1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዝርፊያ እና ግድያ በአማራ ክልል

ረቡዕ፣ ሰኔ 26 2016

በአማራ ክልል በሚገኙ አንዳንድ ታላላቅ ከተሞች ዝርፊያ እና ነጠቃ ኅብረተሰቡን እያማረረ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናገሩ ። ዘራፊዎቹ የተለያዩ ባለ ድምፅና ድምፅ አልባ መሣሪያ በመያዝ ቀንም ሌሊትም ኅብረተሰቡን መግቢያ መውጫ እንዳሳጡት ነው ነዋሪዎቹ ገልጠዋል ።

https://p.dw.com/p/4hpdR
Äthiopien |  Injibara City
ምስል Awi Communication Office

«ዘራፊዎች ሽጉጥና ጩቤ ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት» ነዋሪዎች

በአማራ ክልል በሚገኙ አንዳንድ ታላላቅ ዝርፊያ እና ነጠቃ ኅብረተሰቡን እያማረረ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናገሩ ። ዘራፊዎቹ የተለያዩ ባለ ድምፅና ድምፅ አልባ መሣሪያ በመያዝ ቀንም ሌሊትም ኅብረተሰቡን መግቢያ መውጫ እንዳሳጡት ነው ነዋሪዎቹ ገልጠዋል ። የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ዝርፊያና ንጥቂያውን ለመከላከል የተጠናከረ ሥራ መጀመሩን አመልክቷል ። ኅብረተሰቡም የራሱን አደረጃጀት በመፍጠር ራሱን ከዘራፊዎች እንዲከላከል ኮሚሽኑ አሳስቧል ። የፋኖ ታጣቂዎች በበኩላቸው በአንዳንድ በተቆጣጠሯቸው ቦታዎች ኅብረተሰቡን ያማረሩ ዘራፊዎችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን በማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች በሚለቀቁ መረጃዎች ዐሳውቀዋል ። 

ያነጋገርናቸው የባህር ዳር፣ የጎንደር፣ የደብረማርቆስና የገንዳ ውሀ ከተማ ነዋሪዎች በቀንና በሌሊት የሚደርስባቸው የስርቆት ሙከራና ተግባር አማርሯቸዋል፣ ነዋሪዎቹ ከስርቆት ለመጠበቅ የጋብቻ የጣት ቀለበታቸውን አውልቀው እስከማስቀመጥ ደርሰዋል፡፡

አንድ የጎንደር ከተማ ነዋሪ ለዶቼ ቬሌ እንዳሉትዝርፊያው፣ ነጠቃውና ዛቻው እጅግ እየበዛ ሄዷል፣ ከንብረት አልፎ ሰዎች ራሳቸው በዘራፊዎች እየተወሰዱ ነው ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ገልጠዋል፡፡

«... የጎንደር ቅጥ ያጣ ነው፣ ንብረት ብቻ አይደለም (ዘራፊው) ቤት ገብቶ ሰውንም እያስፈራራ እየወሰደ ነው፣ ሞባይልና ብርንማ ተወው፣ ጩቤም፣ ሽጉጥም ይዞ እያስፈራራ፣ ሰው በችግር ውስጥ ሆኖም እየተቀማ ነው ።»

የእለት ኑሯቸውን ለማሸነፍ ካፍቴሪያና ሻይ ቤት ሰርተው የሚመለሱ ወጣቶች የሰሩበትን ሌቦች ይቀሟቸዋል፣ በመሳሪያም ያስፈራሯቻል፣ ዘራፊዎቹ ጠያቂ እንደሌላቸው ነው እኚህ የባህር ዳር ከተማ አስተያየት ሰጪ የሚናገሩት፡፡

«... አሁን አሁንማ (ዘራፊዎች) ሽጉጥና ጩቤ ይዘው ነው የሚንቀሳቀሱት ቦርሳ ያዝክ፣ ካፌ ሰርተው አምሽተው የሚመጡ ሰዎች የአንገታቸውን ሀብል ሳይቀር እየተነጠቁ ነው፣  ቀንም ቢሆን እጃችን ላይ እየሞነጨቁ ንብረታችን እየወሰዱት ነው፣ በአደባባይ ንብረት ነጥቆ ሲሄድ የሚናገረውም አካል የለም» ብለዋል፡፡

ባሕር ዳር ከተማ
ባሕር ዳር ከተማምስል Matyas/Pond5 Images/IMAGO

ሌላ የባህር ዳር ከተማ ነዋሪ ዝርፊያው  በቀን ጭምር እንደሚከናወን ጠቁመው ጉዳዩ ከሞባይልና ከገንዘብ ንጥቂያ አልፎ የጋብቻ ቀለበት እየተወሰደ ነው ብለዋል፣ ይህን ለመከላከልም የጋብቻ ቀለበታቸውን አውልቀው ለማስቀመት መገደዳቸውን አስተያየተ ሰጪው ለዶቼ ቬሌ ገልጠዋል፡፡

አከለውም፣ «እኔና ባለቤቴ ተነጋግረን የጋብቻ ቀለበታችንን አውልቀን ነው የምንሄደው፣ ከሞባይል ስልክ አልፎ እዛ ደርሷል፣ በአጠቃላይ ድርጊቱ ሕግና ስርዓት አለመኖሩን ነው የሚያሳየው፣ የህን እርምጃ የወሰድኩ እኔ ብቻ ኤደለሁም፣ እኔን ቀለበት እንዳወልቅ የነገሩኝ ሌሎች ወዳጆቼ ናቸው”

የደብረማርቆስ ከተማ አስተያየት እንደገለጡት ደግሞ ህብረተሰቡ በዘራፊዎች ተማሯል፣ እንቅልፍ አትቷል በጭንቅ ውስጥ ነው ያለ ሲሉ ነው አስተያየተ የሰጡት፡፡

"ማታ ላይ ብቻ ላይ ሳይሆን ቀን ራሱ በጣም እየተቸገርን ነው፣ ህብረተሰቡ እንቅልፍ አጥቶ ነው ያለው፣ በር ሁሉ እየተሰረሰረ በአጠቃላይ ህብረተሰቡ ጭንቅ ውስጥ ነው ያለው፣ ኑሮ አይደለም እየኖርን ያለነው፣ ከሁለት ሳምንት በፊት ከሰፈራችን አንድ ሰዓት ምሽት ሽጉጥ ይደቅናል፣ ያለህን ንብረት አራግፍ ብሎ ተረክበው ሄደዋል፡፡ ”

አንዲት የባህር ዳር ከተማ አስተያየት ሰጪ ጓደኛቸው በቅርቡ መዘረፏን አስታውሰው ዘራፊዎቹ ሽጉጥና ጩቤ በማሳየት በማስፈራራት ታርጋ የሌላቸውን ባለሶስት እግር ተሸከርካሪ በዋናነት ለዝርፊያ እንደሚጠቀሙ አስረድተዋል፡፡

" ቦርሳ ቀምቶ መሮጥ፣ ባጅጅ አስጠግቶ ነጥቆ መሮጥ፣ ሀብል መቀማት፣ ጩቤ ያወጣሉ፣ ስትከተላቸው ጥይት ይተኩሱብሀል፣ ሰፈራችን እንደዚያ ተሰርቷል፣ ታርጋ የሌለው ተሸከርካሪ በዋናነት ባጃጅን ነው ለዝርፊያ የሚጠቀሙት፡፡”

ጉዳዩን በተመለከተ የጠየቅናቸው የአማራ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሚዲያ ኃላፊ ኮማንደር መሳፍንት እሸቴ ተቋማቸው ችግሩን ለመቀነስ ጠንክሮ እየሰራ መሆኑን ጠቁመው ህብረተሰቡም የራሱን አደረጃጀት በመፍጠር የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡

የባሕር ዳር ከተማ
የባሕር ዳር ከተማምስል Alemnew Mekonnen/DW

"... ግርግር በበዘባቸው ወቅትና ጊዜ የፀጥታ መደፍረስ በሚያጋጥም ጊዜ የሚያጋጥሙ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፣ በተለያዩ ወቅቶች ሪፖርቶች ለኮሚሽኑ ይደርሳሉ፣ ይህን ለመከላከል ተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ያለበት ሂደት ነው ያለው፣ የፀጥታ ስምሪቶቹ ከየአካባቢውና ከወቅቱ ጋር ይገመገማሉ፣ የመከላከሉም የምርመራው ሂደትም በተለመደው መንገድ እየተከናወኑ ነው፣ በቂ ነው ወይ ከተባለ ግን ብዙ የሚቀር ነገር አለ፣ ወቅቱ የፈጠረውን ችግር እንደ ምቹ ሁኔታ የሚጠቀሙ ዘራፊዎች በየቦታው ይኖራሉ፣ የመጀመሪያው ጉዳይ ህብረተሰቡ በየአካባቢው፣ በየመንደሩ የሚሰራው ስራ ነው ትልቅ ውጤት የሚያመጣው፣ ኮሚሽኑም ባሉት አደረጃጀቶች በተለይም ሌሎች የፀጥታ አካላትን ጭምር በማካተት ስምሪት እየተሰጠ ነው፣ ስለዚህ ተግባራቱ እየተከናወኑ ነው ግን በቂ አይደለም አሁንም ጠንክረነረ እንሰራለን፡፡” ሲሉ ነው ለዶቼ ቬሌ የተናገሩት፡፡

በአማራ ክልል ከተፈጠረው ወቅታዊ የፀጥታ መደፍረስ ጋር በተያያዘ አጋጣሚውን በመጠቀም በብዙ ቦታዎች ዝርፊያና ንጥቂያ መስፋፋቱን ነዋሪዎቹ በምሬት ይገልጻሉ፡፡

ዓለምነው መኮንን

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር