1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚሰሜን አሜሪካ

ካማላ ሐሪስ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ቢመረጡ ምን አይነት ኤኮኖሚያዊ እንድምታ ይኖረዋል?

ረቡዕ፣ ሐምሌ 17 2016

ጆ ባይደን ከፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ራሳቸውን ሲያገልሉ ዴሞክራቶች የመነቃቃት አዝማሚያ አሳይተዋል። በንግድ ሥራ የተሰማሩ ኩባንያዎች በአንጻሩ ካማላ ሐሪስ የመጀመሪያዋ ሴት የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ቢመረጡ በኤኮኖሚው ረገድ ምን ለውጥ እንደሚኖር እርግጠኞች አይደሉም። በርካታ ኩባንያዎች ግብር ለመቀነስ ቃል የገቡት ዶናልድ ትራምፕ እንዲመረጡ ይደግፋሉ።

https://p.dw.com/p/4igiD
ካማላ ሐሪስ በዊስኮዚን
ካማላ ሐሪስ በአሜሪካ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ቁልፍ ሚና በሚኖራት ዊስኮዚን ከ3000 ገደማ ደጋፊዎቻቸው ፊት ባደረጉት ንግግር ተፎካካሪያቸው ዶናልድ ትራምፕን ተችተዋል። ምስል Vincent Alban/REUTERS

ካማላ ሐሪስ የአሜሪካ ፕሬዝደንት ሆነው ቢመረጡ ምን አይነት ኤኮኖሚያዊ እንድምታ ይኖረዋል?

ከአንድ ሣምንት በፊት ዶናልድ ትራምፕ በጥቅምት 2017 መጨረሻ የሚካሔደውን ምርጫ አሸንፈው ወደ ዋይት ሐውስ የመመለሳቸው ጉዳይ የተቆረጠ ይመስል ነበር። ነገር ግን እሁድ ዕለት ጆ ባይደን ራሳቸውን አግልለው የ59 ዓመቷ ካማላ ሐሪስ የዴሞክራቶቹ እጩ እንዲሆኑ ቡራኬ በመስጠት የአሜሪካ ፕሬዝደንት ምርጫን ወለል አድርገው ለውድድር ከፍተውታል።

ካማላ ሐሪስ በምረጡኝ ዘመቻው ነፍስ ዘርተውለት በነሐሴ ወር በቺካጎ በሚካሔደው የዴሞክራቲክ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባኤ በይፋ እጩ ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። ሐሪስ ገና ካሁኑ ለምረጡኝ ዘመቻቸው የሚያደርጉት ገንዘብ የማሰባሰብ ዘመቻ ከፍተኛ ዕድገት አሳይቷል። ከባይደን ውሳኔ በኋላ ሐሪስ 81 ሚሊዮን ዶላር (74.4 ሚሊዮን ዩሮ) በመጀመሪያዎቹ 24 ሰዓታት አሰባስበዋል።

ጉዳዩ የድምጽ ሰጪዎችን፣ ለጋሾች እና ፖለቲከኞችን ትኩረት ብቻ አይደለም የሳበው። የአሜሪካ እና በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ቢዝነሶች ይኸ ለውጥ ምን እንደሚያስከትል ልብ ብለው እያጤኑ ነው። ኩባንያዎች ከማይፈልጓቸው ጉዳዮች አንዱ የእርግጠኝነት ማጣት ነው። ባይደን ራሳቸውን ለማግለል ያሳለፉት ውሳኔ የተሰማቸውን የእርግጠኝነት እጦት በከፊል አስወግዷል። ሙሉ በሙሉ ግን አይደለም።

“አሜሪካ ትቅደም” እና ዴሞክራቶቹ

ለአሜሪካ እና ለሀገሪቱ ምጣኔ ሐብት የባይደን ውሳኔ በጎርጎሮሳዊው 2025 አዲስ ፕሬዝደንት እንደሚመረጥ ማረጋገጫ ሰጥቷል። በባይደን እና በሐሪስ መካከል ያለው ልዩነት ግን ለመለየት ከባድ ነው።

ካማላ ሐሪስ እና አያታቸው ኢሪስ ፊኔጋን
የዘር ሐረጋቸው ከጃማይካ እና ከሕንድ ከሚመዘዝ ቤተሰቦች የተወለዱት ካማላ ሐሪስ ጥቁር እና ሴት መሆናቸው በፕሬዝደንትነት ለመመረጥ ቢጠቅማቸውም በወግ አጥባቂዎች ዘንድ ተቀባይነት የሚያስገኝላቸው ላይሆን ይችላል። ምስል Avalon/Photoshot/picture alliance

“ሐሪስ ከባይደን የበለጠ ተራማጅ የመሆን አዝማሚያ አላቸው። ይሁንና በኤኮኖሚው ረገድ ትልቅ ለውጥ ይመጣል የሚል ዕምነት የለኝም” ሲሉ በሐሪስበርግ የሚገኘው ፔንሲልቫኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ፖሊሲ እና አስተዳደር ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዳን ማሊሰን ይናገራሉ።

