1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለምን ያሳሰበው የምግብ ዋስትና

ዓርብ፣ ሐምሌ 19 2016

በመላው ዓለም የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ አመጋገብ ይዞታን የገመገመ አንድ ጥናት በጎርጎሪዮሳዊው 2030 የሚራብ እንዳይኖር የተመድ ያለመው እቅድ እንደማይሳካ አመለከተ። እንደጥናቱ ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023 በመላው ዓለም 733 ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ ለረሀብ ተጋልጧል።

https://p.dw.com/p/4imUP
የምግብ ዋስትና
አፍሪቃ ውስጥ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከሚደረገው ጥረት አንዱ ፎቶ ከማኅደር ምስል DW

ዓለምን ያሳሰበው የምግብ ዋስትና

እንደዘገባው ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2023 በመላው ዓለም ከሚገኙ 11 ሰዎች አንዱ፤ አፍሪቃ ውስጥ ደግሞ ከአምስት ሰዎች አንዱ ለረሀብ ተጋልጧል። በዚሁ ዓመት በጥቅሉ በዓለም 2,3 ቢሊየን ሕዝብ በመጠነኛ እና በከፋ ረሀብ ነው ዓመቱን የገፋው። ይህም በተለይ በኮቪድ ወረርሽኝ ወቅት ከታየው የቁጥር ጭማሪ ጋር የሚመሳሰል እንደሆነም ተገልጿል። ዘገባው ሪዮ ዲ ጄኔሮ ብራዚል ላይ ይፋ ሲደረግ የዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት የገንዘብ ተቋም በእንግሊዝኛ ምህጻሩ IFAD ፕሬዝደንት አልቫሮ ላሪዮ ያንዣበበውን የረሀብ አደጋ ለመቀነስ በተለይ በገጠር አካባቢ ምግብ ለማምረት መዋዕለ ንዋን ማፍሰስ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

«የ2008 የልማት ዘገባ ድህነትን ለመቀነስ ከሌላ ዘርፍ ይልቅ የእርሻው ዘርፍ እድገት በሁለት እና ሦስት እጅ አዋጪ ነው፤ ይህ ደግሞ በተለይ ከሰሃራ በስተደቡብ ባሉ ሃገራት ላይ ሲሆን አምስት እጥፍ ስኬታማ ነው። ስለዚህ ድህነትን ለማስወገድ ከፈለግን ግብርናው ላይ ስልታዊ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰት ማድረግ ያስፈልገናል። በተለይ ደግሞ ለምግብ ማምረቱ ወሳኝ በሆኑት በአነስተኛ ደረጃ ባሉት ላይ ገንዘብን ሥራ ላይ ማዋል ያስፈልጋል።»

በዚህ ዓመት ይፋ የተደረገው የዓለም የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ አመጋገብ ይዞታ ዘገባ «ርሀብ የምግብ ዋስትና ማጣት እና ሁሉም ዓይነት ያልተመጣጠነ አመጋገብን ለማስቀረት የገንዘብ ድጋፍ» የሚል ነው። ዘገባው በተመድ ዘላቂ የልማት ግቦች በሚል በጎርጎሪዮሳዊው 2030 ርሀብን ለማጥፋት የታቀደው ዘርፈ ብዙ ስልትን ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ አጽንኦት ሰጥቷል።

ኤኮ አፍሪቃ
በመላው ዓለም የምግብ ዋስትና እና የተመጣጠነ አመጋገብ ይዞታን የገመገመው ጥናት በጎርጎሪዮሳዊው 2030 የሚራብ እንዳይኖር የተመድ ያለመው እቅድ እንደማይሳካ አመለከተ። ፎቶ ከማኅደርምስል DW

ዘገባው ምግብ የሚያመርተውን ዘርፍ እንዴት በገንዘብ በመደገፍ የምግብ ዋስትናን በዘላቂነት ማረጋገጥ እንደሚችልም ያብራራል። ይህን ለማሳካት ደግሞ በተለይ የግሉን ዘርፍ፤ ትኩረት ለመሳብ ሁኔታዎችን ማመቻቸት እንደሚያስፈልግ ነው የIFAD ፕሬዝደንት አልቫሮ ላሪዮ ያመለከቱት። በዚህ በኩል ተቋማቸው ሊያጋጥሙ የሚችሉ አደጋዎችን እያሰበም ቢሆን በምግብ ማምረቱ ላይ መዋዕለ ንዋይ በጥንቃቄ ሥራ ላይ ማዋልን ያበረታታል።

«ያሉት የገንዘብ ድጋፎች በሚፈለጉበት ስፍራ መድረሳቸውን ማረጋገጥ ይኖርብናል። የዛሬው ዘገባ ከፍተኛ የምግብ ዋስትና ያጡ እና የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ያለባቸውን እና የገንዘብ አቅርቦት የሚያንሳቸውን ሃገራት ለይቶ አሳይቷል። ይህ ደግሞ የእኩልነት አለመኖርን ያባብሳል።»

ዘገባውን ያዘጋጁት የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት FAO፤ ዓለም አቀፍ የእርሻ ልማት የገንዘብ ተቋም IFAD፤ የተመድ የሕጻናት መርሃ ድርጅት UNICEF፤ የዓለም የምግብ መርሃግብር WFP፤ እንዲሁም የዓለም የጤና ድርጅት WHO በጋራ ነው። ዘገባው ከጎርጎሪዮሳዊው 1999 ዓም ጀምሮ ረሀብን በማስቆም የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ እና የተመጣጠነ ምግብን ለማዳረስ የተደረገውን ጥረት በመከታተል ተንትኗል። የዛሬ ስድስት ዓመት ሊደረስበት የታቀደውን ዘላቂ የልማት ግብ በጥልቀት በመመርመርም እንቅፋቶችን አመላክቷል።

ሸዋዬ ለገሠ

እሸቴ በቀለ