1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሐሙስ ሐምሌ 4 ቀን፣ 2016 ዓ.ም የዓለም ዜና

ሐሙስ፣ ሐምሌ 4 2016

https://p.dw.com/p/4iBra

አርዕስተ ዜና

*ባለፈው ሳምንት ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ አካባቢ በታጣቂዎች ከታገቱት 167 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች 160ዎቹ መለቀቃቸውን የመንግሥት ባለሥልጣናት ቢናገሩም ቤተሰቦች ግን እስካሁን ልጆቹ እንዳልተለቀቁ ዐሳወቁ ።

*በጋምቤላ ክልል ከአንድ ወር በፊት 7 ኑዌሮች መናኸሪያ አካባቢ መገደላቸው ከተገለጠ በኋላ ወደ ኑዌር ዞን የሚደረግ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎት እስካሁን መቋረጡ ተገለጠ ። በአካባቢው ነዋሪዎች ደህንነት ላይ ሥጋት በመከሰቱ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎቱ ከተቋረጠ አንድ ወር ማለፉን ነዋሪዎች ተናግረዋል ።

*ለሳምንታት በሕዝብ ተቃውሞ ስትናጥ የከረመችው ኬንያ ፕሬዚደንት የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውን በተኑ። ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ በዛሬው ዕለት የወሰዱት ርምጃ በመላው ሀገሪቱ ለተነሳው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ እንደምላሽ ነው የታየው።

ዜናው በዝርዝር

ገርበ ጉራቻ፥ኦሮሚያ ክልል በታጣቂዎች ከታገቱ 167 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተለቀቁ የተባሉት አለመለቀቃቸውን ቤተሰቦች ተናገሩ

ባለፈው ሳምንት ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ገርበ ጉራቻ አካባቢ በታጣቂዎች ከታገቱት 167 የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች 160ዎቹ መለቀቃቸውን የመንግሥት ባለሥልጣናት ቢናገሩም ቤተሰቦች ግን እስካሁን ልጆቹ እንዳልተለቀቁ ዐስታወቁ ። እህታቸውን እስከ ትናንት ድረስ በስልክ ማነጋገራቸውን የገለጡ አንድ የታጋች ተማሪ ቤተሰብ የተለየ ነገር አለመኖሩን ለዶይቼ ቬለ አረጋግጠዋል ።

«እንዲህ ተብሎ ሲወራ በስልክ አግኝቻታለሁ ትናንት ጠዋት ። ከሰአት በኋላም አግኝቻቸዋለሁ ። ልጆቹ ያሉት እዛው ነው ። እስካሁን ብር ነው የሚጠየቅባቸው እንጂ ተፈትተዋል የሚባለው በጣም ውሸት ነው ።»

እኚሁ የቤተሰብ አባል እህታቸውን ዛሬ ለማናገር ፈልገው ሲደውሉ በድጋሚ እንዲደውሉ እንደተነገራቸውም አክለዋል ።  

«ዛሬ ጠዋት ራሱ ካገቱት ሰዎች መሀከል አንዱን አውርቼው ነበር ። እህቴን ማግኘት እችላለሁ ወይ ብዬ ስጠይቅ፦ ከ30 ደቂቃ በኋላ ደውዪልኝ ወጥቼ ነው አለኝ ። ስለዚህ ልጆቹ እስካሁን ያሉት እዛው ነው ። ከ100 ተማሪ በላይ አንድ ላይ አለን አለኝ ።»

በተመሳሳይ አንድ ከሀዋሳ ያነጋገርናቸው የታጋች ተማሪ ቤተሰብ የታገተች እህታቸው እስካሁን ያለችበትን እንዳላወቁ ገልጠዋል ። ሆኖም 700,000 ብር ቤዛ መጠየቃቸውን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ። በመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ታጋቾቹ «ተለቅቀዋል» የሚል ዜና መስማታቸውን የገለጹት እኚሁ ነዋሪ ካለፉት ሦስት ቀናት ወዲህ ከአጋቾቹ በኩል ስልክ እንዳልተደወለላቸው አመልክተዋል ።

«እስካሁን እኛ ጋ የመጣ ነገር የለም ። የታገቱ ልጆች አሁን ተቅቀዋው ከሆነ እነሱን አሁን መንግስት ከልጆቹ ቤተሰቦች ጋራ መጀመሪያ በስልክ ማገናኘት ነው ያለባቸው ብዬ ዐስባለሁ ። እነሱ ግን የት እንዳሉ ሳይታወቅ ተለቅቀዋል ይባላል ። የታሉ ተለቅቀዋል የተባሉት ልጆች ነው የእኔ ጥያቄ አሁን ።»

ትናንት ማምሻውን የኦሮሚያ ክልል የመንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ «በተደረገ ጥብቅ ኦፕሬሽን ከ167 ታጋች ተማሪዎች መካከል 160ዎቹ ተለቀዋል» ማለታቸውን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል ። ባለፈው ሳምንት ረቡዕ ጠዋት ከአማራ ክልል ርዕሰ ከተማ ባሕር ዳር መኪና ተራ የተነሱት ሦስት አውቶብሶች እንደነበሩ፤ ቀድመው በወጡት ሁለት አውቶብሶች ውስጥ የተሳፈሩት አብዛኞቹ የደባርቅ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደነበሩ ከእገታው ካመለጡ ተማሪዎች ያገኘነው መረጃ ያመለክታል ። በመጽሄት ዝርዝር ዘገባ ይኖረናል ።

ጋምቤላ፥ በጋምቤላ ክልል ወደ ኑዌር ዞን የሚደረግ የመጓጓዣ አገልግሎት መታጎል

በጋምቤላ ክልል ወደ ኑዌር ዞን የሚደረግ የሕዝብ መጓጓዣ አገልግሎት በአካባቢው ነዋሪዎች ደህንነት ላይ ሥጋት በመከሰቱ ከተቋረጠ አንድ ወር ማለፉን ነዋሪዎች ተናገሩ ። ለችግሩ መፈጠር ዋናው ምክንያት በክልሉ ከአንድ ወር በፊት ከነበረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እንደሆነ ይነገራል ። ከዚህ ቀደም ከነበረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ የኑዌር ተወላጆች “የአኙዋክ ተወላጆች ወደሚበዙበት ዋናው መናኸሪያ ሄደን ለመሳፈር ስጋት አለብን” ሲሉ በተደጋጋሚ ተደምጠዋል ። “ኒውላንድ” በሚባል አካባቢም መናኸሪያ በማቋቋም ወደ ኑዌር ዞኖች ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውን ይገልጻሉ ። ሆኖም የክልሉ መንግስት ኒውላንድ የነበረውን  መናኸሪያ በመዝጋቱ ወደ ኑዌር ዞኖች የመጓጓዣ አገልግሎት ከሰኔ 5 ቀን፣ 2016 ዓ.ም ጀምሮ መቋረጡን የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል።

«7 የሚሆኑ ኑዌሮች መናኸሪያ አካባቢ ተገድለዋል ። ከዚያም ኑዌሮቹ የራሳቸው መናኸሪያ መስርተው ሲገለገሉ ነበር ። የክልሉ መንግስት መናኸሪያው ወደ ነበረበት ቦታ ካልተመለሰ፣ መኪና ወደ ኑዌር ዞን መሄድ አይችልም አለ ። የኑዌር ዞን መኪናዎች በሙሉ ቆመዋል ። »

የጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኡጁሉ ጊሎ ጉዳዩን አስመልክተው ለዶይቼ ቬሌ በሰጡት ምላሽ፦ የኑዌር እና የአኙዋክ ማኅበረሰብን አንድነት በማይፈልጉ አካላት ማደናገሪያ የተፈጠረ ጉዳይ ነው ሲሉ አስተባብለዋል።  በአንድ ትንሽ ከተማም ሁለት መናኸሪያ አያስፈልግም ያሉት ኃላፊው፣ ቅሬታ አቅራቢዎቹ መንግስት ከፍተኛ ወጪ አውጥቶ ባስገነባው ዋናው መናኸሪያ እንዲጠቀሙ ብለዋል ።  የደህንነት ጉዳዩን በተመለከተም ስላለው ኹኔታ አክለዋል ።

