1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ዲጂታል ዓለምዓለም አቀፍ

የማክሰኞ ሐምሌ 16 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ረቡዕ፣ ሐምሌ 17 2016

https://p.dw.com/p/4idtg

የማክሰኞ ሐምሌ 16 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

አርዕስተ ዜና

*በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ብርቱ ዝናም ባስከተለው የመሬት ናዳ የተነሳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 229 መድረሱ ተገለጠ ። በትናንቱ ናዳ ከአንገታቸው በታች ተቀብረው የነበሩ 7 ሰዎች በሕይወት መገኘታቸውም ተዘግቧል ። 

*በመላው ዓለም ከኤች አይቪ ተሐዋሲ ጋ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ባለፈው ዓመት 40 ሚሊዮን ይጠጋ እንደነበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አዲስ መረጃ ጠቆመ ። በኤድስ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቊጥር ከ20 ዓመት በፊት ከነበረው ጋ ሲነጻጸር ያለፈው ዓመት ቊጥሩ ከፍተኛ ለውጥ ማምሳየቱን ተመድ ዘግቧል ።

*የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሐሪስ  ለ2024ቱ የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ የዴሞክራቶች ፓርቲን ወክለው በፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ከፓርቲያቸው በቂ ድጋፍ አገኙ ። 

ዜናው በዝርዝር

​ጎፋ፥በጎፋ የመሬት ናዳ የሟቾቹ ቁጥር 229 ደረሰ፥ 7 ሰዎች በሕይወት ተገኝተዋል

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን ገዜ ጎፋ ወረዳ ብርቱ ዝናም ባስከተለው የመሬት ናዳ የተነሳ የሞቱ ሰዎች 229 መድረሱን የአካባቢው አስተዳደር ዐስታወቀ። በአደጋው 148 ወንዶች እና 81 ሴቶች መሞታቸውን የጎፋ ዞን የመንግሥት ኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ይፋ አድርጓል ። በናዳው ምክንያት ከአንገታቸው በታች ተቀብረው የነበሩ 7 ሰዎች በሕይወት መገኘታቸው ተዘግቧል ።  5 ወንዶችና 2 ሴቶች በሕይወት የተገኙት በሥፍራው እየተከናወነ ባለውን የነፍስ አድን ርብርብ መሆኑን የገዜ ጎፋ ወረዳ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ።  ሰዎቹ በእጅ ፣ በእግርና በወገባቸው ላይ ቀላልና ከባድ ጉዳት እንደደረሰባቸው አክለዋል ። አንድ የመንደሩ ነዋሪ ስለ አደጋው ቀጣዩን ብለዋል።  

«ናዳው በሁለት ሰዎች ላይ ነው መጀመሪያ ጉዳት ያደረሰው ። ያው እነሱን ለመፈለግ የመጡ ሰዎች ላይ ነው እንደገና ተጨማሪ ናዳ በሁለተኛ ዙር የመጣው ናዳ አጠቃላይ የብዙ ሰዎችን ሕይወት ቀጥፏል ።»

ተጎጂዎቹ በአካባቢው ጤና ጣቢያ የመጀመሪያ ርዳታ ከተደረገላቸው በኋላ ለተሻለ ህክምና ወደ ሳውላ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተገልጧል ። ትናንት በደረሰው አደጋ የአስክሬን ፍለጋና የነፍስ አድን ሥራው ተጠናክሮ መቀጠሉ ቢገለጥም የሟቾች ቊጥር ከፍ ሊል ይችላልም ተብሎ ነበር ።  እስከአሁን በተደረገ ቁፋሮ ከ229 በላይ አስክሬን መውጣቱ ተገልጧል ። 7 ሰዎች ከአንገት በታች በአፈር ተቀብረው መገኘታቸውን የዞኑ ባለሥልጣናት ገልጸዋል ሲልም ሸዋንግዛው ወጋየሁ ከሀዋሳ ዘግቧል።

ጄኔቫ፥ 2023 በመላው ዓለም ከኤች አይቪ ተሐዋሲ ጋ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር 40 ሚሊዮን ይጠጋል

በመላው ዓለም ከኤች አይቪ ተሐዋሲ ጋ የሚኖሩ ሰዎች ቁጥር ባለፈው ዓመት 40 ሚሊዮን ይጠጋ እንደነበር የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) አዲስ መረጃ ጠቆመ ። 9 ሚሊዮኑ አንዳችም የሕክምና ክትትል አያገኙም ተብሏል ።  በኤድስ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቊጥር ግን ከ20 ዓመት በፊት ከነበረው ጋ ሲነጻጸር ያለፈው ዓመት ቊጥሩ ከፍተኛ ለውጥ ማምሳየቱን ተመድ ዘግቧል ። ከ20 ዓመት በፊት ከኤድስ ጋ በተያያዘ የሞቱ ሰዎች ቊጥር 2,1 ሚሊዮን ነበር ተብሏል በዘገባው ። እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2023 ደግሞ ከኤድስ ጋ በተያያዙ ሕመሞች ምክንያት 630,000 ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጧል ። የተሻሉ መድኃኒቶች ሥርጭት እና ሕክምና ለሟቾች ቊጥር መቀነስ ምክንያት መሆኑን የተመድ ኤድስ መቆጣጠሪያ ጽ/ቤት ኃላፊ (UNAIDS)ሴዛር ኑኔዝ ተናግረዋል ።

«በሕክምናው ዘርፍ ከፍተኛ እመርታ መታየቱ ብሎም አዲስ በኤች አይቬ ተሐዋሲ የሚጠቁ ሰዎች ቊጥር መቀነሱ በእርግጥም የሚሞቱ ሰዎች ቊጥር እንዲቀንስ አድርጓል ። »

በየዓመቱ በኤድስ ምክንያት የሚሞቱ ሰዎችን ቊጥር ለመቀነስ ያለመው ተመድ ዘንድሮ በኤድስ የሚሞቱ ሰዎችን ቊጥር ወደ 250,000 ለማውረድ አቅዶ እየሠራ መሆኑን ጠቅሷል ። ትናንት ይፋ የሆነው የተመድ መረጃ እንደሚጠቁመው ከሆነ ደግሞ በመላው ዓለም በየደቂቃው ከኤድስ ሕመም ጋ በተያያዘ አንድ ሰው ይሞታል ።

ካምፓላ፥ኡጋንዳ ውስጥ ጸረ ሙስና ተቃውሞ ለማካሄድ አደባባይ የወጡ በርካታ ሰዎች በቊጥጥር ስር ዋሉ

የዩጋንዳ የፀጥታ ኃይላት ዋና ከተማዪቱ ካምፓላ ውስጥ ጸረ ሙስና ተቃውሞ ለማካሄድ አደባባይ የወጡ በርካታ ሰዎችን በቊጥጥር ስር አዋሉ ። የተቃውሞ ሰልፉ አደራጆችም መታሰራቸውን የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት (AFP)ዘግቧል ። የተቃውሞ ሰልፈኞቹ ወደ ሀገሪቱ ምክር ቤት በማቅናት ሰልፍ ለማድረግ መሞከራቸው ሕገወጥ ነው ሲሉ ባለሥልጣናት ተናግረዋል ። ቊጥራቸው አነስተኛ ሰልፈኞች በሚገኙባቸው የካምፓላ የተለያዩ መንደሮች ከፍተኛ ቊጥር ያላቸው ፖሊሶች እና የጦር ሠራዊት አባላት መሠማራታቸውም ተዘግቧል ።  የዩጋንዳ ፖሊስ ቃል አቀባይ ኪቱማ ሩሶክ፦ «የሀገሪቱን ሰላም እና ደሕንነት አደጋ ላይ የሚጥል ሰልፍ ማካሄድ አይፈቀድም» ብለዋል ።  የዩጋንዳ የተቃውሞ ሰልፈኞች አደባባይ የወጡት በጎረቤት ኬንያ የተቃውሞ ሰልፈኞች ተነሳስተው መሆኑም ተዘግቧል ። አዲስ ግብር ለመጣል አቅዶ ድንገት በደጋጋሚ ብርቱ ተቃውሞ የተናጠው የኬንያ መንግሥት ካቢኔቱን እስከመበተን መድረሱም ለዩጋንዳ የተቃው ሰልፈ አደራጆች እንደ አብነት መታየቱን የፈረንሣይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል ።  ላለፉት 38 ዓመታት ዩጋንዳን በፈላጭ ቆራጭነት የመሩት ፕሬዚደንት ዩዌሪ ሙሴቪኒ በቴሌቪዥን ባስተላለፉት መልእክት የተቃውሞ ሰልፈኞችን፦ «በእሳት እየተጫወቱ ነበር» ሲሉ  አስጠንቅቀዋል ። 

ዋሽንግተን፥ካማላ ሐሪስ የዴሞክራቶቹ ፓርቲ እጩ ፕሬዚደንት ተወዳዳሪ ሆነው ተመረጡ

የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዝዳንት ካማላ ሐሪስ  ለ2024ቱ የዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ የዴሞክራቶች ፓርቲን ወክለው በፕሬዝዳንትነት ለመወዳደር ከፓርቲያቸው በቂ ድጋፍ አገኙ ።  የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ከዩናይትድ ስቴትስ ምርጫ ራሳቸውን ማግለላቸውን ካሳወቁ በኋላ ምክትላቸው የፓርቲያቸው እጩ ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ትናንት  ማረጋገጫ ሰጥተዋል ። ካማላ ሐሪስ ከፓርቲያቸው ከ2500 በላይ ተወካዮች ከወዲሁ ድጋፍ እንደሚሰጧቸው ማቀዳቸው ተዘግቧል ።  ምክትል ፕሬዚደንት ካማላ ሐሪስ ፓርቲያቸውንም ሆነ ሀገራቸውን በጋራ ለማስተባበር መቁረጣቸውን ዐሳውቀዋል ።  

«ይህን የእጩነት ጥሪ ወጥቶ መቀበል እና ማሸነፍ ፍላጎቴ ነው ስለዚህ በሚቀጥሉት ቀናት እና ሳምንታት ከእናንተ በመሆን የዴሞክራቲክ ፓርቲያችን ብሎም ሀገራችን በአንድ ለማስተሳሰር ባለኝ ሥልጣኔ ሁሉንም ነገር አደርጋለሁ »

ከፓርቲያቸው ተወካዮች እጅግ ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚያገኙ ከወዲሁ ቃል የተገባላቸው ካማላ ሐሪስ የዴሞክራቶች ፓርቲ እጩ ፕሬዚደንትነታቸው የሚረጋገጠው ግን ዴሞክራቶቹ በነሐሴ ወር መጨረሻ በሚያደርጉት «የፓርቲ ቀን ጉባኤ»  ነው ። የዴሞክራቶች ፕሬዚደንት እጩ ለመሆን በፓርቲው ጉባኤ  1,976 ድምፅ ማግኘት ያስፈልጋል ።

ቤርሊን፥ጆ ባይደን ካማላ ሐሪስ እጩ እንዲሆኑ ቦታ መልቀቃቸውን የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አወደሱ

ይህ በእንዲህ እንዳለ፦ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን እጩ ተወዳዳሪነት ቦታውን ለምክትል ፕሬዚደንት ካማላ  ሐሪስ መልቀቃቸውን የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚንሥትር አወደሱ ። ምርጫው ለዩናትድ ስቴትስ ብቻ ሳይሆን ለአውሮጳም አንዳች ነገር ይዞ እንደሚመጣ መጠበቃቸውን ውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ አናሌና ባዬርቦክ ተናግረዋል ። ብዙዉን ጊዜ «ምርጫ የሚወሰነው በመጨረሻዎቹ ቅጽበቶች ብቻ ነው»ም ብለዋል ። ካማላ  ሐሪስ  በፓርቲያቸው ጉባኤ በቂ የተወካዮች ድጋፍ ድምፅ ከተሰጣቸው የሪፐብሊካን እጩ ሆነው ከቀረቡት የቀድሞው ፕሬዚደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋ ተፎካካሪ ይሆናሉ ።   የ59 ዓመቷ ካማላ ሐሪስ በጎርጎሮሳዊው ኅዳር 5 ቀን፣ 2024 ዓ.ም ለሚካሄደው ምርጫ በፕሬዚደንት ጆ ባይደን ምትክ የዴሞክራቶች እጩ ተወዳዳሪ እንደሚሆኑ ከወዲሁ በሰፊው ተገምቷል ።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።