1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓለም የጋራ ሥርዓት አላት ይሆን?

ሰኞ፣ ጥር 1 2015

የገጠሙትን ጦርነት በዉይይት፣ድርድር፣ ንግግር እንዲፈቱ የጠየቁ፣የመከሩ፣ያሳሰቡ የመብት ተሟጋቾችን፣የፖለቲካ ተንታኝናጋዜጠኞችን አምና ይኼኔ እንደጠላት ሲያስወግዙ፣ሲያሳድዱ፣ ሲያሰድቡ፣ለግድያ ሲያዝቱ የነበሩ ፖለቲከኞች መቶ ሺዎችን ካስፈጁ በኋላ እንደ ጥሩ ወዳጅ ሲተቃቀፉ ማየት የሚገርመዉ ካለ ካለ እሱ-ሰሞኑን ለአዲስ አበባ-መቀሌ ዜና እንግዳ ነዉ

https://p.dw.com/p/4LvUY
USA Volodymyr Selenskiy spricht vor dem US Congress in Washington
ምስል Jonathan Ernst/REUTERS

የምዕራቡ ዴሞክራሲና የዓለም ሥርዓት

         
አብዛኛዉ ዓለም የአዲስ ዓመት መልካም ምኞት፣ስጦታ በተለዋወጠ ሳምንት የኦርቶዶክስ ክርስትና ዕምነት ተከታዮች የእየሱስ ክርስቶስን ልደት ወይም ገናን አከበሩ።ሩሲያ ለገና በዓል ለ36 ሰዓታት አዉጃዉ የነበረዉን የተናጥል ተኩስ አቁም በበዓሉ ማግስት አበቃ።ተፋላሚ ኃይላትም ሆኑ፣ ደጋፊ፣አስታጣቂዎቻቸዉ የበዓላቱን አጋጣሚ፣ የተኩስ አቁሙን ጭላንጭልም ሰላም ለማስፈን ሊጠቀሙበት አልፈለጉም።ዩናይትድ ስቴትስ የምትመራና የምታስተባብራቸዉ መንግስታት በአዲሱ ዓመትም ዘመናይ ጦር መሳሪያቸዉን ለዩክሬን እያስታጠቁ፣ ደግሞ በተቃራኒዉ ለሩሲያ ጦር መሳሪያ ሰጠች  ወይም ሸጠች የሚሏት ኢራንን በተጨማሪ ማዕቀብ እየቀጡ ነዉ።የአዲስ ዓመት ስጦታ መሆኑ ይሆን።ሆነም አልሆነ የዩክሬኑ ጦርነት መነሻ፣የኃያሉ ዓለም ተቃራኒ መርሕ ማጣቃሻ፣የዓለም ሥርዓት መዛባት መድረሻችን ነዉ ላፍታ አብራችሁኝ ቆዩ።
የቀድሞዉ የዩናይትድ ስቴትስ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ሔንሪ ኪሲንጀር የዩናይትድ ስቴትስን፣ በዩናያትድ ስቴትስ በኩልም የምዕራቡን ዓለም የፀጥታና የዉጪ መርሕ ለበጎም ይሁን ለመጥፎ በመቀየስ ፣ብዙዎች እንደሚሉት፣ አቻ ያልተገኘላቸዉ ዲፕሎማት ናቸዉ።
ጀርመናዊዉ-አሜሪካዊዉ ዲፕሎማት፣ በቅርብ የሚያዉቋቸዉ እንደሚሉት፣ ከበሳል ዲፕሎማት፣ አዋቂ፣ሴረኛ፣ተግባቢነታቸዉ እኩል ፌዘኛም ብጤ ናቸዉ።በቅርቡ ጋዜጠኛዉ «ዲፕሎማት፣የቀድሞ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር፣ፕሮፌሰር፣ ዶክተር ማን ልበልዎት ብሎ ማዕረጋቸዉን ጠየቃቸዉ።ሰዉዬዉ መለሱ «አይ የተከበሩ ካልከኝ በቂ ነዉ» ብለዉ።
ዘንድሮ (ዘመኑ በሙሉ እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ) መቶኛ ዓመታቸዉን ይደፍናሉ-ከኖሩ። «ከጥቂት ዓመታት በፊት ካንድ ጓደኛዬ ጋር ስለመፅሐፍት ስንጨዋወት---» አሉ ሽማግሌዉ ዲፕሎማት «ለምን በጣም ስለሚያሳስብሕ ነገር አትፅፍም አለኝ።» ቀጠሉ።«ባሁኑ ጊዜ በጣም የሚያሳስበኝ የዓለም ሥርዓት መጥፋት ነዉ» እያሉ።
በዚሁ ርዕስ መፅፍ አሳተሙ።The world Order  
