ጋዜጠኛ ዜናነህ መኮንን ከዚህ ዓለም በሞት ተለየ
እሑድ፣ ኅዳር 1 2017አዘዞ ጎንደር የተወለደው ዜናነህ ከ1970ዎቹ እስከ ሰማኒያዎቹ አጋማሽ ድረስ በኢትዮጵያ ራዲዮ እና ቴሌቪዥን ድርጅት አገልግሏል። በ1980ዎቹ አጋማሽ ወደ እስራኤል ያቀናው ዜናነህ በህመም ተዳክሞ ከስራው እስኪርቅ ድረስ በኢየሩሳሌም የዶቼ ቬለ ራዲዮ ዘጋቢ በመሆን ሲያገለግል ቆይቷል ። የዶቼ ቬለ አድማጮች ዜናነህን ከመካከለኛው ምስራቅ በእስራኤል አረብ ግጭት እና ጦርነቶች ብሎም በቀጣናው በሚነሱ ፖለቲካዊ ዘገባዎች ያውቁታል። የዜናነህ መኮንን የቀብር ሰነ ስረዓት ቴል አቪቭ ውስጥ በሚገኝ ያኮም መካነ መቃብር እንደሚፈጸም ልጁ ቢታንያ ዜናነህ ገልጻለች ። ዜናነህ ባለትዳር እና የሶስት ሴቶች ልጆች አባት ነበር ።
አድማጮች የሰማችሁት የባልደረባችን ዜናነህ መኮንንን ዜናነህ በኢየሩሳሌም የዶይቸ ቬለ ተባባሪ ዘጋቢ ከሆነበት ጊዜ አንስቶ ስለመካከለኛው ምሥራቅ በመዘገብ እና በመተንተን ለዚህ ጣቢያ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክቷል። ጋዜጠኛው ከ10 ዓመት በላይ እጎአ ከ 2013 ጀምሮ የዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል የጣቢያ መክፈቻ እና በዝግጅቶች መግቢያነት የሚጠቀምባቸው ማስተዋወቂያ ድምፅም ነበር።
ከ1968 ዓ.ም ጀምሮ ከጋዜጠኝነት ሙያ ተለይቶ የማያውቀው ዜናነህ መጀመሪያ በኢትዮጵያ ራዲዮ፣ ቀጥሎ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን እና ራዲዮ፤ በዝግጅቶች እና በዜና አቅራቢነት ለረጅም ጊዜ ያገለገለ አንጋፋ ጋዜጠኛ ነበር። ወደ እስራኤል ከተሰደደ በኋላም በተለያዩ የራዲዮ፣ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እና በኢንተርኔት ዝግጅቶችን በማቅረብ ይታወቃል። ይሁንና እውቁ ጋዜጠኛ በኩላሊት ሕመም ምክንያት በጠና ታሞ እንደነበርም እናውቃለን። ዛሬ ጠዋት ከዚህ ዓለም ማለፉን አመሻሽ ላይ ቤተሰቦቹ አረጋግጠውልናል።
ልደት አበበ
ነጋሽ መሀመድ