1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮሬ ዞን በልጃገረዶች ጠለፋ ተሳትፈዋል የተባሉ 12 ሰዎች በፖሊስ መያዛቸው

ሰኞ፣ ግንቦት 26 2016

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን እየተባባሰ መጥቷል የተባለውን የሴት ልጆች ጠለፋ ለመከላከል ህዝባዊ ንቅናቄ መጀመሩን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታወቁ ፡፡ በዞኑ አንድ ወረዳ ብቻ ሰሞኑን በተደረገ እንቅስቃሴ ሁለት ተማሪዎች ከጠለፋ ነጻ ሲወጡ በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉ 12 ሰዎች ደግሞ በፖሊስ ተይዘዋል፡፡

https://p.dw.com/p/4gaDg
ኮሬ ዞን ገጠር ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ
ኮሬ ዞን ገጠር ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ ምስል Kore Zone communication office

ኮሬ ዞን በልጃገረዶች ጠለፋ ተሳትፈዋል የተባሉ 12 ሰዎች በፖሊስ መያዛቸው

ኮሬ ዞን በልጃገረዶች ጠለፋ ተሳትፈዋል የተባሉ 12 ሰዎች በፖሊስ መያዛቸው
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ኮሬ ዞን እየተባባሰ መጥቷል የተባለውን የሴት ልጆች ጠለፋ ለመከላከል ህዝባዊ ንቅናቄ መጀመሩን የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታወቁ ፡፡ በዞኑ አንድ ወረዳ ብቻ ሰሞኑን በተደረገ እንቅስቃሴ ሁለት ተማሪዎች ከጠለፋ ነጻ ሲወጡ በድርጊቱ ተሳትፈዋል የተባሉ 12 ሰዎች ደግሞ በፖሊስ መያዛቸው ተገልጿል ፡፡  ሰዎቹ በቁጥጥር ሥር ሊውሉ የቻሉት ሴት ተማሪዎችን በመጥለፋቸውና  ተጠላፊዎቹን በቤታቸው በመደበቅ በመተባበራቸው ነው ተብሏል ፡፡
 
የጠላፊዎች እሥር በኮሬ ዞን
በኮሬ ዞን በአዳጊ ሴት ተማሪዎች ላይ የሚፈጸመው የጠለፋ ተግባር እየተባባሰ መምጣቱ ከተገለጸ ወዲህ የዞኑ መስተዳድር ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት የጀመረ ይመስላል ፡፡ በተለይም የሴት ተማሪዎች ጠለፋ በዞንና በወረዳ ምክር ቤት ጉባዔዎች ላይ ከተነሳ ከባለፈው መጋቢት ወዲህ የአካባቢው የህግ አካላት ለጥቃቱ ትኩረት እንዲሰጡት ምክንያት ሆኗል ነው የሚባለው ፡፡  አንዳንድ የዞኑ ወረዳዎች የጠለፋ ጥቃቱን ለመቀልበስ ያስችላል ያሉትን የህዝብ ንቅናቄ በመፍጠር ወደ ሥራ መግባታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ።


የተጠላፊዎች ነጻ መውጣት እና የጠላፊዎች እሥር
በኮሬ ዞን ከሚገኙ ወረዳዎች መካከል የጠለፋ ተግባር ጎልቶ ከሚስተዋልባቸው አካባቢዎች አንዱ የጎርካ ወረዳ ነው ፡፡ በወረዳ በኀሃዝ የተደገፈ መረጃ ባይኖርም ከያዝነው ዓመት መግቢያ ጀምሮ በርካታ አዳጊ ሴቶች በጠላፊዎች መወሰዳቸው ዶቼ ቬለ ከአካባቢው ያሰባሰባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ ፡፡ ዛሬም ድረስ በጠላፊዎች እጅ የሚገኙ አዳጊ ተማሪዎችን ከጠላፊዎች የማስለቀቅ ሥራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የጎርካ ወረዳ አስታውቋል፡፡ 
በጠለፋ ውስጥ ከሚገኙት ከእነኝሁ አዳጊ ሴቶች መካከል ሰሞኑን በተደረገ ጥረት ሁለቱን  ነጻ ማድረግ መቻሉን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የጎርካ የወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አገኘው በቀለ “  በተጨማሪም ከጠለፋው ጋር በቀጥታና በተዘዋዋሪ ተሳትፈዋል የተባሉ  12 ሰዎች በህግ ቁጥጥር ሥር ማዋል ተችሏል ፡፡ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ሰዎች በቀጥታ ተማሪዎቹን የጠለፉና ተጠላፊዎቹን ተቀብለው ደብቀዋል የተባሉ የጠላፊ ቤተሰቦች ጭምር ናቸው ፡፡ ተማሪዎቹን ለማስለቀቅና ጠላፊዎቹንና ተባባሪዎችን በህግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል የተቻለው ወረዳው ሰሞኑን በጀመረው ህዝባዊ ንቅናቄ አማካኝነት ነው “ ብለዋል፡፡


