1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዉይይት፣ ሙስና በኢትዮጵያ

እሑድ፣ ሐምሌ 17 2014

ንግድ ፈቃድ፣የ ግንባታና የስራ ፈቃድ፣ ቦታ፣ ቤት የመሳሰሉትን ለማግኘት፣ የቀበሌ መታወቂያ፣ መንጃ ፈቃድ፣ የልደት ሰርቲፊኬት፣ ፓስፖርት፣ የስልክ፣ የዉኃ፣ የመብራት፣ ግብር ለመክፈል፣ የሕክምና ሳይቀር አገልግሎቶችን ለማግኘት አንድም በየመስሪያ ቤቱ ዘመድ፣ ወዳጅና ዉላጅ መኖር ሁለትም ገንዘብ መክፈል እንደ ባሕል እየተለመደ ነዉ።

https://p.dw.com/p/4EX0C
Hände übergeben Euros
ምስል picture-alliance/U.Baumgarten

«የሙስናዉ ደረጃ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነዉ...»

ለዛሬዉ ዉይይታችን ጥቅል ርዕስ ለመስጠት ያክል ሙስና በኢትዮጵያ ብለዋነዋል።ኢትዮጵያ ዉስጥ ከቀበሌ  እስከ ክልል መስተዳድር የሚገኙ ባለስልጣናት የተጣለባቸዉን ሥራና ኃላፊነት በአግባቡ እንደማይወጡ፣ ግብር ከፍሎ ደሞዝ ከሚቆርጥላቸዉ ምናልባትም ከመረጣቸዉ ሕዝብ ጉቦ፣ ምልጃ፣መደለያ እንደሚጠይቁ፣በየእጃቸዉ የገባ የሕዝብና የመንግስት ንብረትን ለየግላቸዉ እንደሚያዉሉት በሰፊዉ እየተዘገበ ነዉ።

በቅርቡ በችጋር ከሚማቅቀዉ ችግረኛ ሕዝብ ጉሮሮ ቀምተዉ፣በምፅዋት የተገኘ እሕልና ሌላ ቁሳቁስ በሕዝብ ስም ሸጠዋል፣ ጉቦና ምልጃ ተቀብለዉ የሐሰት ሰነድ ፈርመዋል ተብለዉ የተጠረጠሩ ኮሚሽነር ታስረዋል።አዲስ አበባ መስተዳድር ለዓመታት ከልጆቹና ከራሱ ጉርስ ቆጥቦ ባጠራቀመዉ ገንዘብ ቤት አገኛለሁ ብሎ ተራ የሚጠብቀዉ ተራ የከተማይቱ ነዋሪ በስሙ የተሰሩ ሕንፃዎች ገንዘብ ለከፈሉ ሌሎች ሊሰጥ ወይም ዕጣ ሊወጣ ሲል መሰረዙን ሰምተናል።

በአዲስ አበባ የጋራ መኖሪያ  ቤቶች መርሐ ግብር መሠረት ለዓመታት ገንዘብ ቆጥበዉ ዕጣ ሊወጣላቸዉ የሚገባ 79ሺሕ ነዋሪዎች መሆን ሲገባቸዉ ዕጣዉ ሊወጣ ሲል ግን ከ70 ሺሕ የሚበልጡ ግን በቁጠባዉና በወረፋዉ ያልነበሩ ሌሎች  ሰዎች የዕድሉ ተካፋይ እንዲሆኑ ተካትተዉ እንደነበር ተዘግቧል።

Symbolbild Korruption Deutschland
ምስል picture-alliance/dpa

የዕጣዉን አወጣጥ ለማጭበርበር ሞክረዋል የተባሉ ባለስልጣናትና ባለሙያዎች መያዛቸዉ ተዘግቧል።ይሁንና የኮሚሽነሩንም ሆነ የአዲስ አበባ ባለስልጣናትና ባለሙያዎች የመታሰራቸዉ ዜናን   የሰሙ በርካታ ኢትዮጵያዉያን እርምጃዉን ከክምሩ መሐል አንዲት ሰንበሌጥ የመምዝ ያክል ነዉ የቆጠሩት።

የሙስናን ደረጃ የሚያጠናዉ ትራንስፓረንሲ ኢንተርናሽናል የተባለዉ ተቋም እንደ ግሪጎሪያኑ አቆጣጠር በ2021 (አምና) ባወጣዉ መዘርዝር ኢትዮጵያ በሙስና ከ180 ሐገራት 87ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።የሙስናዉ መጠን ግን ከ2012 (እጎአ) ወዲሕ እየቀነሰ መምጣቱን የተቋሙ ሰንጠረዥ ያመለክታል።የኢትዮጵያን ሙስና  የሚያጠኑ፣ የሚከታተሉና በየኑሯቸዉ ላይ ያደረሰዉን ጉዳት የሚያዉቁ ግን ሙስና እየቀነሰ መጥቷል የሚለዉን የተቋሙን ሰንጠረዥ አይቀበሉትም።

እንዲያዉም ብዙዎች እንደሚሉት ንግድ ፈቃድ፣የግንባታና የስራ ፈቃድ፣ ቦታ፣ ቤት የመሳሰሉትን ለማግኘት፣ የቀበሌ መታወቂያ፣ መንጃ ፈቃድ፣የልደት ሰርቲፊኬት፣ፓስፖርት፣የስልክ፣የዉኃ፣የመብራት፣ግብር ለመክፈል፣ የሕክምና ሳይቀር  አገልግሎቶችን ለማግኘት አንድም በየመስሪያ ቤቱ ዘመድ፣ ወዳጅና ዉላጅ መኖር ሁለትም ገንዘብ መክፈል እንደ ባሕል እየተለመደ ነዉ።

Symbolbild Korruption
ምስል Gina Sanders/Fotolia

አገልግሎቶችን ማግኘት የሚገባቸዉ ሲነፈጉ ሕገወጦች ወይም ማግኘት የማይገባቸዉ ደግሞ በገንዘብ፣  በምልጃና ጉቦ በቀላሉ ይሸምቷቸዋል ይባላል። በየመስሪያ ቤቱ ደጃፍ ጉቦ የሚያቀባብሉ  ደላሎች እንዳሉም ይነገራል። ሙስና በኢትዮጵያ ያለበት ደረጃ፣ የሰዉ አስተሳሰብ፣ ቁጥጥሩና ዉጤቱን አንስተን እንወያያለን።

ነጋሽ መሐመድ