1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህወሓት ቡድኖች እና የአስተዳደር አካላት የሚያስተባብሯቸው ሰልፎች በትግራይ እየተካሔዱ ነው

ሚሊዮን ኃይለ-ሥላሴ
ሰኞ፣ ጥር 19 2017

የትግራይ ክልል ከተሞች የህወሓት ሁለት ቡድኖች እና የአስተዳደር አካላት የሚያስተባብሯቸውን የድጋፍ እና የተቃውሞ ሰልፎች እያስተናገዱ ነው። በውቅሮ በነበረ ሰልፍ ላይ በተነሳ ግጭት ቁጥራቸው ያልታወቀ ወጣቶች መጎዳታቸው ተነግሯል። ለሁለት ዓመታት ከተካሔደ ኃይለኛ ጦርነት ባላገገመው ክልል የሚካሔዱት ሰልፎች ለነዋሪዎች ሌላ ሥጋት ፈጥረዋል።

https://p.dw.com/p/4ph47
አቶ ጌታቸው ረዳ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት በሰላማዊ ሰልፍ ላይ
አቶ ጌታቸው ረዳ "የፀጥታ ሐይላችን የህዝብ እንጂ የጥቂት ቡድን የስልጣን ፍላጎት ማስፈፀሚያ እንዳልሆነ፥ ከፀጥታ ሐይላችን ጋር ሆነን ልናረጋግጥለት፣ በሌላ በኩል የፀጥታ ሐይሉ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ስራዎች እንዲከውን አንድነቱ እንዲያጠናክር በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል።

የህወሓት ቡድኖች እና የአስተዳደር አካላት የሚያስተባብሯቸው የድጋፍ እና የተቃውሞ ሰልፎች በትግራይ እየተካሔዱ ነው

በትግራይ የተለያዩ ከተሞች የትግራይ ኃይሎች ውሳኔ የሚቃወሙ እና የሚደግፉ ሰልፎች በመካሄድ ላይ ናቸው። ትላንትና እና ዛሬ በመቐለ ሁለት የተለያዩ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን፥ ሰልፎቹ የህወሓት ቡድኖች እና የአስተዳደር አካላት የሚያስተባብሯቸው ናቸው።
የትግራይ ኃይሎች አመራሮች ባለፈው ሓሙስ በሰጡት መግለጫ በዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የህወሓት ክንፍ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመሩትን ጊዜያዊ አስተዳደር እንዲረከብ

እንደሚፈልጉ ማስታወቃቸው ተከትሎ፥ በትግራይ ከፍተኛ ፖለቲካዊ ውጥረት የሰፈነ ሲሆን፥ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሚሳተፉባቸው የጦር መኮንኖቹ ውሳኔ የሚቃወሙ እና የሚደግፉ ሰልፎች በተለያዩ ከተሞች እየተካሄዱ ይገኛሉ። 

ትላንት እሁድ በዶክተር ደብረፅዮን የሚመራ የህወሓት ክንፍ ያስተባበረው የተባለ እና የትግራይ ኃይሎች አዛዦችን ውሳኔ የሚደግፍ ሰልፍ በመቐለ ከተማ ተካሒዷል። ዛሬ ሰኞ ደግሞ በተመሳሳይ በመቐለ የአስተዳደር አካላት እና በአቶ ጌታቸው የሚመራው የህወሓት ክንፍ ያስተባበሩት የተባለ የወታደራዊ መኮንኖቹ ውሳኔ ያወገዘ የተቃውሞ ሰልፍ ተካሂዷል። እነዚህ ሰልፎች እየተካሄዱ ያሉት የትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ እንዲሁም የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ሰልፍ እንዳይደረግ ያስተላለፈው ውሳኔ በመተላለፍ ነው።

በትግራይ የወታደራዊ መኮንኖችን አቋም “በመደገፍም ሆነ በመቃወም” ሰልፍ ማካሔድ ተከለከለ

በሺዎች የሚቆጠሩ ተሳታፊዎች የተገኙበት በትላንቱ የመቐለ ሰልፍ “የትግራይ ሰራዊት አመራሮች ያስተላለፉት ውሳኔ እንደግፋለን”፣ “የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ማስተካከያ ይደረግበት”፣ “ሰራዊት ለማፍረስ እየተደረገ ያለው አሻጥር አንቀበልም”፣ “የህወሓት ሕጋዊ ሰውነት በአፋጣኝ ይመለስ” የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮች ተስተጋብተዋል።

በትግራይ የተለያዩ ከተሞች የትግራይ ኃይሎች ውሳኔ የሚቃወሙ እና የሚደግፉ ሰልፎች በመካሄድ ላይ ናቸው።
በትግራይ የተለያዩ ከተሞች የትግራይ ኃይሎች ውሳኔ የሚቃወሙ እና የሚደግፉ ሰልፎች በመካሄድ ላይ ናቸው።

