1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«TeenMamos» መፅሔት

ዓርብ፣ ጥቅምት 13 2013

ኢትዮጵያ ውስጥ በአስራዎቹ ለሚገኙ ወጣቶች የተዘጋጀ መፅሔት ማግኘት ብዙም የተለመደ ነገር አይደለም። ይህን የታዘቡት የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት እንግዶቻችን TeenMamos የተሰኘ መፅሔት በማዘጋጀት ክፍተቱን ለመሙላት እየተንቀሳቀሱ  ይገኛሉ። TeenMamos ምን አይነት መፅሔት ነው?  ወጣቶቹስ እነማን ናቸው? 

https://p.dw.com/p/3kK5y
TeenMamos I Saron Nathnael und Amran Wondosen
ምስል TeenMamos

የ«TeenMamos» መፅሔት

TeenMamos የተሰኘው መጽሔት ላይ አዝናኝ፣ አስተማሪ እና ወጣቶችን የሚስቡ ጉዳዮች በየምድባቸው ተከፋፍለው ይነበባሉ። መፅሔቱ ገና አዲስ ነው። በእጅ የሚዳስሱትም አይደለም። የሚገኘው በኦንላይን ብቻ ነው። የመፅሔቱ መስራቾች የ17 ዓመቷ ሳሮን ናትናኤል እና የ 15 ዓመቷ አምራን ወንዶሰን ሲሆኑ ሁለቱ የአጎትማማች ልጆች ናቸው። «ይህንን ነገር ልንጀምር ስንል የሚያመሳስለን ነገር እንፈልግ ነበር» የምትለው ሳሮን በኋላም የጋራ የሆነ የአያታቸው ማሞ  ስምን እንዳገኙ እና መፅሔቱንም በዚህ ስም እንደሰየሙ ትናገራለች። ቲን የሚለው ቃል ደግሞ ከእንግሊዘኛው ቲኔንጀር የተወሰደ እና በአስራዎቹ እድሜ ክልል የሚገኙ ወጣቶች የሚጠሩበት ጥቅል ስም ነው። መፅሔቱን ለማዘጋጀት ሀሳቡ እንዴት እንደፈለቀ ሌላዋ መስራች አምራን እንዲህ ስትል ገልፃልናለች።« እኔ እና እሷ ለማህበረሰቡ የሚጠቅም ነገር ማድረግ እንፈልግ ነበር። እና አንድ ቀን አክስታችን ቤት ደብሮን ቁጭብለን ሳለ የመፅሔት ስብስቦች አገኘን። ከዛ ለምን መፅሔት አንሰራም የሚል ሀሳብ አመጣን»
የመፅሔቱ ዋና አላማ ማዝናናት ቢሆንም ከፀጉር አበጣጠር እና ኔት ፊሊክስ ላይ የትኞቹን ፊልሞች ወጣቱን ሊያስደስቱ እንደሚችሉ ከመጠቆም ያለፈ ይመስላል። ትምህርታዊ የሆኑ እና እምብዛም ከሌሎች ሰዎች ጋር በግልፅ የማይወያዩባቸው ርዕሶችን ሳይቀሩ ይነሳሉ። ለምሳሌ ወሲባዊ ጥቃት ወይም ፆታዊ ጥቃት ምን እንደሆነ ያብራራሉ፣  እንደዚህ አይነት ጥቃት የሚደርስባቸው ወጣቶችም የት ርዳታ እንደሚያገኙ መጽሔቱ ይጠቁማል። ለአዘጋጆቹ ሳሮን እና አምራን የውጭ ሀገር መፅሔቶች በርዕስ አመራረጥ እና አቀራረብ ዘይቤ ላይ ትልቅ ሚና ነበራቸው። « TeenVogue ከሚለው መፅሔት ላይ ሀሳቦችን ወስደናል። » ትላለች አምራን። እንደዛም ሆኖ ለእኛ ሀገር የሚሆኑ ርዕሶችን መምረጥ ነበረብን ስትል የውጭ ሀገር ተሞክሮ ያላት ሳሮን ታክላለች። « አውሮፓ እና አሜሪካ ብዙ መፅሔቶች እና ለልጆች መረጃ የሚደርስበትን መንገዶች አይቼያለሁ።» የውጭ ሀገር ልጆች አስተዳደግም ከኢትዮጵያውያኑ ስለሚለይ ሳሮን እና አምራን የራሳቸውን ባህል  በመፅሔታቸው የሚያካትቱበትን መንገድ አጠኑ። ስለሆነም ስለ ዶሮ ወጥ አሰራር ወይም ስለ ቡና ታሪክ አመጣጥ የወጣቶቹ መፅሔት ላይ ይገኛሉ። የመፅሔቱ ታሪኮች ለኢትዮጵያውያን ቅርብ ሆነው ቢዘጋጁም አሁንም ቢሆን ልክ እንደ ውጭ መፅሔቶች ለአንባቢያኑ ቋንቋ ፈተና ሊሆን ይችላል። ሳሮን በእንግሊዘኛ ቋንቋ ለመፃፍ የመረጡበትን ምክንያት « የኤሌክትሮኒክስ መገልገያዎች ያሏቸው ልጆች በእንግሊዘኛ ማንበብ ይችላሉ፤ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ልጆችም በቀላሉ ማንበብ እንዲችሉ ለዛ ነው በእንግሊዘኛ የሆነው» ስትል ታስረዳለች።
የመፅሔቱ ፀሀፊዎች አዘጋጆቹ የመረጡዋቸው እድሜያቸው በ 13 እና 19 መካከል የሚገኙ ተማሪዎች ናቸው። ቅዱስ መንግስቱ ከእነዚህ ፀሀፊዎች አንዱ ነው። የ12 ኛ ክፍል ተማሪ የሆነው ወጣት ስለ ቲን ማሞ መጽሔት ከሰማበት ጊዜ አንስቶ ሁለት ጊዜ ስለ አዕምሮ ጤና ጉዳይ ለመጽሔቱ ጽፏል። በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ላይ የመፃፍ ሀሳቡም የመጣው ከራሱ ቅዱስ ነበር። « በዚህ ጉዳይ ላይ የሚሰቃዩ ጓደኞች አሉኝ። ድብርት ያለባቸው። እኔም በትንሹ አለብኝ። እና ስለዚህ ጉዳይ በደንብ የሚያውቁ ጓደኞች ስላሉኝ ለሌሎች ግንዛቤ ማስጨበጥ ስለፈለኩ ነው» በዚህ ጉዳይ ላይ ለመፃፍ የፈለኩት ይላል ቅዱስ። ምንም እንኳን እስካሁን የፃፋቸው ፁሁፎች ላይ የህክምና ባለሙያዎች አናግሮ ባይሆንም ትክክለኛ መረጃ ለመፃፍ ከብዙ ምንጮች አጣርቶ እንደሚፅፍ ገልፆልናል። ወደፊትም በዚህ ጉዳይ ላይ ቀጥሎ መፃፍ ይፈልጋል። 
ኤፍራታ ያሬድ የ 18 ዓመት ወጣት ናት። ስለ TeenMamos የሰማችው ኢንስታግራም ላይ ነው። የ 12 ኛ ክፍል ተማሪዋ ለወጣቶች የተዘጋጀ መፅሔት ስታነብ ይህ የመጀመሪያ ጊዜዋ ነው። «ብዙ መረጃዎች አሉት፤ ብዙ መዝናኛዎች አሉት። » ስትል አዘጋጆቹ ጥሩ ስራ እንደሰሩ ትናገራለች።  
የ TeenMamos መጽሔት እስካሁን ሁለት ጊዜ በኦንላይን ተዘጋጅቶ ቀርቧል።ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበው በመስከረም ወር ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በጥቅምት ወር ነው። ወጣቶቹ ወደፊትም በየወሩ አዳዲስ ርዕሶችን ይዘው መቅረብ ይፈልጋሉ። እስካሁን ከ1000 በላይ አንባቢያን መጽሔቱን ዳውንሎድ አድርገውታል የምትለው አምራን የ10ኛ ክፍል ተማሪ ናት። ትምህርት ቤት ሲከፈትም እሷ እና ዘመዷ መፅሔቱን ለማዘጋጀት እየተጋገዙ ስለሚሰሩ በቂ ጊዜ እንደሚኖራቸው ርግጠኛ ናት። የ TeenMamos መፅሔት ወደፊትም በኦንላይ ብቻ የሚቀጥል እንደሆነ አዘጋጆቹ ገልፀውልናል። 
ልደት አበበ 
ነጋሽ መሀመድ

TeenMamos መጽሄት

ለቲን ማሞስ መጽሄት ከሚጽፉት ወጣቶች መካከል አንደኛው ነው
ቅዱስ መንግሥቱ ምስል Privat