1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐሙስ መስከረም 9 ቀን፣ 2017 ዓ.ም የዓለም ዜና

ሐሙስ፣ መስከረም 9 2017

https://p.dw.com/p/4kriZ

አርዕስተ ዜና

*ባለፈው ማክሰኞ የተኩስ ድምፅ ሲያጓራባት የቆየችው የጎንደር ከተማ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ በአብዛኛው ወደነበረበት መመለሱን ነዋሪዎች ተናገሩ ። በትንሹ 5 ሰዎች መገደላቸውንም አክለዋል  ።

*የኢትዮጵያና ሶማሊያ ባለሥልጣናትን ቱርክ ዳግም ግን በተናጥል ለማነጋገር ማቀዷን ይፋ አደረገች ። ለማክሰኞ ታቅዶ የነበረው ሦስተኛው ዙር ንግግር መሰረዙ ተገልጧል ።

*የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሽኝት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ተፈፀመ ። ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሚሊኒየም አዳራሽ ሽኝት ተደርጎላቸዋል ።

*የጦጣ ፈንጣጣ ክትባት በአፍሪቃ ለመጀመሪያ ጊዜ መሰጠቱ ተገለጠ ። ርዋንዳ ውስጥ ክትባቱ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች መሰጠቱን የአፍሪቃ ኅብረት የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል (CDC)ዛሬ (ሐሙስ) ይፋ አድርጓል ።

ዜናው በዝርዝር

​ጎንደር፥ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ በአብዛኛው ወደነበረበት እየተመለሰ ነው

ባለፈው ማክሰኞ የተኩስ ድምፅ ሲያጓራባት የቆየችው የጎንደር ከተማ ማኅበራዊ እንቅስቃሴ በአብዛኛው ወደነበረበት መመለሱን ነዋሪዎች ተናገሩ ። ባለፈው ሰኞ ከሰዓት በኋላና ማክሰኞ እለት  በጎንደር ከተማ የተለያዩ አካባቢዎች በፋኖ ታጣቂዎችና በመከላከያ ሠራዊት መካከል ጦርነቶች ሲካሄዱ እንደነበር ተዘግቧል ። በወቅቱ በነበረው ተኩስ በንብረትና በሕይወት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጧል ። ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየት በትንሹ 5 ሰላማዊ ሰዎች ተገድለዋል ። መረጋጋት ተስኗት የቆየችው ጎንደር ከተማ ከዛሬ ጠዋት ጀምሮ ግን አብዛኛዎቹ የከተማዋ ክፍሎች ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ወደነበሩበት መመለሳቸውን አንድ የከተማዋ ነዋሪ ለዶይቼ ቬለ በስልክ ተናግረዋል ።

«እየሠራን ነው ያለነው ። ሁሉም ነገር ክፍት ነው ። ምንም ዝግ የለም ። ታክሲ፤ ባጃጅ፤ መጠጥ ቤት፤ ሱቅ ምናምን ሁሉም ምንም ነገር የለም ። ይኸው እኔ ባንክ ላይ ነው ያለሁት ። ሦስት ባንክ አለ እጥጌ ። ኧረ ምንም ነገር ዝግ የለም ። »

ሌላ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ከሰዓት በኋላ አብዛኛዎቹ የከተማዋ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ጠቁመዋል ። ሆኖም ጦርነቱ በነበረበት ቀበሌ 18 በተባለው አካባቢ ብዙም እንቅስቃሴ እንደሌለ አመልክተዋል ።

«ከሰአት በኋላ ያው ሁሉም ቦታ እንቅስቃሴው ጀምሯል ሁሉም ቦታ ። አሁን ምንም ነገር የለም ። ያው በ18 ነው ፤ 18 ያው እንደተዘጋጋ ው ። ሌላው ሁሉም ሥራውን ጀምሯል ። መኪናም እንቅስቃሴ ጀምሯል ። አሁን ደህና ነው፤ ተረገግቷል ።»

የመንገድ ዳር ግብይይቶችም ወደ መደበኛ ሥራቸው እየተመለሱ እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎቹ ዛሬ ከሰዓት በኋላ ገልጠዋል ። የጎንደር ከተማ አስተዳደር የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ አበበ ላቀው ትናንትና በሁሉም የከተማዋ አካባቢዎች ሰላማዊ እንቅስቃሴዎች መጀመራቸውን ገልጠው ነበር ። ዜናውን የላከልን ዓለምነው መኮንን ነው ።

