏል ቃል አቀባዩ።
ውሳኔው ሒዝቦላህ በእስራኤልና ሊባኖስ ድንበር 30 ኪሎሜትር ርቆ ከሚገኘው የሊታኒ ወንዝ እንዲለቅ የሚያዝ እንደሆነ ይታወቃል ሲል የዘገበው የጀርመን ዜና አገልግሎት (DPA) ነው።
በሌላ ዜና  በሒዝቦላህ የተገደሉ ወጣቶችን ለመቅበር በነበረው ስነስርዓት በሺዎች የሚቆጠሩ እስራኤላውያን ጥቁር ልብስ በመልበስ መገኘታቸውንና በአካባቢው ያለው የጸጥታ ስጋት እንዳሳሰባቸው ገልጸዋል። አንድ በቀብሩ ስነስርዓት ለመገኘት የመጡ የ43 ዓመት ነርስ ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ "በዚህ አካባቢ ሲጫወቱ የነበሩ ሕጻናት ማጣታችን እጅግ አሳዝኖናል፤ በየቀኑ፣በየሌሊቱና በየደቂቃው ስጋት ውስጥ ነን" ሲሉ ተናግሯል። 
ይህ የተካረረው ውጥረትን ተከትሎ ፈረንሳይ ዜጎቿ ወደ ሊባኖስ፣እስራኤል አልያም ወደ ፍልስጤም ድንበር እንዳይጓዙ አስጠንቅቃለች።

ዩክሬይን አንድ ግዙፍ የሩስያ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ማጋየቷን 

ዩክሬይን አንድ ግዙፍ የሩስያ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ ማጋየቷን አስታወቀች። ሩስያ ውስጥ በኩርስክ ዞን በሚገኝ የነዳጅ ማከማቻ ዲፖ በደረሰ ጥቃት ከፍተኛ እሳት መፍጠሩን ታውቋል።
ፖልቫያ የተባለው የሩስያ የነዳጅ ማከማቻ የነደደው በዩክሬይን የጸጥታ ሃይሎች መሆኑን ክዬቭ አስታውቃለች። ይህ ከባድ ፍንዳታን የፈጠረ ጥቃት በምን አይነት መንገድ እንደተፈጸመ ግን ዩክሬይ የገለጸችው ነገር የለም። የዜናው ምንጭ ሮይተርስ የዜና ወኪል ነው።

የሩስያው ፕረዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የመካከለኛ ርቀት የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንደገና ማምረት እንደሚጀምሩ ዛቱ

የሩስያው ፕረዚደንት ቭላድሚር ፑቲን የመካከለኛ ርቀት የኑክሌር ጦር መሳሪያ እንደገና ማምረት እንደሚጀምሩ ዛቱ። ፕረዚደንቱ ይህን ያሉት ዛሬ የሐገሪቱን ባሕር ሐይል በፒተርስቡርግ ወታደራዊ ሰልፍ ከተመለከቱ በኋላ ነው።
ፕረዚደንት ፑቲን አክለውም  “አሜሪካ ወደ ጀርመን ወይም ሌላ የአውሮጳ ሐገር ሚሳይሎችን የምትልክ ከሆነ ከዚህ ቀደም የመካከለኛ ርቀት ኒኩለር ለማምረት ከሚያግደው ውል እራሳችንን ነጻ እናወጣለን” ማለታቸውን የዘገበው አዣንስ ፍራንስ ፕረስ ነው።
ዩናይትድ ስቴትስ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃልኪዳንን ለማጠናከር እንደጎርጎሮሳውያኑ አቆጣጠር በ2026 ረዥም ርቀት ተወንጫፊ ሚሳይሎችን ወደ ጀርመን እንደምታሰማራ በአለፈው ወር ማሳወቋ ይታወሳል።

ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።