የገጠሙትን ጦርነት በዉይይት፣ድርድር፣ ንግግር እንዲፈቱ የጠየቁ፣የመከሩ፣ያሳሰቡ የመብት ተሟጋቾችን፣የፖለቲካ ተንታኝና ጋዜጠኞችን አምና ይኼኔ እንደጠላት ሲያስወግዙ፣ ሲያሳድዱ፣ ሲያሰድቡ፣ለግድያ ሲያዝቱ የነበሩ ፖለቲከኞች መቶ ሺዎችን ካስፈጁ በኋላ እንደ ጥሩ ወዳጅ ሲተቃቀፉ ማየት የሚገርመዉ ካለ  ካለ እሱ-ሰሞኑን ለአዲስ አበባ-መቀሌ ዜና እንግዳ ነዉ።
የሐገራት መሪዎች ሲያሰኛቸዉ ሕዝብ እያቃቃሩ፣ ወጣቶችን እያጫረሱ፣ ሲያሻቸዉ  የራሳቸዉን ሕግ እየጣሱ የሚወዳጁባት ዓለም ሁነኛ ሕግ፣ደንብ ሥርዓት አላት ማለት በርግጥ ሊያሳሳት ይችላል።
ዓለም አምና ከኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እስከ ሶሪያ፣ ከአፍቃኒስታን እስከ ኢትዮጵያ፣ ከናጎርኖ ካራባሕ እስከ ቡርኪናፋሶ በተጫሩና በቀጠሉ ጦርነቶች ሚሊዮኖች አልቀዉባታል።
እንደ ዩክሬን ጦርነት ግን  ብዙ መንግስታት የተሞጀሩበት፣ዘመናይ ጦር መሳሪያቸዉ የተፈተሸበት፣ ብዙ ዓለምን በእሕል፣ማደበሪያ፣በጋዝና ዘይት እጦት ያንገረገበ ምናልባትም ለኑክሌር ፍንዳታ ያሰጋ የለም።
ጦርነቱ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደቆጠረዉ እስካሁን ሰባት ሺሕ የዩክሬን ዜጎችንና በሺሕ የሚቆጠሩ የሩሲያ ወታደሮችን ሕይወት አጥፍቷል።የሮማ ካቶሊካዊት ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ «የጦርነት ዋጋ ይሉታል።
«የጦርነቱ ሰለቦችን፣ በዚሕ ጦርነት የወደቁ ወታደሮችን አናቶች አስባለሁ።ልጆቻቸዉን ያጡ የሁለቱንም የዩክሬንና የሩሲያ እናቶችን አስባለሁ።ይሕ የጦርነት ዋጋ ነዉ።በጦርነቱ ወታደር ልጆቻቸዉን ላጡ ለዩክሬንም ለሩሲያም እናቶች እንፀልይ።»
የጦርነቱ ዋጋ ከሰዉ ህይወት በተጨማሪ በዩክሬን፣ በአስታጣቂዎችና በሩሲያ ሐብት፣ ንብረት ላይ ያደረሰዉ ጥፋትና ኪሳራ በአንዳዶች ግምት በትሪሊዮን ዶላር ይቆጠራል።
የሩሲያዉ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን የኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ገናን ምክንያት በማድረግ ያወጁት የ36 ሰዓት የተናጥል ተኩስ አቁም አስፈሪዉን ጦርነትና መዘዙን ለማቆም እንደ መንደርደሪያ ሊያገልግል ይችል ነበር።
የዩክሬንና የደጋፊዎችዋ አፀፋ  ተኩስ አቁምን ማጣጣል፣ ሩሲያን ማዉገዝ፣ ለተጨማሪ ዉጊያ መጠጋጀት መሆኑ ነዉ-ቀቢፀ ተስፋዉ።ዩናይትድ ስቴትስ ለግሪጎሪያኑ የገና «ስጦታ» ለዩክሬን ፓትርየት የተባለዉን ዕዉቅ ፀረ-ሚሳዬል ሚሳዬሏን አስታጥቃለች።ፈረንሳይና ጀርመን ደግሞ ለኦርቶዶክሶቹ የገና «ስጦታ» ዘመናይ ታንኮቻቸዉን ለግሰዋል።
ለወትሮዉ ንግድና ሐብት ማፍራትን ያበረታታል የሚባለዉ ለዘብተኛዉ የጀርመን የነፃ ዴሞክራቶቹ ፓርቲ የ(FDP) መሪና የሐገሪቱ የገንዘብ ሚንስትር ክርስቲያን ሊንድነር እንዳሉት ደግሞ መንግስታቸዉ ለዩክሬን የሚሰጠዉ ሁለንተናዊ ድጋፍ ይቀጥላል።
                 