አንካራ፥ ቱርክ የኢትዮጵያና የሶማሊያ ባለሥልጣናትን በተናጥል ልታነጋግር ነዉ

የኢትዮጵያና ሶማሊያ ባለሥልጣናትን ቱርክ ዳግም ግን በተናጥል ለማነጋገር ማቀዷን ይፋ አደረገች ። ቱርክ የተናጠል ንግግሩን የምታደርገው አንካራ ውስጥ አዲስ ዙር ንግግር ከመጀመሩ በፊት መሆኑን የሀገሪቱ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ማሳወቁን የዜና ምንጮች ዘግበዋል ። የሁለቱ ሃገራት ፍጥጫን በድርድር ለማስወገድ የምትጥረዉ ቱርክ ባይሳኩም ከዚህ ቀደም ለሁለት ጊዜያት በስማበለዉ (በተዘዋዋሪ)የሁለቱ ሃገራት ባለሥልጣናትን አነጋግራለች ። ለማክሰኞ ታቅዶ የነበረው ሦስተኛው ዙር ንግግር ገቢራዊ ያልሆነው ሁለቱ ሃገራትን በተናጠል ማነጋገሩ ስለሚሻል መሆኑን የቱርክ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሐካን ፊዳን ተናግረዋል ። ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ የመንግሥትነት ዕዉቅና ከሌላት ሶማሊላንድ ጋር ወደብ ለመኮናተር የመግባቢያ ስምምነት በፈራረሟ የአዲስ አበባና የሞቃዲሾ ጠብ ተካርሯል ። ግብፅ ለሶማሊያ ጦር መሳሪያ ማስታጠቅ መጀመሯና ሶማሊያ ዉስጥ ወታደር ለማስፈር ማቀዷ ደግሞ አዲስ ግጭት ሊያስከትል ይችላል የሚል ሥጋት አሳድሯል ።

አ.አ፥ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ተቀበሩ

የፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የሽኝት እና የቀብር ሥነ ሥርዓት ዛሬ ተፈፀመ ። አንጋፋው ምሑር እና ፖለቲከኛ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ለሕክምና በሄዱበት ኬንያ ነበር መስከረም 7 ቀን፣ 2017 ዓ.ም ማረፋቸው የተነገረው ። ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ዛሬ አዲስ አበባ ውስጥ በሚሊኒየም አዳራሽ ሽኝት ተደርጎላቸዋል። በዚሁ ሥነ ሥርዓት ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት፣ ቤተሰቦቻቸው እና ወዳጆቻቸው ተገኝተዋል። በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር ሆነው የሚያገለግሉት ፕሮፌሰር ተከተል ዮሐንስ ከፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ ጋር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለረጅም ጊዜ በጋራ ሠርተዋል ።

«የእሳቸው ተማሪዎች በተለያዩ ተቋማት መሪ ሆነው ያሉ ፕሮፌሰር ደረጃ የደረሱ፤ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፤ በምርምር ተቋማት የሚያገለግሎ እጅግ ከፍተኛ ቁጥታ ያላቸውን ምሑራን ያፈሩ ጀግና አባት ነበሩ ። ጀግና ምሑር ነበሩ ብል የሚያንስባቸው አይደለም ።»

ከ1983 ዓ. ም ጀምሮ የፖለቲካ ፓርቲ ተሳትፎ ውስጥ የቆዩት ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ የኢትዮጵያ ሶሻል ዴሞክራቲክ ፓርቲ (ኢሶዴፓ) ሊቀ መንበር ነበሩ። በመንግሥት መዋቅር ውስጥም የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር በመሆን እስከ ኅልፈታቸው ድረስ ሲሠሩ ቆይተዋል። ሥርዓተ ቀብራቸውም በጴጥሮስ ወጳውሎስ መካነ መቃብር ከቀትር በኋላ ተፈጽሟል ። ዜናውን ከአዲስ አበባ የላከልን ሰለሞን ሙጬ ነው ።

ኪጋሊ፥ የጦጣ ፈንጣጣ ክትባት ለመጀመሪያ ጊዜ አፍሪቃ ውስጥ ተሰጠ

የጦጣ ፈንጣጣ ክትባት በአፍሪቃ ለመጀመሪያ ጊዜ መሰጠቱ ተገለጠ ። ርዋንዳ ውስጥ ክትባቱ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ከፍተኛ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች መሰጠቱን የአፍሪቃ ኅብረት የበሽታ መቆጣጠሪያ ማዕከል (CDC)ዛሬ (ሐሙስ) ይፋ አድርጓል ። የመጀመሪያው ዙር ክትባት ለ300 ሰዎች ማክሰኞ እለት ከኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ጋር በሚያዋስነው ድንበር አካባቢ መሰጠቱን የማዕከሉ የአፍሪካቃ ቃል አቀባይ ለፈረረንሳይ ዜና አገልግሎት ተናግረዋል ።  የጦጣ ፈንጣጣ ወረርሽኝ አሁንም ድረስ አፍሪካ ውስጥ በቁጥጥር ስር አለመዋሉን ማዕከሉ አሳስቧል ። በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ወደ 3,000 የሚጠጉ በበሽታው የተጠረጠሩ ሰዎች ተመዝግበው 374ቱ ላይ በሽታው መኖሩ ተረጋግጧል ሲል ማእከሉ ዐሳውቋል ። ከጦጣ ፈንጣጣ በሽታ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ 14 ሰዎች መሞታቸውንም ገልጿል። ከጥር ወር አንስቶ ባሉት ወራቶች በ15 ሃገራት ከ29,000 በላይ የጦጣ ፈንጣጣ ምልክት የታየባቸው ሰዎች መመዝገባቸው ተጠቅሷል ።  738 ሰዎች በበሽታው ሞተዋል ።

ሊባኖስ፥ የፔጀርና ዎኪ ቶኪ ዎች ሁለተኛ ዙር ጅምላ ፍንዳታ

ሊባኖስ ውስጥ የተለያዩ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛዎች ላይ በቀጠለው የጅምላ ፍንዳታ እስካሁን ከ3,000 በላይ ሰዎች መቁሰላቸው ተዘገበ ።  ቢያንስ 40 ሰዎች ደግሞ በፍንዳታው ተገድለዋል ተብሏል ። ትናንት በነበረው ሁለተኛ ዙር ፍንዳታው 25 ሰዎች ሲገደሉ ቢያንስ 20ዎቹ የሊባኖሱ የሒዝቦላ ታጣቂ ቡድን አባላት መሆናቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት (AFP)ዘግቧል ። በፍንዳታው በርካታ ሰላማዊ ሰዎችም መገደላቸው እና መቁሰላቸው ተገልጧል ። ማክሰኞ ዕለት በተለያዩ የሊባኖስ ግዛቶች ውስጥ በመቶዎች የሚቆጠሩ ፍንዳታዎች በተመሳሳይ በሚባል ሰአት ተከስተው ነበር ። በያኔው ፍንዳታ ቢያንስ 12 ሰዎች ሲገደሉ፤ ወደ 2,800 ሰዎች ደግሞ ቆስለው ነበር ። የፔጀርና ዎኪ ቶኪ ዎች ጅምላ ፍንዳታው መላ ሊባኖስን ያስደነገጠ መሆኑ ተነግሯል ። አንዳንዶች ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልኮቻቸውን የመያዝ ሥጋት እንዳደረባቸው ገልጠዋል ። ሒዝቦላህ ለፍንዳታው እሥራኤልን ተጠያቂ በማድረግ ለበቀል ዝቷል ። ሒዝቦላህ በዩናይትድ ስቴትስ፤ ጀርመን እና በርካታ የሱኒ ዐረብ ሃገራት አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀ፤  በኢራን የሚደገፍ የሊባኖስ የሺዓ ፖለቲካ ፓርቲ  እና ወታደራዊ ክንፍ ነው ። የእሥራኤል መከላከያ ሚንስትር ጆአቭ ጋላንት ዘመቻው ወደ ሰሜን መቀየሩን በመጥቀስ «አዲስ ምእርፍ» መከፈቱን አውጀዋል ። የመከላከያ ሚንስትሩ ንግግር በታጣቂዎቹ ላይ ሙሉ ጦርነት ሊካሄድ ይችላል የሚል ስጋት አጭሯል ።  

ቤሩት፥ እሥራኤል ሊባኖስ ላይ፤ ሒዝቦላህ እሥራኤል ላይ ጥቃት አደረስን አሉ

ሒዝቦላህ በበኩሉ ጋዛ ውስጥ ያሉ ፍልሥጥኤማውያን ለመደገፍ በሚል ሰሜናዊ እሥራኤል የሚገኝ ወታደራዊ ይዞታ መምታቱን ዐሳውቋል ። ዛሬ ማለዳ በደረሰው ጥቃት ሰዎች መቁሰላቸውን የእሥራኤል መገናኛ አውታሮች ዘግበዋል ።  ከባለሥልጣናት በኩል ግን ማረጋገጫ አልተሰጠም ። ሐማስ ተመሳሳይ «ብርቱ የበቀል ጥቃቶችን» እንደሚሰነዝር ዝቷል ። እሥራኤል በበኩሏ እኩለ ሌሊት ላይ በደቡባዊ ሊባኖስ በርካታ ወታደራዊ ይዞታዎችን ከኢየር መደብደቧን ዛሬ ይፋ አድርጋለች ።

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።