1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊዮኔል ሜሲ አርጀንቲና የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሆነች

እሑድ፣ ታኅሣሥ 9 2015

በስተመጨረሻ የአርጀንቲናው ድንቅ ሊዮኔል ሜሲ ከአገሩ ልጅ ዲየጎ አርማንዶ ማራዶና ተስተካከለ። ኪልያን ምባፔ በ97 ሰከንዶች ሁለት ግቦች ቢያስቆጥርም ሜሲ እና አርጀንቲናን ማስቆም አልቻለም። በውድድሩ ሰባት ግቦች ያስቆጠረው ሊዮኔል ሜሲ የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል።

https://p.dw.com/p/4L8VI
FIFA Fußball WM 2022 in Katar | Finale Argentinien - Frankreich
ምስል Manu Fernandez/AP Photo/picture alliance

የ35 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ እና አርጀንቲና የኳታሩ የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሆኑ። ስድስት ግቦች በተቆጠሩበት የ120 ደቂቃ ጨዋታ ፈረንሳይ ሁለት ጊዜ አቻ መሆን ብትችልም ሜሲ እና አርጀንቲን ከዓለም ዋንጫ ባለቤትነት ማቆም አልቻለችም። 

ሊዮኔል ሜሲ በ23ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት፤ አንጊል ዲ ማርያ በ36ኛው ደቂቃ በጨዋታ ባስቆጠሯቸው ግቦች አርጀንቲና የመጀመሪውን አጋማሽ 2 ለባዶ አጠናቃለች። ይሁንና ኪልያን ምባፔ በሁለተኛው አጋማሽ ከፍጹም ቅጣት ምት እና በጨዋታ ባስቆጠራቸው ሁለት ግቦች አቻ ሆነው ጨዋታው ወደ ተጨማሪ ሰዓት ተሸጋግሯል። 

በተጨማሪ ሰዓት ሊዮኔል ሜሲ በጨዋታ ኪሊያን ምባፔ በፍጹም ቅጣት ምት ተጨማሪ ግቦች አስቆጥረው ሙሉ ጨዋታው 3-3 ተጠናቋል። 

አርጀንቲና የዓለም ዋንጫ አሸናፊ ሆነች
አርጀንቲና ለፍጻሜ ስትደርስ ይኽኛው ስድስተኛዋ ነው። ከ36 ዓመታት በኋላ ያነሳችው የዛሬው  ዋንጫ ደግሞ ሶስተኛው ሆኖ ተመዝግቦላታል። ምስል CARL RECINE/REUTERS

ጨዋታው 3-3 አቻ ከተጠናቀቀ በኋላ አርጀንቲና በመለያ ምት 4-2 አሸንፋለች። ኪንግስሌይ ኮማን የመታውን የመለያ ምት የአርጀንቲናው ግብ ጠባቂ ኢሚሊያኖ ማርቲኔዝ አድኖበታል። ሌላው ፈረንሳዊ ኦሬሊየን ቶካሜኒ የመለያ ምቱን ስቷል። 

የኳታሩን የዓለም ዋንጫ በሳዑዲ አረቢያ የ2-1 ሽንፈት የጀመረችው አርጀንቲና ውድድሩን በበላይነት ለማጠናቀቅ የሊዮኔል ሜሲ ድንቅ ክህሎት አስፈልጓታል።  ከፍጻሜ ጨዋታው ስድስት ግቦች አምስቱን ያስቆጠሩት ሊዮኔል ሜሲ እና ኪልያን ምፓፔ የኳታሩ የዓለም ዋንጫ ኮከብ ተጫዋች እና ኮከብ ግብ አግቢ ሆነው አጠናቀዋል። 

አርጀንቲና ከኔዘርላንድስ እና በፍጻሜው ከፈረንሳይ ባደረገቻቸው ጨዋታዎች የመለያ ምቶች ያዳነው ኤሚ ማርቲኔዝ የዓለም ዋንጫ ኮከብ ግብ ጠባቂ ሆኖ ተመርጧል። የ21 ዓመቱ አርጀንቲናዊ የመሀል ሜዳ ተጫዋች ኤንዞ ፈርናንዴዝ የውድድሩ ወጣት ኮከብ ተጫዋች ለመሆን በቅቷል።

ኪልያን ምባፔ
ፈረንሳዊው ኪልያን ምባፔ የኳታር የዓለም ዋንጫ ኮከብ ግብ አግቢ ሆኖ ጨርሷል። የ23 ዓመቱ ወጣት በውድድሩ ስምንት ግቦች አስቆጥሯል።ምስል Natacha Pisarenko/AP/dpa/picture alliance

ሁለቱ ብሄራዊ ቡድኖች ቀደም ሲል ሁለት ሁለት ጊዜ የዓለም ዋንጫን አሸንፈዋል። አርጀንቲና በጎርጎርሳዊው 1978 እና በ1986 ፤ እንዲሁም ፈረንሳይ ደግሞ በ1998 እና በ2018 አሸናፊ መሆን የቻሉባቸው ጊዜያት ነበሩ።

አርጀንቲና ለፍጻሜ ስትደርስ ይኽኛው ስድስተኛዋ ነው። ከ36 ዓመታት በኋላ ያነሳችው የዛሬው  ዋንጫ ደግሞ ሶስተኛው ሆኖ ተመዝግቦላታል። ሊዮኔል ሜሲ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ከመመረጡ ባሻገር በዚህ ዓለም ዋንጫ  በምድብ፣ በጥሎ ማለፍ፣ በሩብ ፍፃሜ፣ በግማሽ ፍፃሜ እና የፍፃሜ ጨዋታዎች ላይ ግብ በማስቆጠር የዓለማችን ብቸኛው ተጫዋች ሆኖ አዲስ ታሪክ ጽፏል።

ሊዮኔል ሜሲ
የ35 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ የውድድሩ ኮከብ ተጫዋች ሆኖ ተመርጧል። ሜሲ በፍጻሜው ጨዋታ ሁለት ግቦች አስቆጥሯል። ምስል Julian Finney/Getty Images

በዓለም ዋንጫው ትናንት ቅዳሜ ለሶስተኛ ደረጃ በክሮሽያ እና ሞሮኮ ብሄራዊ ቡድኖች መካከል በተደረገ ጫወታ ክሮሽያ ሞሮኮን 2 ለ 1 አሸንፋ የነሐስ ሜዳልያ ተሸላሚ መሆን ችላለች ። አፍሪካን ወክለው ከቀረቡት አምስት ቡድኖች ግማሽ ፍጻሜ መድረስ የቻለችው ሞሮኮ አራተኛ ሆና ስታጠናቅቅ ይህ ለአፍሪቃ አዲስ ታሪክ ነው።