የቀሪ ተጠላፊዎች ጉዳይ
የኮሬ ዞን ፍትህ መምሪያ የጠለፋ ጥቃት ያደረሱ ግለሰቦች ለህግ እንዲቀርቡ ለወረዳዎች በደብዳቤ ትዕዛዝ መስጠቱን ተከትሎ መሻሻሎች መታየት መጀመራቸው የጥቃቱ ሰለባዎች ተናግረዋል ፡፡  “ በእርግጥ ጅምሩ ጥሩ ቢሆንም አሁንም በርካታ ልጆች በጠላፊዎች እጅ እንደሚገኙ የጠቀሱት አንድ የጥቃቱ ሰለባ የሆነች ታዳጊ አባት “ በህግ አካላት ጥረት ከጠላፋ ነጻ የወጡና በወንጀሉ የተያዙ ሰዎችን ማየታችን መልካም ነው  ፡፡ ይህ ግን ሁሉም ቦታ ደርሷል ማለት አይደለም ፡፡ ለምሳሌ የእኔ ልጅ ከተጣለፊዎች እገታ ወጥታ ከቤተሰብ ጋር የተቀላቀለችው በራሷ ጥረት ነው ፡፡ ጠላፊዎቹ ሌሊት ተኝተው ሳሉ ነው ጠፍታ የመጣችው ፡፡ አሁንም በጠለፋ ተይዘው የሚገኙ ልጆችን ማስለቀቅና የድርጊቱን ፈጻሚዎችን በመያዝ ረገድ ገና ብዙ ይቀራል “ ብለዋል ፡፡


የማህበራዊ መገናኛዎች ተፅእኖ
የጎርካ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አገኘው የተጠላፊ ተማሪዎ ቤተሰቦች እያቀረቡ በሚገኘው ሀሳብ እንደሚስማሙ ይናገራሉ ፡፡ አሁን ላይ በጠላፊዎች እጅ የሚገኙ ቀሪ ተማሪዎችን ለማስለቀቅ ቀጣይ ጥረቶች በመደረግ ላይ እንደሚገኝ  የጠቀሱት ዋና አስተዳዳሪው አቶ አገኘው  “  ነገር ግን አስቀድመው በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚለቀቁ መረጃዎች የክትትል ሥራውን እያደናቀፉብን ይገኛሉ ፡፡ ድርጊቱ ሲፈጸም ከቤተሰብ በሚመጣ ጥቆማ ጠላፊዎችን ወዲያው ተከታትሎ መያዝ ይቻል ነበር ፡፡ ነገር ግን የጠላፊዎቹ ማንነትና ልጆቹን ይዘው የሄዱበት ቦታ ጭምር  በማህበራዊ ሚዲያ ሥለሚለቀቅ ተፈላጊዎቹ አድራሻቸውን እንዲቀይሩና አንዳንዶቹም አገር እንዲቀይሩ አድርጓል ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ማህበረሰቡ መረጃዎችን ለህግ አካላት ብቻ በመስጠት ውጤቱን እንዲጠብቅ  ጥሪ እናቀርባለን “ ብለዋል ፡፡ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል  ኮሬ ዞን በአዳጊ ሴት ተማሪዎች ላይ በሚፈጸም የጠለፋ ተግባር የተነሳ ወላጆች ልጆቻቸውን ወደ ትምህርት ቤት ለመላክ እንደተቸገሩ መግለጻቸውን ዶቼ ቬለ ቀደምሲል መዘገቡ ይታወሳል፡፡


ሸዋንግዛው ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሰ