1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ውይይት፦አከራካሪው የስደተኞች አዋጅ

እሑድ፣ ጥር 19 2011

ኢትዮጵያ ከዜጎቿ ተርፎ ላስጠለለቻቸው ከ900 ሺሕ በላይ የጎረቤት አገራት ስደተኞች የሚሰጥ የስራ ዕድል አላት? ኖራትም አልኖራት በቅርቡ የጸደቀው አዋጅ ዕውቅና ላገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የመስራት፤ የመማርና በፋይናንስ ተቋማት የመገልገል መብት ሰጥቷል። የኢትዮጵያ ውሳኔ ምን ይፈይዳል? ፖለቲካዊና ምጣኔ-ሐብታዊ ዳፋውስ ምንይ ይሆን?

https://p.dw.com/p/3CHNX
Äthiopien Flüchtlinge aus Eritrea in Tigray
ምስል DW/J. Jeffery

ውይይት፦አከራካሪው የስደተኞች አዋጅ

ኢትዮጵያ ባለፈው ሳምንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያጸደቀችው የስደተኞች አዋጅ ዕውቅና ላገኙ ስደተኞች እና ጥገኝነት ጠያቂዎች የመሥራት መብት አጎናፅፏል። እነዚሁ ስደተኞች እርሻ፣ ኢንዱስትሪ፣ አነስተኛና ጥቃቅን፣ እደጥበባትና ንግድ የመሳሰሉ ዘርፎች ውስጥ በግል ለመሰማራትና የንግድ ማኅበሮችን ለማቋቋም ተፈቅዶላቸዋል። 

ይኸው አዋጅ ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ አጋሮቿ ጋር በመተባበር ለዜጎቿ እና ለስደተኞች ሥራ ለመፍጠር ላዘጋጀችው እቅድ አተገባበር ሕጋዊ መሠረት ይሰጣል። Jobs Compact በተባለው እቅድ በኢትዮጵያ በሚገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮች 30 ሺሕ ስደተኞች ለመቅጠር ታስቧል። 

ከ900 ሺሕ በላይ ስደተኞች ያስጠለለችው ኢትዮጵያ ያጸደቀችው አዋጅ የተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች መርጃ ድርጅትን የመሰሉ ተቋማት ተራማጅ ሲሉ አወድሰውታል። ተንታኞች ግን ኢትዮጵያ የጀመረችው መንገድ አውሮጳውያን ድንበር እና ባሕር አቋርጠው ወደ ግዛቶቻቸው የሚደርሱ ስደተኞችን ለመግታት የሚያደርጉት ጥረት አንድ አካል አድርገው ይቆጥሩታል።

በኢትዮጵያ የሚገኙ ስደተኞች ከዚህ ቀደም ከነበራቸው የተሻለ መብት የሚያጎናፅፈው አዋጅ ለአገሪቱ ፖለቲካ፣ ኤኮኖሚ እና ፀጥታ ፈተና ሊፈጥር እንደሚችል በዛሬው የውይይት መሰናዶ የተሳተፉ ባለሙያዎች ያስጠነቅቃሉ። 

ስደተኞች ኢ-መደበኛ ወደ ሆነው የኤኮኖሚ ክፍል ገብተው በከተሞች እና ገጠራማ አካባቢዎች ከሚገኙ ሥራ አጥ ወጣቶች ጋር ፍትጊያ ሊፈጠር እንደሚችል ሥጋት ያላቸውም ይገኙበታል።

በዛሬው ውይይት የምጣኔ ሐብት ጥናት ባለሙያው ዶክተር አየለ ገላን፤ በስደት ጉዳይ ላይ ጥናት የሰሩት ዶክተር ደረሰ ጌታቸው እና አቶ ዮርዳኖስ አልማዝ ሰይፉ ተካፍለዋል።

ሙሉ ውይይቱን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ። 
እሸቴ በቀለ