በሌላ በኩል ዛሬ በመቐለ ሮማናት አደባባበይ በተደረገው ሰልፍ ደግሞ “የትግራይ ሰራዊት አመራሮች ያስተላለፉት ውሳኔ ቅቡልነት የለውም” ፣ “የትግራይ ኃይሎች የህዝብ ከለላ እንጂ የአንድ መጠቀሚያ አይደሉም” ፣ “የትግራይ ጊዚያዊ አስተዳደር እንደግፋለን”፣ “ምርጫችን ሰላም ነው” የሚሉ እና ሌሎች መፈክሮች ተሰምተዋል። 

ከዚህ በተጨማሪ በዚሁ ሰልፍ የትግራይ ደቡብ ምስራቅ ዞን ከፍተኛ አመራሮች የተሳተፉ ሲሆን፥ የዶክተር ደብረፅዮን የህወሓት ቡድን የሚያወግዙ ንግግሮችም አሰምተዋል። ከዞኑ አመራሮች መካከል አቶ ፀጋይ ገብረጊዮርጊስ "የዘር ማጥፋት ጦርነት ከፈፀሙ፣ የትግራይ ግዛት ይዘው ካሉ የኤርትራ መንግስት እና የአማራ ታጣቂዎች ጋር አብሮ ለመስራት ማሰባቸው፥ የኤርትራ መንግስት እና የአማራ ኃይሎች በትግራይ ህዝብ ላይ የፈፀሙት ወንጀል የሚያጣጥል እንዲሁም በትግራይ ህዝብ እና ግዛት ክህደት ጭምረ የፈፀመ ነው" ብለዋል።

ትግራይ ክልል የቀጠለው ውዝግብ

በመቐለ፣ በሽረ፣ ዓብይዓዲ፣ ማይጨው፣ ዓዲግራት እና ሌሎች ከተሞች ቅዳሜ እና እሁድ ጀምሮ ዛሬ ሰኞ ድረስ የቀጠለ ሰልፍ እየተካሄደ ያለ ሲሆን የትግራይ ኃይል አዛዦች ውሳኔ በመቃወም እና በመደገፍ መልእክቶች ይተላለፉሉ።

200 ገደማ የሚሆኑ የጀነራል እና ኮነሬል መአርግ ያላቸው ወታደራዊ መኮንኖች ባለፈው ሳምንት ሓሙስ በሰጡት መግለጫ በዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመሩት የህወሓት ክንፍ ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲረከብ እንደሚፈልጉ አስታውቀው የነበረ ሲሆን፥ እሱን ተከትሎ ደግሞ የትግራይ ሰላም እና ፀጥታ ቢሮ የትግራይ ወታደራዊ መኮንኖች የሰጡትን መግለጫ እና የያዙት አቋም ተከትሎ የድጋፍ ይሁን ተቃውሞ ሰልፍ ማካሔድ እንደማይቻል አስታውቆ ነበር።

በትግራይ ከተካሔዱ ሰልፎች አንዱ
በመቐለ፣ በሽረ፣ ዓብይዓዲ፣ ማይጨው፣ ዓዲግራት እና ሌሎች ከተሞች ቅዳሜ እና እሁድ ጀምሮ ዛሬ ሰኞ ድረስ የቀጠለ ሰልፍ እየተካሄደ ያለ ሲሆን የትግራይ ኃይል አዛዦች ውሳኔ በመቃወም እና በመደገፍ መልእክቶች ይተላለፉሉ።

የዛሬው የመቐለ ሰልፍ ተሳታፊዎች ከሮማናት አደባባይ ተነስተው ወደ የትግራይ ፕሬዝደንት ፅሕፈት ቤት የተጓዙ ሲሆን የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ ለሰልፈኞቹ ባደረጉት ንግግር “የትግራይ ኃይሎች አዛዦች ከአንድ ቡድን ውግንና ራሳቸው እንዲያገሉ ይሰራል” ብለዋል።

የትግራይ ክልል ኃይል አዛዦች ውሳኔ የገጠመው ተቃውሞ

አቶ ጌታቸው "የፀጥታ ሐይላችን የህዝብ እንጂ የጥቂት ቡድን የስልጣን ፍላጎት ማስፈፀሚያ እንዳልሆነ፥ ከፀጥታ ሐይላችን ጋር ሆነን ልናረጋግጥለት፣ በሌላ በኩል የፀጥታ ሐይሉ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ስራዎች እንዲከውን አንድነቱ እንዲያጠናክር በዚህ አጋጣሚ ጥሪ አቀርባለሁ" ብለዋል።

በሌላ በኩል በትላንትናው ዕለት በውቅሮ ከተማ በነበረ ሰልፍ በተነሳ ግጭት ቁጥራቸው በውል ባልታወቀ ወጣቶች ላይ ጉዳት መድረሱ፥ ሶስት ሰልፈኞች ደግሞ በፖሊስ መታሰራቸው ተነግሯል። በዚሁ ጉዳይ ከከተማዋ አስተዳደር መረጃ ለማግኘት የተደረገ ጥረት አልተሳካም።

ሚሊዮን ኃይለስላሴ 
እሸቴ በቀለ
ጸሀይ ጫኔ