“ሁለቱም ለሠራተኛው መደብ ጥብቅና የሚቆሙ ናቸው። ሁለቱም ወላጆች በወሊድ ወቅት የሚሰጣቸው እረፍት እንዲጨምር ይደግፋሉ። ሁለቱም እንደ ሜዲክኤይድ፣ ሜዲኬር እና ሶሻል ሴኪዩሪቲ ያሉ የማኅበራዊ ጥበቃ ፖሊሲዎችን ይደግፋሉ” በማለት ተመሳስሏቸውን ያብራራሉ።

በአሁኑ ወቅት ለበርካታ የቢዝነስ መሪዎች ካማላ ሐሪስ እና የዴሞክራቲክ ፓርቲው አቋም ባለፉት ዓመታት ከታየው የመለወጥ ዕድሉ አነስተኛ በመሆኑ እምብዛም አያሳስባቸውም። ይልቅ የሚያሳስባቸው ካማላ ሐሪስ ካሸነፉ ሊያቆሙት የሚችሉት የዶናልድ ትራምፕ ፖሊሲ ነው።

የዶናልድ ትራምፕ ትልቁ ዓላማ “አሜሪካ ትቅደም” በሚል መርኅ የሚያራምዱትን አጀንዳ ማደስ ነው። በድንበር እና የፈላሲያን ጉዳይ ላይ ከሚያሰሙት የከፋ ንግግር ባሻገር ትራምፕ አሜሪካ ከውጭ በምትሸምታቸው ሸቀጦች ላይ 10 በመቶ ቀረጥ ለመጣል ሐሳብ አቅርበዋል። የቀድሞው ፕሬዝደንት ከቻይና ወደ አሜሪካ የሚገቡ ሁሉም ዕቃዎች ላይ 60 በመቶ ቀረጥ መጣል እንደሚፈልጉ ተናግረዋል።

ባይደን ከዚህ ቀደም ዶናልድ ትራምፕ ሥልጣን ላይ እያሉ የጣሏቸውን ቀረጦች ባሉበት እንዲቆዩ አድርገው እንዲያውም ተጨማሪ ገደቦች ቢያኖሩም ሁሉም በተመረጡ የኢንዱስትሪ ዘርፎች ላይ ያነጣጠሩ ናቸው። በሁሉም ሸቀጦች ላይ በጅምላ የሚጣል ቀረጥ ውድድርን በማዳከም የኑሮ ውድነት የበረታባቸው አሜሪካውያን ላይ የዋጋ ግሽበት ያስከትላል። የዋጋ ጭማሪ በተራው የዋጋ ንረትን በማባባስ የወለድ ምጣኔ ከፍተኛ ሆኖ እንዲቆይ የሚያደርግ ነው።

ዶናልድ ትራምፕ እና ጄድ ቫንስ
ዶናልድ ትራምፕ በፕሬዝደንትነት ጄድ ቫንስ በምክትል ፕሬዝደንትነት ለማስመረጥ የተዘጋጀው የዴሞክራቶች ማኒፌስቶ ለነዳጅ አምራች ኢንዱስትሪው የተዘጋጁ የቁጥጥር ሕግጋትን ለማላላት ቃል ገብቷል።ምስል Carlos Osorio/AP Photo/picture alliance

ይኸ እና ዓለም አቀፍ የንግድ ጦርነት ሊፈጠር ይችላል የሚል ፍርሐት ብዙ የቢዝነስ ሞዴሎችን በአፍጢማቸው የደፋ ሲሆን በርካታ ኩባንያዎችም ትራምፕ አሸንፈው ፈቃዳቸውን ቢጭኑ እንዴት ሥራቸውን እንደሚያከናውኑ ማሰላሰል ጀምረዋል። እነዚህ ኩባንያዎች በተለይም በቻይና የሚገኙ ካማላ ሐሪስ በይፋ እጩ ሆነው ይቀርባሉ ተብሎ ስለሚጠበቅ እና ዴሞክራቶችን ሊያነሳሳ ስለሚችል ለጊዜው ተንፈስ ማለት ይችላሉ።

የተወሰኑ የአሜሪካ ኩባንያዎች በተለይም የተሽከርካሪ አምራቾች፣ በኃይል ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት እና ክሪፕቶከረንሲዎች ዴሞክራቶች በሚኖራቸው የተሻለ የማሸነፍ ዕድል እምብዛም ደስተኛ የሚሆኑ አይደሉም። በሪፐብሊካን ፓርቲ የምርጫ ማኒፌስቶ ኩባንያዎቹ ከፍ ያለ ቦታ የተሰጣቸው ሲሆን የትራምፕ የማሸነፍ ዕድል ይጠናከራል የሚል ተስፋ ነበራቸው።

የፓርቲው ሠነድ ለነዳጅ አምራች ኢንዱስትሪው የተዘጋጁ የቁጥጥር ሕግጋትን ለማላላት ቃል ገብቷል። ሪፐብሊካኖች ከዚህ በተጨማሪ “ሕገ-ወጥ እና አሜሪካዊ ያልሆነ” ያሉትን “በክሪፕቶ ላይ በዴሞክራቶች የሚደረግን ጥብቅ ቁጥጥር” እንደሚያቆሙ ሠነዱ ያትታል። ሪፐብሊካኖቹ ለዲጂታል የመገበያያ ገንዘብ ማዕከላዊ ባንክ ማቋቋምን እንደሚቃወሙም በሰነዱ አስፍረዋል።

