1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮንሶ፣የድርቅ መዘዝ

ረቡዕ፣ መጋቢት 20 2015

በ119 ትምህርት ቤቶች ከሚማሩ 73 ሺህ ተማሪዎች 13 ሺህ ያህሉ ካለፈዉ ጥር ወር ጀምሮ ትምህርታቸውን ማቋረጣቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ለዶቼ ቬለ DW አረጋግጧል

https://p.dw.com/p/4PRLm
Äthiopien Konsso | Wassermangel
ምስል Konso Development Association

ተማሪዎች በምግብ እጦት ትምሕርት እያቋረጡ ነዉ

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በደቡብ ክልል በተከሰተው ድርቅ ወደ ሦስት ሚሊዮን የሚጠጉ ነዋሪዎች በምግብ ድጋፍ ማዕቀፍ ውስጥ ይገኛሉ ፡፡ በተለይም ከ227 ሺህ በላይ ነዋሪዎች ለምግብ እጥረት የተዳረጉበት የኮንሶ ዞን ድርቁ በመማር ማስተማር ሥራዎች ላይም አሉታዊ ተፅኖውን እያሳረፈ እንደሚገኝ የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል ፡፡

በዞኑ ሰገን ዙሪያ ወረዳ የቢርቢርሳ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት ደነቀው ገለቦ እና ገንታ ኦርካይዶ የድርቅ ክስተቱ እየበረታ በመምጣቱ ልጆቻቸው ከባለፈው ጥር ጀምሮ ከትምህርት ቤቶች መቅረታቸውን ነው ለዶቼ ቬለ DW  የተናገሩት ፡፡ የሏቸውን ስምንት ልጆች መመገብም ሆነ በቂ ምግብ ማቅረብ እንዳልቻሉ የጠቀሱት አቶ ገንታ “ ለመሥራትም ፣ ለማረስም ሆነ ለመማር መብላት ያስፈልጋል ፡፡ በባዶ ሆዳቸው ትምህርት ቤት መሄድ ባለመቻላቸው አሁን ላይ ትምህርታቸውን አቋርጠው አቤት  ለመዋል ተገደዋል “ ብለዋል ፡፡

Äthiopien Konsso | Wassermangel
ምስል Konso Development Association

በኮንሶ ዞን በሚገኙ 119 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 73 ሺህ ተማሪዎች  ትምህርታቸውን ሲከታተሉ መቆየታቸውን የዞኑ ትምህርት መምሪያ ሃላፊ አቶ ኩሴ ጭሎ ይናገራሉ ፡፡ ያም ሆኖ የድርቅ ክስተቱ ካስከተለው የምግብ ችግር ጋር በተያያዘ ከባለፈው ጥር ወዲህ ብቻ 13 ሺህ ተማሪዎች ትምህርታቸውን መቋረጣቸውን ነው ለዶቼ ቬለ DW ያረጋገጡት ፡፡

ትምህርት ላቋረጡ ተማሪዎች የምገባ ሥረዓት በማዘጋጀት ወደ ትምህርት ገበታ ለመመለስ ጥረት መደረጉን የጠቀሱት አቶ ኩሴ “ አሁን ላይ ከአሜሪካ የህጻናት አድን ድርጅት ባገኘነው ድጋፍ በ85 ትምህርት ቤቶች ላይ የምግብ ድጋፍ እያደርግን እንገኛለን ፡፡ በዚህም ወደ 4ሺህ 323 ተማሪዎችን ለመመለስ ችለናል ፡፡ ሌሎች 8ሺህ 640 ተማሪዎች ግን  እስከአሁን አልተመለሱም ፡፡ ይህ የሆነው በቂ የምግብ አቅርቦት ባለመኖሩ ነው  ፡፡ በቀጣይ በተቀሩት ትምህርት ቤቶች የምግባ ሥረዓት እንዲጀመር ለማድረግ የደቡብ ክልል ፣ የፌዴራል መንግስትንና የረድኤት ድርጅቶችን ደጋፍ በመጠየቅ ምላሽ እየተጠበቅን እንገኛለን “ ብለዋል ፡፡

ዶቼ ቬለ DW በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው በደቡብ ክልል ትምህርት ቢሮ የመማር ማስተማርና ምዝና ዘርፍ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ገለቦ ጎልቶሞ በክልሉ ኮንሶን ጨምሮ ደቡብ ዞሞ ፣ ጋሞ ፣ ጎፋ ዞኖችና እንዲሁም አማሮ ፣ ቡርጂ  ፣ አሌና ደራሼ ልዩ ወረዳዎች ድርቁ በትምህርት ሥራ ላይ ተጸፅኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ተናግረዋል ፡፡በእነኝሁ ዞኖችና ልዩ ወረዳች በሚገኙ 461 ትምህርት ቤቶች ላይ  ለ231 ሺህ ተማሪዎች ምግባ ሥረዓት እየተከናወነ እንደሚገኝ  ምክትል ቢሮ ሃላፊው አስረድተዋል  ፡፡

Äthiopien Bureau of Education
ምስል Shewangizaw Wegayoh/DW

አሁን እየተካሄደ ያለው የምግባ ሥራ ችግሩን ሙሉ በሙሉ እንደማይቀርፍ የጠቀሱት ምክትል ቢሮ ሃላፊው “ በቀሪ 336 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚገኙ 289 ሺህ ተማሪዎች የቅርብ ክትትል እንደሚያስፈልጋቸው በጥናት ለይተናል ፡፡ በአሁኑወቅትም ቢሮው  ለእነኝሁ ተማሪዎች ተጨማሪ የምግብ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስፈልጉ ሀብቶችን እያፈላለገ ይገኛል “ ብለዋል፡፡

ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ነጋሽ መሐመድ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር