1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ወደ ሥርዓት አልበኝነት ሊያመራ ይችላል"

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 27 2016

"የክልሉ አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ከመስራት ይልቅ፥ ችግሮች በመዘርዘር ተጠምዷል ሲሉ ወቅሰዋል። አቶ አሉላ "እኔ በጣም የሚያሳዝነኝ በትግራይ ችግርቹ ተዘርዝረው እየተነገሩ ያሉት፣ ችግሮቹ ሊፈቱ ስልጣን በያዙ ሰዎች ነው። ሐላፊነታችሁ ልትወጡ ይገባል" የሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አሉላ ሃይሉ፥

https://p.dw.com/p/4j4yG
 Meeting on Current Affairs in Tigray 03.08.2024
ምስል Million Haileslasse/DW

"ሐላፊነታችሁ ልትወጡ ይገባል"

በትግራይ ሕገወጥነት መስፈኑ እና ወደከፋ ደረጃ እያመራ መሆኑ ተገለፀ። በክልሉ ምሁራን የተደረገ ጥናት በትግራይ "የስርዓት ለውጥ" ማምጣት እየታዩ ናቸው ለተባሉ ችግሮች መፍትሔ ተደርጎ ቀርቧል። የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ፥ በክልሉ መንግስት ስራው እንዳይሰራ መቸገሩን ገልፀዋል። ተቃዋሚዎች በበኩላቸው የክልሉ አስተዳደር ሐላፊነቱ ከመወጣት ይልቅ ችግሮች መዘርዘር ላይ ተጠምዷል ብለው ይወቅሳሉ።

በትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር በተደራጀ ገለልተኛ የተባለ አጥኚ ቡድን የተደረገው ጥናት እንደሚለው፥በክልሉ ሕገወጥነት መስፈኑእና ይህም ወደ ስርዓት አልበኝነት የሚሄድበት ዕድል ከፍተኛ መሆኑ ይገልፃል። የመንግሰት መዋቅር በአንድ ፓርቲ መጠለፉ፣ የክልሉ ህዝብና መንግስት ሀብት በግለሰቦች፣ የውጭ ዜጎች ጭምር እየተዘረፈ መሆኑ፣ የፍትህ ስርዓቱ ተአማኒነት ማጣቱ፣ በህዝቡ ዘንድን ተስፋ ማጣት እና ስደት መንሰራፋቱ አጥኚዎቹ ይገልፃሉ።

በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተካሄደ የምክክር መድረክ
በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተካሄደ የምክክር መድረክምስል Million Haileslasse/DW

የትግራይ ፖለቲካዊ አስተዳደር የሚዳስስ እና የክልሉ ባለስልጣናት፣ የህወሓት እና ሌሎች ተቃዋሚ የፖለቲካ ድርጅቶች አመራሮች፣ ሲቪል እና የሃይማኖት ተቋማት የተሳተፉበት መድረክ ባለፉት ሁለት ቀናት በመቐለ ሲካሄድ የጥናት ውጥት ያቀረቡት የቀድሞ የኢትዮጵያ ደህንነት መስርያቤት ከፍተኛ አመራር የነበሩና እና የአሁኑ የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት አማካሪ ወልደስላሴ ወልደሚካኤል በትግራይ ያለው ዘርፈ ብዙ ችግር መነሻው ስርዓታዊ ብልሹነት ነው ያሉ ሲሆን፣ ትግራይ የስርዓት ለውጥ በምትሻበት ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ሲሉ ተናግረዋል። ወልደስላሴ "ችግሩ ስርዓታዊ ችግር ነው። የሚያስፈልገን ደግሞ ስርዓታዊ ለውጥ ነው። ልንድን ከሆነ፣ ተወዳዳሪ ልንሆን ከሆነ፣ ሀይላችን ልናጠነክር ከሆነ፣ ያሉ ሁሉ ችግሮች ሊፈቱ፣ ሊቀየሩ የሚፈለግ ከሆነ የትግራይ ችግር ስርዓታዊ መሆኑ ብሔራዊ መግባባት ያስፈልገዋል ብለን ነው የምናምነው" ብለዋል።

በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተካሄደ የምክክር መድረክ
በትግራይ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ የተካሄደ የምክክር መድረክምስል Million Haileslasse/DW

የፖሊስ እና ፀጥታ ተቋማት መዳከም፣ የፍርድቤቶች ተአማኒነት ማጣት፣ መንግስታዊ አገልግሎት መደናቀፍ እና ሌሎች ምክንያቶች በትግራይ ህዝብ በመንግስት ያለው እምነት እንዲወርድ እንዳደረገው በመድረኩ ተገልጿል። በሌላ በኩል አስተያየታቸው የሰጡት የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ፥  "መለያችን ሆነው ይታወቁ የነበሩ ክብሮቻችን እና ባህሎቻችን አደጋ ላይ የወደቁበት፣ መንግስት እንደ መንግስት ስራ መስራት የሚያስችለው አቅም ያጣበት ሁኔታ ላይ እንገኛለን። ባለንበት ደረጃ ሆነን፣ የተገኘው የሰላም አጋጣሚ በሙሉእነት ለመጠቀም የሚያስችለን ዕድል ሳንጠቀም ቀርተን በርካታ ችግሮች ተደቅነውብን ይገኛሉ" ብለዋል።

በዚሁ በትግራይ ያለው ፖለቲካ ሁኔታ የዳሰሰ በርካቶችን ያሳተፈ መድረክ አስተያየታቸው የሰጡት የተቃዋሚው ፓርቲ ሳልሳይ ወያነ ትግራይ ሊቀመንበር አቶ አሉላ ሃይሉ፥ የክልሉ አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት ከመስራት ይልቅ፥ ችግሮች በመዘርዘር ተጠምዷል ሲሉ ወቅሰዋል። አቶ አሉላ "እኔ በጣም የሚያሳዝነኝ ነገር አለ። በትግራይ ችግርቹ ተዘርዝረው እየተነገሩ ያሉት፣ ችግሮቹ ሊፈቱ ስልጣን በያዙ ሰዎች ነው። ሐላፊነታችሁ ልትወጡ ይገባል" ብለዋል።
ሚልዮን ሃይለስላሴ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር