ከጋዛ እስከ ዩክሬን ጦርነት ያልተለየዉ ዓለም ከአዉሽቪትስ ምን ተማረ?
ሰኞ፣ ጥር 19 2017
የሶቭየት ሕብረት ቀዩ ጦር የአዉሽቪትስ ማጎሪያና መፍጂያ ጣቢያ ከጀርመን ናዚ ጦር እጅ ነፃ ያወጣበት 80ኛ ዓመት ዛሬ እየተዘከረ ነዉ።በአብዛኛዉ የሁዲዎች በግፍና በገፍ የተጨፈጨፉበት ማጎሪያ ጣቢያ ነፃ የወጣበትን ዕለት ዓለም ሲዘክር ዛሬ፣ የያኔዎቹ ነፃ አዉጪዎች ሩሲያና ዩክሬን የገጠሙት ጦርነት የሚያደርሰዉን ጥፋት እየታዘበ፣የእስራኤልና የሒዝቡላሕ፣ የእስራኤልና የሐማስ ለንቋሳ የተኩስ አቁም ዉል ዉጤት-እንቅፋቶችን እያስተነተነ ነዉ።እርግጥ ነዉ ጋዛዎች፣ ደቡብ ሊባኖሶች፣ ሰሜን እስራኤሎች ከሞት፣ቁስለት፣ ስደት-ጥፋት፣ ዉድመት፣ መሸማቀቅ ተንፈስ ብለዋል።ዳር ይዘልቅ ይሆን? ላፍታ አብረን እንጠይቅ።
WDR-በሚል የጀርመንኛ ምሕፃረ ቃል የሚጠራዉ ማሠራጪያ ጣቢያ ጋዜጠኛ «አዉሽቪትስን ጎብኝቼ አላዉቅም አለች ዛሬ በራዲዮ ዝግጅቷ» ምክንያቱም «ያ ሁሉ ሰዉ ያለቀበትን ሥፍራ ማየት አፈራለሁ።»
የታሪክ አዋቂዎች እንደሚገምቱት በአምስት ዓመት ዉስጥ 1.1 ሚሊዮን ሕዝብ ቃላት ለመግለፅ አቅም በሚያጡበት ግርፋት፣ ረሐብ፣ ስቃይ፣ በእሳት እየተንጨረጨረ ያለቀበት ሥፍራ ከ80 ዓመት በኋላ እንኳን ያዉም ለማየት ጋዜጠኛዋ እንዳለችዉ ያስፈራል።አሜሪካኖች የመሠረቱት የአዉሽቪትስ መታሰቢያ ድርጅት እንደሚለዉ ግን ያለፈዉን ግፍ ከመዘከር፣ ከመፍራት እኩል አስተምሕሮቱም አስፈላጊ ነዉ።የአዉሽቪትስ (ፀረ) ጥላቻ፣ ፅንፈኝነትና አክራሪነት ማዕከል የበላይ ማርክ ዋላስ እንደሚሉት ሕልማቸዉ አስተምሕሮቱ ነዉ።
«የኔም ሆነ የሁሉም ባልደረቦቼ ሕልም እዚሕ የሚመጣ ማንኛዉም ጎብኚ፣ማንኛዉም ወገን፣ የትኛዉም ምሑር የትም ሥፍራ የሚከሰቱ ፅንፈኝነትና ፀረ-ሴማዊነትን ለመዋጋት እርምጃ እንዲወስዱ ነዉ።»
ዓለም እብሪት፣ማንአሕሎኝነት፣ ጥላቻ፣ፅንፈኝነት፣ፀረ-ሴማዊነትን እየተዋጋች ይሆን? መልሱ በርግጥ እንደየተመልካቹ አይ-አዎ ነዉ።ያን የዘግናኝ ግፍ ማዕከል ከናዚዎች ነፃ ያወጣችዉ የሶቭየት ሕብረት ሶሻሊስት ሪፐብሊኮች ግን ተበታትነዉ ሁለቱ ትላልቅ ሪፐብሊኮች ሩሲያና ዩክሬን ከመጠላላትም አልፈዉ እየተጋደሉ ነዉ።
በአይሁድ ላይ የተፈፀመዉን ግፍ ከማንም በላይ የምትዘክረዉ እስራኤልም ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ከጎረቤቶቿ ጋር ከመቃቃር፣ መጠላላት፣ መወነጃጀልም በላይ በማያበራ ጦርነት እንደተዘፈቀች ነዉ።ለእስካሁኑ የመጨረሻዉ የፍልስጤሞችን ትንሽ ግዛት ጋዛንና ደቡባዊ ሊባኖስን ያወደመዉ እስራኤልን የሠጋዉ ጦርነት ነዉ።