«ዩክሬን ፖለቲካዊ፣ቁሳቁሳዊና ወታደራዊ ድጋፍ መስጠታችንን እንደምንቀጥል በኛ  ልትተማመን ትችላለች።አሁን ተጨማሪ ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት ተባባሪዎቹ ሐገራት እየተወያዩ ነዉ።ይሕ ተገቢ ዉሳኔ ነዉ ብዬ አምናለሁ።እንዲያዉም ከተባባሪዎቻችን ጋር እንዲሕ አይነቱን እርምጃ ለመዉሰድ ፈጥነን መወሰን አለብን።»
ዩክሬን አምና 355 ሺሕ የማይሞላ ሕዝብ ካላት አይስላድ እስከ ዩናይትድ ስቴትስ ካሉ 40  መንግስታት ከ120 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያወጣ የገንዘብና የጦር መሳሪያ ድጋፍ ተደርጎላታል።
የዩክሬን ስደተኞችን ለመርዳት፣የዩክሬን ወታደሮችን ለማሰልጠን፣ ለማማከር፣ ሩሲያ ድንበር ጦር ለማስፈርና ሩሲያን ለመሰለል የወጣና የሚወጣዉ ሐብት፣ዕዉቀት፣ ጊዜና ገንዘብ ለጊዜዉ ሚስጥር ነዉ።ሩሲያ፣ዩክሬንም ሆነች ለዩክሬን መንግስት ሐብት፣ዕዉቀት፤ጦር መሳሪያና ገንዘቡን የሚረጨዉ አሜሪካ መራሹ ዓለም የሰላም ድርድር አማራጭን እስካሁን እንደዘጋ ነዉ።
ምዕራቡ ዓለም በሩሲያ ላይ የሚጥለዉ ማዕቀብ አላባራም።ኢራንንም ከሩሲያ ደብሎ ከ1979 ጀምሮ ቴሕራኖች በለመዱት ማዕቀብ ላይ አዲስ ማዕቀብ ጨምሮላቸዋል።ቴሕራኖችን በማዕቀብ በመቅጣት የሩቅ ኦሺኒያቱ ትንሽ ደሴት ኒዉ ዚላንድ ቀዳሚ መሆንዋ በርግጥ ፈገግ ያሰኝ ይሆናል።የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር ጄሲንዳ አርደርን ግን አረጋገጡ።ታሕሳስ አጋማሽ
«ለሩሲያ ድሮን በመስጠቷ በኢራን ላይ ማዕቀብ መጣላችንን ዛሬ ጠዋት አስታዉቀናል።ኢራን በሩሲያ የማዕቀብ ደንብ መሰረት ከራስዋ ከሩሲያና ከቤሎሩስ ቀጥሎ ማዕቀብ የተጣለበት ሶስተኛዋ ሐገር ናት።»
የኢራን እስላማዊ አብዮተኞች የቴሕራንን ቤተ-መንግስት ከተቆጣጠሩበት ከ1979 ጀምሮ የተፈራረቁ የዩናይትድ ስቴትስ መሪዎችና አስተዳደራቸዉ በሙሉ በኢራን ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።ተባባሪ፣ተከታያዎቻቸዉ፣ የተባበሩት መንግስታትም ማዕቀብ እንዲጥል አድርገዋል።
ከዲሞክራቶቹ ጂሚ ካርተር እስከ ሪፐብሊካኑ ሮናልድ ሬገን፣ ከክሊንተን እስከ ቡሽ፣ ከኦባማ እስከ ትራምፕ ለነበሩ መሪዎች ቴሕራኖች አንድም ምዕራባዉያንን  አሳጋች፣ሁለትም አሸባሪ፣ሶስትም ኑክሌር ጦር መሳሪያ አምራች ነበሩ።ናቸዉም።ጂሚ ካርተር 1979።ቢል ክሊንተር 1996።ጆርጅ ቡሽ 2002።ባራክ ኦባማ 2010።ዶናልድ ትራምፕ 2019 ኢራን ላይ ማዕቀብ ጥለዋል።
ጆሴፍ ባይደንስ ለምን ይቅርባቸዉ።የባይደን አስተዳደር ኒዉዚላንድን ተከትሎ በኢራን የመከላከያና የየብስ ኢንዱስትሪ ኃላፊና ሰራተኞች ላይ ባለፈዉ ሳምንት ማብቂያ ማዕቀብ ጣለ።ለማዕቀቡ የተሰጠዉ ምክንያት የኢራን መንግስት ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ማሰር፣ማንገላታት፣ መግደሉ አይደለም። ቴሕራኖች ለሞስኮዎች ሰዉ አልባ አዉሮፕላን (ድሮን) መስጠት ወይም መሸጣቸዉ እንጂ።
በብዙ ማዕቀብ በመቀጣት እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ አንደኛዋ ኢራን ነበረች።ካምና ጀምሮ ሩሲያ የአንደኝነቱን ደረጃ ስትይዝ ኢራን ወደ ሁለተኝነት ዝቅ ብላለች።ለዘመኑ ዓለም አሜሪካኖችና ተባባሪዎቻቸዉ ኪቭን በገፍ ማስታጠቅ፣መርዳት፣ ከጦርነት መማገዳቸዉ  ሕጋዊ ነዉ።ኢራኖች ከሞስኮዎች ጎን መቆማቸዉ ግን ወንጀል።
ዓለም በርግጥ የምትመራበት የፖለቲካ ባሕል፣ተጠይቅ፣ደንብ፣ሕግና ስርዓት አላት ይሆን? አናወቅም።ኪሲንጀር ግን የላትም ባይ ናቸዉ።
                                         
