1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐሙስ ሰኔ 13 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ሐሙስ፣ ሰኔ 13 2016

https://p.dw.com/p/4hKJ4

*የኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን መብት ለማስከበር ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያረጋግጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)ጠየቀ።

*በዘንድሮው የመካው የሀጅ ጉዞ ወቅት በተከሰተው ኃይለኛ ሙቀት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከአንዲ ሺህ መብለጡን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገበ። ዛሬ በወጣው አዲስ መረጃ ተጨማሪ 58 ከግብጽ የመጡ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።  ሕይወታቸው ካለፈው 658 ግብጻውያን ተጓዦች መካከል 630ው ያልተመዘገቡ ናቸው ሲል አንድ ዲፕሎማትን ጠቅሶ ዜና አገልግሎቱ ዘግቧል።

*የሶማሊያ መንግስት የአፍሪቃ ኅብረት ሠራዊት ከሶማሊያ ወደየ ሀገሩ የሚመለስበት ጊዜ እንዲዘገይ የሚፈልግ መሆኑን ዐሳወቀ። የኢትዮጵያ ሠራዊት ግን ቶሎ እንዲወጣ ይሻል። ሶማሊያ ከሠፈሩት 18 ሺሕ የአፍሪቃ ሐገራት ወታደሮች 5 ሺሕዉ ካለፈዉ የግሪጎሪያኑ 2023 ጀምሮ ወጥተዋል።

ዜናው በዝርዝር

አ.አ፥ የኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን መብት እንዲስከብር ኢሰመኮ ጠየቀ

የኢትዮጵያ መንግስት የስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎችን መብት ለማስከበር ያለውን ቁርጠኝነት እንዲያረጋግጥ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን (ኢሰመኮ)ጠየቀ። ኢሰመኮ ጥያቄውን ያቀረበው  በየዓመቱ ሰኔ 20 የሚከበረውን የአለም የስደተኞች ቀን ምክንያት በማድረግ ነው ። ስደተኞች ከጥገኝነት፣ ከደህንነት እና  ከሰነዶች ጋር ከተያያዙ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ አሁንም ፈተናዎች እንደሚገጥማቸው ኢሰመኮ ገልጧል ።  የዘፈቀደ እሥራት ሁኔታዎች፣ ፍትሕ እና መሰረታዊ ፍላጎቶችን የማግኘት መብት ፣ የሰብአዊ ርዳታ፣ ዘላቂ መፍትሔዎች እና መልሶ ማቋቋምን የተመለከቱ ጉዳዮች ስደተኞች ለችግር ከሚጋለጡባቸው  መካከል መሆናቸውንም ጠቅሷል። የኢሰመኮ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ይህንኑ ዛሬ የሚከበረውን የስደተኞችን ቀን በማስመልከት ለመንግሥት ጥሪ ማስተላለፋቸውን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ።

«በእኛ  ሀገር ያለው የጥበቃቸው፤ የሰብአዊ መብቶቻቸውን በተለይ ደግሞ ደህንነት እና ሴኪዩሪቲን በተመለከተ ያሉ ክፍተቶችን በመሸፈን ስደተኞች ምቹ አካባቢን፣ ተቀባይ ሀገር ማመቻቸት በሚለው መንግስትም እስከ ዛሬ ድረስ የሠራቸውን ሥራዎች ዕውቅና በመስጠት አስፈላጊውን ግን የትብብር ሥራዎች፤ ድጋፉንም፤ ጥበቃውንም አጠናክሮ የተሻለ ሁኔታ እንዲፈጥር።»

ኢትዮጵያ በዋናነት ጋምቤላ ውስጥ የተጠለሉ የደቡብ ሱዳን፣ የሶማሊያ፣ የየመን፣ በአዲስ አበባ በብዛት የሚኖሩ የኤርትራ እንዲሁም ጎንደር ውስጥ የሱዳን ዜጎች የሆኑ ስደተኞችን ተቀብላ ታኖራለች። አብዛኞቹ ስደተኞች በስደተኞች ካምፖች ውስጥ የሚኖሩ ሲሆን በተወሰነ ቁጥርም ቢሆን በከተማ አካባቢ መጠጊያ አግኝተው የሚኖሩ መኖራቸውን ኢሰመኮ ገልጧል።

ሪያድ፥በመካው ሙቀት የሞቱት ምዕመናን ቁጥር ከአንድ ሺህ በለጠ 

በዘንድሮው የመካው የሀጅ ጉዞ ወቅት በተከሰተው ኃይለኛ ሙቀት የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከአንዲ ሺህ መብለጡን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘገበ። እንደ ዘገባው ከሟቾቹ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ሳዑዲ አረብያን በመታው ኃይለኛው ሙቀት ሃይማኖታዊውን ጉዞ ያደረጉ ያልተመዘገቡ ምዕመናን ናቸው። ዛሬ በወጣው አዲስ መረጃ ተጨማሪ 58 ከግብጽ የመጡ ሰዎች መሞታቸው ታውቋል።  ሕይወታቸው ካለፈው 658 ግብጻውያን ተጓዦች መካከል 630ው ያልተመዘገቡ ናቸው ሲል አንድ ዲፕሎማትን ጠቅሶ ዜና አገልግሎቱ ዘግቧል። በእስልምና እምነት አቅሙ ያላቸው ምዕመናን በሕይወት ዘመናቸው ቢያንስ አንዴ ሊደርጉት ይገባል በሚባለው ዓመታዊው ሃጅ ወደ ዐሥር የሚሆኑ ሀገራት ዘንድሮ አንድ ሺህ ሰማንያ አንድ ሰዎች መሞታቸውን ዐሳውቀዋል። የሳዑዲ አረብያ የሜትሮሎጂ አገልግሎት፣ በታላቁ የመካው መስጊድ 51.8 ዲግሪ ሴንቲግሬድ የሙቀት መጠን በዚህ ሳምንት መመዝገቡን አሳውቋል። የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደተናገረው መካ የሚገኘው የግብጽ ቆንስላ  ቡድን የጠፉ ሰዎችንና የአስከሬኖች ፍለጋ በከተማይቱ ሆስፒታሎች እያካሄደ ነው። በየዓመቱ ለሀጅ የሚያስፈልገውን ወጪ መሸፈን የማይችሉ በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን ሕገ ወጥ በሚባሉ መንገዶች በጉዞው ለመካፈል ሙከራ እንደሚያደርጉም ተዘግቧል።እነዚህ ያለ ፈቃድ ገቡ የሚባሉት ምዕመናን ለአደጋው የተዳረጉት፣ የሳዑዲ ባለሥልጣናት ቁጥራቸው 1.8 ሚሊዮን ለሚሆነው ሕጋዊ ተጓዦች በሚያዘጋጇቸው የሙቀት ማቀዝቀዣ ባለባቸው ስፍራዎች መግባት ስለማይፈቀድላቸው መሆኑም ተገልጿል። 

ሞቃዲሾ-የሶማሊያ መንግስት የአፍሪቃ ኅብረት ሰላም አሰከባሪ መውጣት እንዲዘገይ ይፈልጋል

የሶማሊያ መንግስት የአፍሪቃ ኅብረት ሠራዊት ከሶማሊያ ወደየ ሀገሩ የሚመለስበት ጊዜ እንዲዘገይ የሚፈልግ መሆኑን ዐሳወቀ። የኢትዮጵያ ሠራዊት ግን ቶሎ እንዲወጣ ይሻል። የአፍሪቃ ሕብረት የሽግግር ተልዕኮ (ATMIS)በሶማሊያ እስከመጪዉ ታኅሣሥ ማብቂያ ድረስ ከሶማሊያ ጠቅልሎ እንዲወጣ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ወስኗል። ይሁንና ሮይተርስ ዜና አገልግሎት የሶማሊያ መንግስት ለአፍሪቃ ኅብረት የፃፈዉን ደብዳቤ ጠቅሶ ዛሬ እንዘገበዉ ሠራዊቱ በተያዘዉ ጊዜ ከሶማሊያ ለቅቆ ከወጣ የፀጥታ «ክፍተት» ሊፈጠር በዉጤቱም አልሸባብ አንሰራርቶ ሥልታዊ ቦታዎችን ሊቆጣጠር ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሯል። በተለይ እስከ መጪዉ መስከረም ድረስ ከሶማሊያ ይወጣል ተብሎ የታቀደዉ 4ሺሕ ሠራዊት የሚወጣበት ጊዜ እንዲራዘም የሶማሊያ መንግስት ጠይቋል። ይሁንና ኢትዮጵያ ከሶማሊላንድ ጋር የወደብ ኮንትራትን የሚመለከት የመግባቢያ ስምምነት መፈራረሟን አጥብቀዉ የሚቃወሙት የሶማሊያ ባለስልጣናት የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሶማሊያ ባስቸኳይ እንዲወጡ እየገፋፉ ነዉ። ሶማሊያ ከሠፈሩት 18 ሺሕ የአፍሪቃ ሐገራት ወታደሮች 5 ሺሕዉ ካለፈዉ የግሪጎሪያኑ 2023 ጀምሮ ወጥተዋል።

ሮም-ሕንዳዊዉ ሠራተኛ አሰቃቂ ሞት

ኢጣሊያ ዉስጥ በአንድ የእርሻ ማሳ ዉስጥ ተቀጥሮ ይሠራ የነበረ ሕንዳዊ ወጣት በአሰቃቂ ሁኔታ መሞቱ ከፍተኛ ቁጣና ተቃዉሞ ቀስቅሷል። የቀን ሠራተኛዉ ሳትናም ሲንግሕ፣ ቦርጎ ሳንታ ማሪያ በተባለ ከሮም በስተደቡብ በሚገኝ አንድ ማሳ ውስጥ ሰብል ሲሰበስብ አሰቃቂ አደጋ ደርሶበታል ። የ31 ዓመቱ ሕንዳዊ የሚሠራበት ማሺን ጠልፎ ከጣለው በኋላ  ሁለት እግሮቹ ተሠብረው  እጁም  ተቆርጦ ሲወድቅ ይታያል ። መርማሪዎች እንዳሉት የሲንግሕ ቀጣሪዎች አደጋ የደረሰበትን ሠራተኛቸዉን ሐኪም ቤት አልወሰዱትም። የቁስለኛዉን ጩኸት የሰሙ ጎረቤቶች ለአደጋ ሠራተኞች ደዉለዉ ከአንድ ሰዓት በኋላ ቁስለኛዉ ሆስፒታል ደርሶ ነበር። ይሁንና ደሙ ፈስሶ በማለቁ ሐኪሞች ሊያድኑት አልቻሉም። ትናንት ሕይወቱ ማለፉ ቁጣን ቀስቅሷል ። እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ከ2021 ጀምሮ ኢጣሊያ ዉስጥ ይኖሩ የነበሩት ሲንግሕ እና ባለቤቱ ሕጋዊ ወረቀት አልነበራቸዉም። ዘገቦች እንደጠቆሙት ኢጣሊያ ዉስጥ 230,000 ያክል ሕጋዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸዉ የዉጪ ዜጎች እስከ 40 ዲግሪ ሴልስየስ በሚደርስ ሙቀት በእርሻ ማሳ ዉስጥ በርካሽ ክፍያ ይሠራሉ።

ፍራንክፉርት፥ የአዉሮጳ የእግር ኳስ ግጥሚያ

በአውሮጳ እግር ኳስ ግጥሚያ የምድብ ግጥሚኢዎች ቀጥለው ዛሬም እየተከናወኑ ነው ። ከምድብ «ሐ» ሦስት ነጥብ ይዛ አንደኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው እንግሊዝ እና ዴንማርክ ፍራንክፉርት ከተማ በሚገኘው የዶይቸ ባንክ ፓርክ ስታዲየም ውስጥ እየተጫወቱ ነው ። ዴንማርክ እንደ ሠርቢያ አንድ ነጥብ ይዛ በግብ ክፍያ ልዩነት ከምድቡ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ሰፍራለች ። በኢትዮጵያ ሰአት አቆጣጠር ከምሽቱ አራት ሰአት ሲል የምድብ «ለ» ብርቱ ተፎካካሪዎች ስፔን እና ጣሊያን ሁለተኛ ጨዋታቸውን ያከናውናሉ ። ሁለቱም ከምድባቸው ተጋጣሚዎቻቸውን አሸንፈው ሦስት ሦስት ነጥብ ይዘዋል ።  በዚሁ ምድብ የሚገኙት አልባኒያ እና ክሮሺያ ትናንት ባዳረጉት ልብ ሰቃይ ሁለተኛ ግጥሚያቸው ሁለት እኩል ተለያይተዋል ። በተለይ ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ክሮሺያዎችን የአልባኒያ ተጨዋቾች ለማሸነፍ ማስጨነቃቸው ጨዋታውን ይበልጥ አጓጊ አድርጎት ነበር ። ትናንት በነበሩ ግጥሚያዎች አዘጋጇ ጀርመን ሐንጋሪን 2 ለ0 አሸንፋ ከምድብ «ሀ» ወደ ቀጣይ ዙር ማለፏን ከወዲሁ አረጋግጣለች ። በሁለት ጨዋታዎች ስድስት ነጥብ ሰብስባለች ። ስዊትዘርላንድ በአራት ነጥብ ትከተላለች ። ትናንት ከስዊትዘርላንድ ጋ ተጋጥማ አንድ እኩል የተለያየችው  ስኮትላንድ በአንድ፤ እንዲሁም ሐንጋሪ ያለምንም ነጥብ ሦስተኛ እና አራተኛ ደረጃ ይዘዋል ። ዛሬ በነበረ ግጥሚያ ስሎቬኒያ በአውሮጳ እግር ኳስ ውድድር የመጀመሪያዋ ሊሆን የሚችለው ድሏን በባከነ ሰአት በሠርቢያ ተነጥቃለች ። በዛሬው የምድብ «ሐ» ግጥሚያ ስሎቬኒያ እና ሠርቢያ አንድ እኩል ተለያይተዋል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሠ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።