መነሻዉ እስራኤል፣ ዩናይትድ ስቴትስና የአዉሮጳ ሕብረትን ጨምሮ 40 መንግሥታት በአሸባሪነት የፈረጁት የፍልስጤም ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሐማስ አምና መስከረም ደቡባዊ እስራኤልን ማጥቃቱ ነዉ።በጥቃቱ ከ1130 በላይ እስራኤላዉያን ተገድለዋል፤ 240 ያክል ታግተዋል።ጥቃቱ የቀድሞዉ የእስራኤል ምክር ቤት (ክነሴት) ምክትል አፈ-ጉባኤ ንጉሴ ሽለሞ ሞላ እንደሚሉት በእስራኤል ታሪክ ደርሶ አያዉቅም።
«ሐማሶች ቅድመ ዝግጅት አድርገዉ፣ የእስራኤል ደሕንነቶች፣ የእስራኤል መከላከያ፣ የእስራኤል መንግስት እነሱን በመናቅ፣ አያደርጉትም፣ አይደፍሩንም በማለት የደረሰዉ ዉድቀት ለእስራኤል ማሕበረሰብ ከፍተኛ ትራዉማ ነዉ።»
ጥቃቱን ለመበቀል እስራኤል ጋዛ ሰርጥ ላይ የከፈተችዉ ድብደባ ባንፃሩ የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት እንዳሉት ያቺን ትንሽ ሰርጥ ወደ ጥፋት ሥፍራነት ቀይሯታል።
«መላዉን የጋዛ ሰርጥን እያየሁ ነዉ።ሁሉም ነገር ተመሰቃቅሏል።በእዉነት ምስቅልቅል ያለ ነዉ።ሁሉም የየፈረሰበት ሥፍራ ነዉ።ሰዎችም እየሞቱ ነዉ።»
የፍልስጤም የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን እንደገመተዉ ትንሺቱ ሰርጥ 85 ሺሕ ቶን ፈንጂ እየዘነበባት አስከሬን ስታመርት፣ ቁስለኛ ስታሰላ፣ ፍርክስካሽ ስትከምር 15 ወራት አስቆጥራለች።መኖሪያ፣ ትምሕርት፣ መስሪያ ቤቶች፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ የስደተኛ መጠለያዎች፣ መሳጂዶች፣ የንግድ፣ የዉሐ፣ የኤሌክትሪክ፣ የስልክ ተቋማት ወድመባታል።
የፍልስጤም ባለሥልጣናት እንዳሉት ከ47 ሺሕ በላይ ሕዝብ አልቋል።ከ11 ሺሕ የሚበልጥ ሕዝብ አንድም ፍርስራሽ ተጭኖታል፣ አለይም የደረሰበት አይታወቅም።ከ110 ሺሕ በላይ ሕዝብ ቆስሏል።2.3 ሚሊዮን ከሚገመተዉ ሕዝቧ አብዛኛዉ በረሐብ፣ በመድሐኒት፣ በመጠለያ እጦት ተሰቃይቷል።ከሁለት ጊዜ በላይ ተፈናቅናቅሏል።
ኢትዮጵያዊ-እስራኤላዊዉ የቀድሞ ፖለቲከኛ ንጉሴ ሽለሞ ሞላ እንደሚሉት ጋዛ ወድማለች፣ ሕዝቧም ተሰቃይቷል።ተጠያቂዉ ግን ሐማስ ነዉ ይላሉ።
የጋዛ ሕዝብ ዋጋ ከፍሏል።የጋዛ ሕዝብ እየተሰቃየ ነዉ።የጋዛ ሕዝብ 75 ከመቶ ንብረቱ ወድሟል።ፈርሰዋል።---የሐማስ አሸባሪ ቡድን---»
በርግጥም እስራኤል ባለፉት 15 ወራት ዉስጥ ከኢስማኤል ሐኒየሕ እስከ መርዋን ኢሳ ያሉ የሐማስ፣ከሐሰን ነስረላሕ እስከ ታሌብ አብደላሕ ያሉ የሒዝቡላሕ መሪዎች፣ ቢያንስ 3 የኢራን ጄኔራሎችን ጭምር ገድላለች።
በጋዛዉ እልቂት መሐል እስራኤል በኃይል ወደያዘችዉ የምዕራባዊ ወንዝ ዳርቻ ጦሯን አዝምታ ከ800 በላይ ፍልስጤማዉያንን ገድላለች።ዘገቦች እንደጠቆሙት እስራኤል ራሷም ከመስከረም 26፣2016 ወዲሕ ከ1800 በላይ ሲቢልና ወታደራዊ ዜጎችዋ ተገድለዉባታል።
የጋዛ መዘዝ የሊባኖሱን የሺዓ ደፈጣ ተዋጊ ቡድን ሒዝቡላሕን፣ የየመን ሁቲዎችን፣ የኢራቅ ደፈጣ ተዋጊዎችን፣ኢራንን፣ ዩናይትድ ስቴትስንና ተባባሪዎቻቸዉን በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ከዉጊያዉ ሞጅሯል።
የዓለም ሕግጋት፣ የተኩስ አቁም ስምምነቱ ትሩፋት
ዓለም በተለይ ምዕራባዉያን መንግሥታት ከሁለተኛዉ የዓለም ጦርነት ፍፃሜ ወዲሕ ብዙ የሚደሰኩሩለት የሰብአዊ መብት ጥበቃ፣ የሐኪሞች፣ የጋዘጠኞች፤ የርዳታ አቀባዮች ሕይወት የመሥራት ነፃነትና ደሕንነትን መና አስቀርቶታል።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ደንቦች፣ ዓለም አቀፍ ዉሎች፣ የዓለም ፍርድ ቤቶች ዉሳኔዎች የሚከበሩት ጉልበተኞች ሲፈልጓቸዉ ብቻ መሆኑን ጋዛ ባለፉት 15 ወራት በግልፅ አሳይታለች።
እስራኤልና ሐማስ ከ12 ቀን በፊት ያደረጉት ስምምነት የተመሰቃቀለዉን የዓለም ፖለቲካዊ-ሥርዓት ሕግና ደንብ ለማቃናት መጥቀም አለመጥቀሙ በርግጥ አይታወቅም።ትራምፕ «የተመሰቃቀለች» ላሏት ጋዛና ሕዝቧ ግን ላጭር ጊዜም ቢሆን እፎይታ ነዉ።ከ1989 (እግአ) ጀምሮ እስራኤል እስር ቤቶች ይማቅቁ ከነበሩ ፍልስጤማዉያን እስካሁን ለተለቀቁት ለ290ዉና ለቤተሰቦቻቸዉ ደስታ።
ከ470 ቀናት በላይ ጋዛ ዉስጥ ታግተዉ ከነበሩት እስራኤላዉን ቢያንስ እስካሁን ለተለቀቁትና ለቤተሰቦቻቸዉም ፌስታ ነዉ።
በሶስት ምዕራፍ የተከፈለዉ የጋዛዉ ተኩስ አቁም ዉል ዳር መዝለቅ አለመዝለቁ በግልፅ የሚታወቀዉ የመጀመሪያ የተባለዉ ምዕራፍ ከ30 ቀናት በኋላ ሲጠናቀቅ ነዉ።እስራኤልና ሒዝቡላሕ ከ60 ቀናት በፊት ያደረጉት የተኩስ አቁም ስምምነት መፅናት አለመፅናቱ ግን ዛሬም እያጠያየቀ ነዉ።
የሊባኖሱ ጣጣ
በስምምነቱ መሠረት የእስራኤል ጦር ከደቡብ ሊባኖስ መዉጣት አለበት።የሒዝቡላሕ ተዋጊዎች ደግሞ ሊታኒ ከተባለዉ ወንዝ ወደ ሰሜን ማፈግፈግ፣ በአዋሳኙ ድንበር የሊባኖስ መንግስት ጦር መስፈር፣ ።በጦርነቱ የተፈናቀለዉ የሊባኖስ ሕዝብም ወደየቀዉ መመለስ አለበት።ሁሉም ወገኖች የተባሉትን እንዲያደርጉ የተስማሙበት የ60 ቀናት ቀነ-ገደብ ትናንት አበቅቷል።ሁለቱ ጠላቶች አንዱንም ገቢር አላደረጉም።
የተፈናቀለዉ ሕዝብም ወደየቀየዉ አልተመለሰም።ለመለስ የሞከሩ ተፈናቃዮች እንደሚሉት የእስራኤል ጦር ተፈናቃዮቹን እየገደለ ነዉ።
«ጠላት ከግዛታችን አልወጣም እያለ ነዉ።እነሱ ባይወጡም እኛ ወደቀያችን መመለስ እንዳለብን ልናሳያቸዉ እንፈልጋለን።ባካባቢዉ ሥንደረስ የእስራኤል ድሮን ሁለት ቦቦች ጣሉብን።የመጀመሪያዉ አልጎዳንም ሁለተኛዉ ግን ጓደኛዬን ገደለዉ፣ እኔን እጄን አቆሰለኝ።»
ኢትዮጵያዊዉ-እስራኤላዊዉ የቀድሞ የእስራኤል የምክር ቤት ምክትል አፈጉባኤ ንጉሴ ሽለሞ ሞላም እስራኤል ደቡብ ሊባኖስ ዉስጥ ጥቃት መክፈቷን አረግጠዋል።ግን የምትጎዳዉ የሒዝቡላሕ ታጣቂዎችን ነዉ ባይናቸዉ።
«ሒዝቦላዎች ደግሞ ከደቡብ ሊባኖስ ወደ ሰሜን ተሰድዶ የነበረዉን ሕዝብ አብረዉ ሕዝብ መስለዉ ታጥቀዉ እየመጡ---እስራኤል እየጎዳች ነዉ።»
እስራኤልና ሒዝቡላሕ በገጠሙት ዉጊያ ከ3100 በላይ የሊባኖስ ዜጎች፣ በመቶ የሚቆጠሩ የእስራኤል ሰላማዊ ሰዎችና ወታደሮች ተገድለዋል።ሊባኖስ የሠፈሩ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ወታደሮች ቆስለዋል።በመቶ ሺሕ የሚገመቱ የሰሜን እስራኤልና የሊባኖስ ዜጎችን አፈናቅሏል።
የትራምፕ መፍትሔ፣ የሌላ ጦርነት ዝግጅት
የእስራኤል ሒዝቡላሕ፣ የእስራኤል ሐማስ ተኩስ አቁም ገቢር መሆን አለመሆኑ ሲያከራክር፣ ዘላቂ መፍትሔዉም እያነጋገረ ነዉ።የዉጪ ስደተኞችን ከዩናይትድ ስቴትስ የሚያባርሩት ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ግን የጋዛ ፍልስጤሞችን ወደ ግብፅና ዮርዳኖስ ማሰደድ መፍትሔ ነዉ ይላሉ።
የባይደን አስተዳደር ለእስራኤል እንዳይሰጥ ያገደዉን 2000 ፓዉንድ ቦምብ ለእስራኤል እንዲሰጥ ትራምፕ ወስነዋል።ኢራን ባንፃሩ «ጋዛ» ብላ የሰየመችዉን በርካታ ዘመናይ ሰዉ አልባ አዉሮፕላን (ድሮን) አስመርቃለች።
የእስራኤል መሪዎች አላማና ዉጤቱ
የእስራኤል መሪዎች የጋዛና የሊባኖስን ጦርነት ሲከፍቱ አራት አላማ እንደነበራቸዉ አስታዉቀዉ ነበር።ሐማስን ማጥፋት፤ ታጋቾችን ማስለቀቅ፣ ጋዛ ዉስጥ እስራኤልን የሚያሰጋ ኃይል እንዳይኖርና የእስራኤል ተፈናቃዮችን ወደየቀያቸዉ መመለስ።
ከአንዱ ስደተኛ መንደር ወደ ሌላዉ የሚፈናጠረዉ፣ ዋሻ-ለዋሻ-የሚሽ-ሎከሎከዉ ሐማስ መስከረም 29 2016 እስራኤልን ማጥቃት የቻለበት አቅም፣ ብልሐትና ሥልት እስካሁን ግልፅ መልስ እንዳላገኘ ሁሉ፣ የእስራኤል ገደብ የለሽ ጥቃት፣ድብደባና እመቃ የመሪዎቿን አላማ ከግብ ማድረስ-አለማድረሱ፣ ዓለም ከ80 ዓመት በፊት ከነበረዉ እብረት፣ጥላቻና ፅንፈኝነት መማር አለማመሩ እንዳጠያያቀ 15 ወር አለፈ።አዲስ ተኩስ አቁም።የአዲስ የዉጊያ ዝግጅት።ለዛሬ ይብቃን።
ነጋሽ መሐመድ
ፀሐይ ጫኔ