«ባሁኑ ዘመን የተለያዩ የዓለም ክፍሎች አንዳቸዉ ከሌላቸዉ ጋር ይገናኛሉ።የጥንቶቹ የሮማና የቻይና ኢምፓየሮች የኖሩና ዓለምን የገዙት አንዳቸዉ ስለሌላቸዉ ብዙ ሳያዉቁ ነበር።በአሁኑ ዘመን ግን የተለያየ ታሪክ ያላቸዉ የተለያዩ ማሕበረሰባት የአንድ ዓለም አቀፍ ስርዓት አካል ናቸዉ።ይሁንና ለዓለም ስርዓት የተግባቡበት ፅንሰ ሐሳብ የለም።»
አንዳዶች የምዕራቡ ዴሞክራሲ አደጋ ተጋርጦበታል ይላሉ።ሌሎች ዴሞክራሲዉ ራሱ ከበሳል ፖለቲከኞች ይልቅ አፈ ጮሌዎችን፣ ከአርቆ አሳቢዎች ይበልጥ የፖለቲካ አቀንቃኞች፣ ሆሆይታ የሚያበዙና ስሜትን የሚቀሰቅሱ ብልጣ ብልጦችን ለስልጣን አብቅቷል ባዮች ናቸዉ።
ሌሎች ደግሞ ጥቅምና ሐብት ለማጋበስ የሚደረገዉ ሩጫ ለከት በማጣቱና በጡንጫና ጠመንጃ መመካቱ በመናሩ የሕግ፤ደንብና ስርዓት አስፈላጊነት ተሸርሽሯል ባይ ናቸዉ።ሌላ ባዮችም አሉ።እርስዎስ?

የሩሲያ ዘመናይ ጦር መሳሪያ
የሩሲያ ዘመናይ ጦር መሳሪያምስል Alexander Zemlianichenko/AP Photo/picture alliance
ጀርመን ለዩክሬን ያስታጠቀችዉ ታንክ
ጀርመን ለዩክሬን ያስታጠቀችዉ ታንክምስል BeckerBredel/IMAGO
ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን ያስታጠቀችዉ ፓትሪየት ሚሳዬል
ዩናይትድ ስቴትስ ለዩክሬን ያስታጠቀችዉ ፓትሪየት ሚሳዬል ምስል Ints Kalnins/REUTERS
Wladimir Putin
ምስል Pavel Bednyakov/Kremlin/REUTERS

ነጋሽ መሐመድ 

አዜብ ታደሰ