1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚሰሜን አሜሪካ

ዓለም አቀፍ የአፍሪቃ የዲያስፖራ ቀን

ማክሰኞ፣ መጋቢት 10 2016

ዓለም አቀፍ የአፍሪቃ ዲያስፖራ ቀን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተከበረ ። የአፍሪቃ ዲያስፖራ ማኀበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዋጅ ሥራ ላይ ለማዋል እየተጣረ መሆኑን ተገልጧል ። ዓለም አቀፍ የአፍሪቃ የዲያስፖራ ቀን፣ ትናንት በጆርጂያ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ውስጥ በከፍተኛ ድምቀት ተከብሯል።

https://p.dw.com/p/4duMA
ዓለም አቀፍ የአፍሪቃ ዲያስፖራ ቀን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተከበረ
ዓለም አቀፍ የአፍሪቃ ዲያስፖራ ቀን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተከበረምስል Tariku Tessema/DW

የአፍሪቃ ዳያስፖራ አስተዋጽኦ

ዓለም አቀፍ የአፍሪቃ ዲያስፖራ ቀን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተከበረ ። የአፍሪቃ ዲያስፖራ ማኀበረሰብን ተጠቃሚ የሚያደርግ አዋጅ ሥራ ላይ ለማዋል እየተጣረ መሆኑን ተገልጧል ። ይህንኑም በዩናይትድ ስቴትስ የጆርጂያ ግዛት የላይኛው ምክር ቤት/ሴኔት/ ዓለም አቀፍ ትብብር ሊቀመንበር ሴናተር ጀምስ ዶንዜላ በበዓሉ ወቅት ለዶይቸ ቬለ ተናግረዋል ። ዓለም አቀፍ የአፍሪቃ የዲያስፖራ ቀን፣ ትናንት በጆርጂያ የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ውስጥ በከፍተኛ ድምቀት ተከብሯል።

የአፍሪቃ ዳያስፖራ አስተዋጽኦ

ዝግጅቱ የአፍሪቃ ዲያስፖራ አባላት፣ በአሜሪካ ማኀበረሰብ ውስጥ ያበረከቱትን አስተዋጽኦ በመዘክር፣ የበለጸገውን ባህላዊ ቅርሶቻቸውን የሚያስተዋውቁበት መድረክ የፈጠረ ነበር።

በዓሉ በጆርጂያ ግዛት ምክር ቤት የመከበሩን ፋይዳ በተመለከተ የጠየቅናቸው ሴናተር ዶንዜላ የሚከተለውን መልሰዋል።

"ዛሬ ዓለምአለም የአፍሪቃ ዲያስፖራና የአፍሪካ ቀን ነው። በየዓመቱ እናከብረዋለን። በኮንግረስ እና በሴኔት ያሉ ባልደረቦቼ ከመራጮቻቸው ጋር እንዲገናኙ እድል እናመቻቻለን።በንግድ ስራ ከተሰማሩ መሪዎች ጋር በመነጋገር እና ያሉበትን ሁኔታ በመረዳት፣ለንግድ ማካሄጃ የሚሆን ተጨማሪ ገንዘብ እንዲመደብ ድምጽ እንሰጣለን። በየደረጃው የሚገኙ የንግድ ተቋማትን ለማገዝ ዝግጁ ነን።"

የጆርጂያ ሴኔት ያወጣው ደንብ

የጆርጂያ ግዛት የላይኛው ምክር ቤት/ሴኔት/የአፍሪቃ ዲያስፖራ ደንብን አጽድቋል። ሴናተሯ፣ይህ ደንብ በአሜሪካ ለሚገኘው የአፍሪቃ ዲያስፖራ ማኀበረሰብ ምን ጠቀሜታ እንደሚኖረው ሲናገሩ የሚከተለውን ብለዋል። 

"እኛ ይህ ቀን በጆርጂያ ግዛት ውስጥ አስደናቂ ቀን መሆኑን አውጀናል። ምክንያቱም ከተለያዩ የዲያስፖራው ማኀበረሰብ የተውጣጡ ባህላቸውን ለማስተዋወቅ እዚህ መጥተዋል። አፍሪቃ ምን እንደምትመስል እያየን ነው። ስለዚህ የዚህየዲያሰፖራ ቀን  ዋና ነጥብ፣ሁላችንም እንድንገናኝ አድርጎናል።የጆርጂያ ሕግ በሚፈቅደው ልክ ከሁሉም ጋር ተገናኝተን እንወያያለን።"

ይህን ደንብ፣ "ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ" ሲሉ ሴናተር ጉንዜላ ጨምረው ገልጸውታል።

ዓለም አቀፍ የአፍሪቃ ዲያስፖራ ቀን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተከበረ
ዓለም አቀፍ የአፍሪቃ ዲያስፖራ ቀን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ተከበረምስል Tariku Tessema/DW

ወይዘሮ ሚሚ ታደሰ፣የኢትዮጵያ ማኀበረሰብ ማኀበር በአትላንታ የቦርድ አባል ሲሆኑ፣ ማኀበራቸውን በመወከል በበዓሉ ላይ ተገኝተው  ነበር።

መድረኩ ኢትዮጵያን ያስተዋውቃል

"እኔ ኮሚኒቲዬን ወክዬ ነው በኮሚኒቲዬ  በኩል የመጣኹት። በውነቱ በጣም በጣም ደስ የሚል ነው። እንደዚህ ዓይነት ቦታ ላይ ሁልጊዜ መሳተፍ አለብን።ጥሩ ጥሩ አስፈላጊ ሰዎችን ለማግኘት በተለይ ወጣቱ የስራ ዕድል ለመፍጠር፣ እንደዚህ ዓይነት ቦታ መገኘት አለባቸው።"  ዝግጅቱ ኢትዮጵያን የማስተዋወቅ ዕድል እንደሚፈጥም ወይዘሮ ሚሚ አመልክተዋል።

"ባገኘነው ቀዳዳ ሁሉ ኢትዮጵያን ማስጠራት አለብን። ኢትዮጵያ ልክ እንደሌላው የተማሩ ዜጎች አሏት በጣም ብዙ።እና እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ህንዶቹን ግሪኮችን ቁጭ ብለን ከምናደንቅ፣ እነሱ የደረሱበት ደረጃ መድረስ አለብን፣ እና ወገኖቻችንን መርዳት አለብን። እጅ ለእጅ እንያያዝ መንገዶችንና ዕቅዶችን እናውጣ እና እንበርታ።"

የዳያስፖራ አማካሪ ምክር ቤቱ ጉባዔ

ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በርካታ አፍሪቃውያን ይኖራሉ
ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በርካታ አፍሪቃውያን ይኖራሉ ። ካፒቶል ሕንፃምስል Ting Shen/Xinhua/picture alliance

 በሌላ በኩል የአሜሪካ ኘሬዚዳንት ጆሴፍ ባይደን  የአፍሪቃ ዲያስፖራ ተሳትፎ በዩናይትድ ስቴትስ አማካሪ ምክር ቤት ፣አትላንታ ጆርጂያ በሚገኘው ስፔልማን ኮሌጅ ጉባዔውን አካሄዷል።

ጉባዔው፣ በአፍሪቃና በአሜሪካ መኻከል ያለውን የባህልና የትምህርት ፕሮግራሞችን ለማስፋት እንዲሁም ከንግድ ኢንቨስትመንት እና ምጣኔ ሀብተ ጋር በተገናኘ በአሜሪካ የሚገኙ ዲያስፖራዎችን ተሣትፎ ማሳደግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ  መክሯል።

አማካሪ ምክር ቤቱ፣ በአፍሪቃ ዲያስፖራ ማኀበረሰብ መኻከል ያለውን የባህል፣ ማኀበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለማጠናከር፣ እንደ ጎርጎርጎሮሳዊው ጊዜ አቆጣጠር መስከረም 2003 ላይ፣በፕሬዚዳንት ባይደንና በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አንቶኒ ብሊንከን ይፋ መደረጉ አይዘነጋም።

ታሪኩ ኃይሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