1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የሊባኖስ ፍንዳታና ኢትዮጵያውያን

ዓርብ፣ ነሐሴ 1 2012

በዚህ ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ማምሻው ላይ የሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩንትን ባናጋው ፍንዳታ እስካሁን የሞቱት ሰዎች ቁጥር 154 መድረሱን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አመለከቱ። በአደጋው ሕይወቱን ያጣው አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻ መሆኑን ቤሩት ካለው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ያገኘው መረጃ ያስረዳል። 

https://p.dw.com/p/3gdMA
BdTD | Libanon | Protest in Beirut
ምስል Reuters/M. Azakir

«በፍንዳታው አንድ ኢትዮጵያዊ ሕይወቱን አጥቷል»


ባለፈዉ ማክሰኞ ማምሻ ላይ የሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩንትን ባናጋው ፍንዳታ እስካሁን የሞቱት ሰዎች ቁጥር 154 መድረሱን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሃን አመለከቱ። በአደጋው ሕይወቱን ያጣው አንድ ኢትዮጵያዊ ብቻ መሆኑን ቤሩት ካለው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽሕፈት ቤት ዛሬ ያገኘው መረጃ ያስረዳል። 

የሊባኖስ ዋና ከተማ ቤሩት ዛሬ የወትሮው ድባብ እንደራቃት ለዓመታት እዚያ የኖረችውና ፍንዳታው በደረሰበት አቅራቢያ እንምትሠራ የገለጸችልን ኢትዮጵያዊት ትናገራለች። ፍንዳታው ባስከተለው የመሬት ነውጥ የመሰለ መንቀጥቀጥ መናጋትም የበርካቶች ንብረት ለከፍተኛ ጉዳት ተዳርጓል ባይ ናት።

ኢትዮጵያዊቷ ከዓመታት በፊት በተጠመዱ መንታ ቦምቦች የአንድ ባለሥልጣን ሕይወት ሲጠፋ የነበረው ፍንዳታ የማክሰኞ ዕለቱ ለማዳበሪያ የሚውል ነው የተባለው ንጥረነገር ካስከተለው የፍንዳታ ድምፅ ሲነጻጸር ኢምንት ነበር ነው የምትለው። አሁንም ብዙዎች ከድንጋጤው አልተላቀቁምም ባይ ናት።  ወደአራት መቶ ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ እንደሚኖሩ ነው በቤሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ጽሕፈት ቤት የዲያስፖራ ጉዳይ የሚመለከታቸው ዲፕሎማት የገለጹልን። ማክሰኞ ማምሻውን ቤይሩት በነበረው ከባድ ፍንዳታ አደጋው በደረሰበት ስፍራ ይሠራ የነበር አንድ ኢትዮጵያዊ ሕይወቱ ማለፉን፤ ሌሎች ደግሞ ቀላል እና ከባድ ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና እያገኙ መሆኑን  የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ተመስገን ዑመር ገልጸውልናል።

Libanon Beirut | nach Explosion im Hafenviertel
ምስል Reuters/M. Azakir

ከዚህ ም ሌላ ፍንዳታው በደረሰባት የሊባኖስ ዋና ከተማ የሚገኙና ቤታቸው በዚሁ ምክንያት ለተጎዳና ሌላም ችግር ላጋጠማቸው ኢትዮጵያውያን የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም በሊባኖስ የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ርዳታ በማስተባበር እያቀረቡ መሆኑንም ዘርዝረዋል።  የሥራ ቦታዋ ፍንዳታው በደረሰበት አቅራቢያ የሆነው ኢትዮጵያዊት ዛሬ የረገፈ መስታወት ጠረጋና የተሰባበሩ ንብረቶች ጽዳት ላይ መሆናቸውን ነው የነገረችን። እሷ እደምትለውም ፍንዳታው የደረሰው የሥራ ሰዓት ካለፈ በመሆኑ ሊደርስ ይችል የነበረውን ጉዳት ቀንሷል። ሆኖም በወቅቱ ፍንዳታው ከደረሰበት የወደብ ዕቃ ማከማቻ ስፍራ ከፍተኛ ጭስ መውጣቱ እሳት የተነሳ መስሏቸው ቪዲዮ የሚቀርጹ፣ ፎቶም የሚያነሱ በርካታ ሰዎች ከደቂቃዎች በኋላ መላ ከተማዋን ያንቀጠቀጠው ድምጽ ሲከተል ለጉዳት ተዳርገዋል ትላለች።

Libanon I Explosion in Beirut
ምስል picture-alliance/dpa/M. Grigoryev

 ዛሬም ከፍርስራሽ ውስጥ ሰዎችን የማውጣቱ ሥራ መቀጠሉን፤ በዚህም ሕይወታቸውን ያጡት ቁጥር ሊጨምር ይችላል ተብሎ እንደሚገመትም አመልክታለች።  በቤሩት የኢትዮጵያ ቆንስላ ጀነራል ፍንዳታው ካስከተለው ጉዳት ሌላ ኤኮኖሚዋም ሆነ የህክምና አገልግሎቷ በተዳከመው ሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ራሳቸውን ከኮሮና ተሐዋሲ ለመከላከል የሚችሉትን ሁሉ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ዶቼ ቬለ ማሳሰቢያ እንዲያስተላልፍላቸውም ጠይቀዋል። በተለይም ወደሀገር ለመመለስ በተለያዩ ስፍራዎች ሰብሰብ ብለው ለመኖር የተገደዱት ወገኖች ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚኖርባቸው አሳስበዋል። ለዚህ ማሳሰቢያቸው መነሻ የሆናቸው ደግሞ ወደሀገር ቤት ለመመለስ የተዘጋጀች አንዲት እህት በተደረገላት ምርመራ የኮሮና ተሐዋሲ እንደያዛት የተረጋገጠ ሲሆን እሷም ወደቤቷ በመመለሷ ባለው ማኅበራዊ ትስስር ምክንያት ሌሎችም ለተሐዋሲው የመጋለጥ ዕድላቸው አሳሳቢ ሊሆን እንደሚችል በማመልከት ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።  ትናንት ዶቼ ቬለ በሊባኖስ ነዋሪ የዓይን እማኝ መሆናቸውን የገለጹ ትዕግሥት የተባሉ ምንጭን ጠቅሶ የሞቱት ኢትዮጵያውያን 10 ደርሰዋል በማለት የዘገበው የተሳሳተ መሆኑንም በዚህ አጋጣሚ እንገልጻለን።

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