ባለወረቶች አሁን ፖለቲካዊ ስሌቶቻቸውን እና ከፍተኛ ትርፍ የማግኘት ተስፋቸውን እያስተካከሉ ሊሆን ይችላል። በታዳሽ ኃይል ዘርፍ የተሰማሩት እና በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች አምራቾች ሐሪስ አሸንፈው የነበረው እንዲቀልጥ ተስፋ ሊያደርጉ ይችላሉ። ይሁንና በንድፈ-ሐሳብ ደረጃም ቢሆን በጥቂት ወራት ውስጥ መሠረታዊ የፖሊሲ ለውጥ ሊኖር ይችላል።

የሐሪስ ኤኮኖሚ ምን ሊመስል ይችላል?

ካማላ ሐሪስ ስለ ኤኮኖሚውም ሆነ እንዴት ሊያካሒዱት እንዳቀዱ ብዙ ያሉት ነገር የለም። በካሊፎርኒያ ግዛት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሳሉም ሆነ በምክትል ፕሬዝደንትነት በሠሩባቸው ዓመታት በኤኮኖሚ ረገድ ያላቸውን አቋም መልሶ መፈተሽ ጥቂት መረጃ ሊሰጥ ይችላል።  

የአሜሪካ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን እና ምክትል ፕሬዝደንት ካማላ ሐሪስ
ካሚላ ሐሪስ አብዛኞቹን የጆ ባይደን አስተዳደር የኤኮኖሚ ፖሊሲዎች ያስቀጥላሉ ተብሎ ቢጠበቅም ባለሙያዎች የራሳቸውን መንገድ መቀየድ እንደሚኖርባቸው ያምናሉ። ምስል Matt Kelley/AP Photo/picture alliance

እንደ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ሐሪስ በነዳጅ ኩባንያዎች እና በባንኮች ላይ ጥብቅ ነበሩ። በምክትል ፕሬዝደንትነታቸው ታዳሽ ኃይልን ማበረታታት፣ በኮቪድ ወረርሽ የተጎዳውን ኤኮኖሚ ለማነቃቃት የተዘጋጀውን ዕቅድ እና የዋጋ ግሽበት ለመቀነስ የተላለፈውን ውሳኔ ጨምሮ የጆ ባይደንን ትልልቅ ኤኮኖሚያዊ ዕቅዶች ደግፈዋል። ፕሬዝደንቱ በኤሌክትሪክ ለሚሰሩ ተሽከርካሪዎች፣ ቅንጡ ስልኮች እና ኮምፒውተሮችን ለመሳሰሉ ቁሳቁሶች አስፈላጊ የሆኑት ቺፕሶች እና ሰሚኮንዳክተሮች ምርት፣ ምርምር እና ልማት በቢሊዮን ዶላሮች ኢንቨስት በማድረግ ለማበረታታት ያሳለፉት ድንጋጌ ሐሪስ ከደገፏቸው መካከል ናቸው።

ካማላ ሐሪስ ወደ አሜሪካ በሚገቡ ሸቀጦች ላይ በጅምላ ቀረጥ መጣልን ተቃውመው ቢሟገቱም አሁን በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት እንደሚያደርገው ሁሉ ቻይናን በዐይነ ቁራኛ ሊመለከቱ ይችላሉ። ሐሳቦቻቸው ምንም ይሁኑ ምን ሐሪስ ለአሜሪካ ኤኮኖሚያላቸውን ርዕይ በፍጥነት ለመራጮች ማሳየት አለባቸው። በኤኮኖሚው ረገድ ሐሪስ የራሳቸው ሐሳቦች አሏቸው ወይስ ባይደን ቁጥር 2 ይሆናሉ? ይኸ ብርቱ ጥያቄ ነው።

ሐሪስ ከሚገጥሟቸው ተግዳሮቶች አንዱ አባል የሆኑበት የጆ ባይደን አስተዳደር ያከናወናቸውን ሥራዎች እየተከላከሉ የራሳቸውን ቦታ ማስተካከል እንደሚሆን በፔንሲልቫኒያ ስቴት ዩኒቨርሲቲ የፐብሊክ ፖሊሲ እና አስተዳደር ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት ዳን ማሊሰን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ማሊሰን እንደሚሉት ይኸ ደግሞ ኤኮኖሚውን ይጨምራል። ኤኮኖሚው ቀውስ ውስጥ ሳይገባ የዋጋ ግሽበትን መቀነስ እና የሥራ ዕድሎች መፍጠር እንደሚችሉ መራጮችን ማሳመን ከቻሉ ካማላ ሐሪስ የመጀመሪያዋ የዩናይትድ ስቴትስ ሴት ፕሬዝደንት የመሆን ዕድል አላቸው።

ቲሞቲ ሩክስ/እሸቴ በቀለ