«እንደዚህ የሚያራግቡ ሰዎች በሁለቱ ብሔሮች መካከል ሰላምና አንድነት እንዳይኖር የሚፈልጉ ሰዎች ናቸው ። በአንድ ትንሽ ከተማ ላይ ሁለትና ሦስት መናኸሪያ በተወሰኑ ግለሰቦች ፍላጎት ሳይሆን በሕዝብና በመንግስት ፍላጎት ሊደራጅ ይችላል ። በመከላከያ ኮሎኔሎች ከማኅበረሰቡ ጋር ስብሰባ ተደርጓል ። መናኸሪያ የሚሠሩ ልጆች እኛ ኃላፊነት እንወሰስዳለን ብለዋል ። የአንድም ሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ግጭትም እንዳይኖር እኛ እየሠራን ስለሆነ፣ አንድም ሰው እዛ (መናኸሪያ) ውስጥ ገብቶ ወደሚፈልግበት ቦታ እንዲሄድ ኃላፊነት እንወስዳለን።»

ዜናውን የላከልን የባሕር ዳር ወኩኪላችን ዓለምነው መኮንን ነው ።

ናይሮቢ፥ የኬንያ ፕሬዚደንት ካቢኔያቸው ከተቃውሞ በኋላ በተኑ

ለሳምንታት በሕዝብ ተቃውሞ ስትናጥ የከረመችው ኬንያ ፕሬዚደንት የካቢኔ ሚኒስትሮቻቸውን በተኑ። ፕሬዝደንት ዊልያም ሩቶ በዛሬው ዕለት የወሰዱት ርምጃ በመላው ሀገሪቱ ለተነሳው ፀረ መንግሥት ተቃውሞ እንደምላሽ ነው የታየው።

«ዛሬ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 1521 እና 1525B የጠቅላይ አቃቤ ሕግ አዋጅ ክፍል 12 በተሰጠኝ ሥልጣናት መሠረት ከአሁኑ ሰአት ጀምሮ የኬንያ ሪፐብሊክ ካቢኔ ጽሕፈት ቤቶችን እና ጠቅላይ አቃቤ ሕግን በትኛለሁ ።»

ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ የካቢኔያቸው ተቀዳሚ ዋና ጸሐፊ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሙሳሊያ ሙዳቫዲ እንዲሁም ምክትል ፕሬዝደንት ራጋቲ ጋቻጉ ሲቀሩ፤ ሌሎቹን ሚኒስትሮቻቸውን በሙሉ ማሰናበታቸውን መናገራቸውን ከናይሮቢ የወጡ ዘገባዎች ያመለክታሉ ። ፕሬዝደንቱ ርምጃውን የወሰዱት የሕዝባቸውን ድምፅ በመስማት መሆኑን ተናግረዋል ።

ኪስማዮ፥በሶማሊያ አልሸባብ 30 የሶማሊያ ወታደሮችን መግደሉን ዐሳወቀ

በሶማሊያ ከኪስማዮ ወደብ ወጣ ብሎ አልሸባብ 30 የሶማሊያ ወታደሮችን መግደሉን ዐሳወቀ ። የቡድኑ አፈቀላጤ የሆነው ራዲዮ አንዳሉስ እንደዘገበው፦ ጥቃቱ የደረሰው ትናንት ነው ። እንደዘገባው ጥቃቱ የተፈጸመው የሶማሊያ ወታደሮች ቡሎ ሃጂ በተባለችው መንደር ዘመቻ ለማካሄድ እየተዘጋጁ ሳሉ ነበር ። የሶማሊያ መንግሥት በድንገተኛው ጥቃት ሁለት ወታደሮች ብቻ መሞታቸውን እና ሌሎች አምስት ደግሞ መጎዳታቸውን ዐሳውቋል ። የጁባላንድ ግዛት የሶማሊያ ወታደሮች በአልሸባብ ታጣቂዎች ላይ «ከባድ ጉዳት» አድርሰዋል ብሏል ። የአልሸባብ ጥቃት የደረሰው የመንግሥት ወታደሮች ወደ ሃርቦ መንደር የሚወስደወን መንገድ መቆጣጠራቸውን እንዲሁም አፍማዶ ከተማ አጠገብ የሚገኘውን ዌልማሮ አካባቢን ይዘናል ባሉበት ቀን ነው ። የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን የመንግሥት ጦር የአልሸባብ አቅርቦት ማስተላለፊያ መስመርና መገናኛ የሆነውን ስልታዊ አካባቢ ተቆጣጥረዋል በማለት ዘግበዋል ።

ስቶክሆልም፥ የስዊድን ፖሊስ ባቡር ጣቢያ ፈንጂ በሻንጣ ይዘው ሊገቡ ነበር ባላቸው ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ ዛሬ ክስ መሰረተ

የስዊድን ፖሊስ ወደ ስቶክሆልም ባቡር ጣቢያ ፈንጂ በሻንጣ ይዘው ሊገቡ ነበር ባላቸው ሁለት ተጠርጣሪዎች ላይ ዛሬ ክስ መሰረተ።  በትናንትናው ዕለት ፖሊሶች የስቶክሆልም ዋና የባቡር ጣቢያን በከፊል ዘግተው ነበር ፈንጂ አምካኝ ቡድን የጠሩት። ፈንጂው ከመከነ በኋላ ምርመራ መካሄዱን ፖሊስ ዐሳውቋል ። በ30ዎቹ ዕድሜ ውስጥ የሚገኙ አንድ ወንድ እና አንዲት ሴት የሚፈነዳና ተቀጣጣይ ነገሮችን መያዝ የሚያግደውን ደንብ በመተላለፍ መታሰራቸውን አቃቤ ሕግ ገልጧል ። በተጠርጣሪዎቹ ላይም አደገኛ ወንጀል እና ንብረት ለማውደም በማቀድ ክስ ተመስርቶባቸዋል። ተጠርጣሪዎቹ ጓዳ ሠራሽ ፈንጂ፣ አደንዛዥ ዕጽና ስለት በሻንጣቸው ይዘው ወደ ሰሜናዊ ስዊድን ለመጓዝ ሲሉ መያዛቸውን የሀገሪቱ ጋዜጦች ዘግበዋል። የስዊድን ፖሊስ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ከፈንጂዎች ጋር የተያያዙ በርካታ ሴራዎችን ማክሸፉን አስታውቋል። የስካንዴኔቪያን ሃገሯ ስዊድን፤ ባለፉት ቅርብ ዓመታት እየተባባሰ የመጣውን የቡድን ጥቃት ለመቆጣጠር እየታገለች ነው።

ዋሽንግተን ዲሲ፥ የኔቶ የ3 ቀናት ጉባኤ ዛሬ ተጠናቀቀ

የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (NATO) የቻይና እና የጋራ ደህንነት ጉዳዮችን በተመለከተ ከኢንዶ-ፓሲፊክ  ሃገራት ሊመክር ነው ። ኔቶ በጋራ የደህንነት ጉዳዮች ያነጋግራቸዋል የተባሉት ሃገራት ጃፓን፤ ደቡብ ኮሪያ፤ አውስትራሊያ እና ኒውዚላንድ ናቸው ። ኔቶ ከዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ጋርም በድጋሚ ይነጋገራል ተብሏል ። የጥምረቱ 32 አባል ሃገራት ዩክሬን የኔቶ አባል የመሆኗ ጉዳይ «ፈጽሞ የማይቀለበስ ነው» ብሏል ። ኔቶ የተመሰረተበት 75ኛ ዓመቱን በማክበር ዩናይትድ ስቴትስ ዋሽንግተን ዲሲ ውስጥ ለሦስት ቀናት ያካሄደው ጉባኤ የሚጠናቀቀው ዛሬ ነው ።  

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ስለዚሕ ዝግጅት

ስለዚሕ ዝግጅት

PODC-DW-Amharisch-News-DWcom

የዓለም ዜና

ዶይቼ ቬለ የዕለቱን ዋና ዋና የዜና ትንታኔዎች ከኢትዮጵያ እና ከመላው ዓለም በየቀኑ ያቀርባል። የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ፖለቲካዊ እና ኤኮኖሚያዊ ጉዳዮችን ጨምሮ የመላው ዓለምን ውሎ የተመለከቱ ጠቃሚ መረጃዎች በሰባቱም የሣምንቱ ቀናት ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከዶይቼ ቬለ ያድምጡ።