1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከኦሞ ወንዝ በተነሳዉ ጎርፍ ከ15 ሺህ በላይ ሰዉ ተፈናቀለ

ሰኞ፣ ነሐሴ 11 2012

በደቡብ ክልል ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ ከ15 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን አፈናቀለ። ከሁለት ሺህ የሚልቁ ተጨማሪ ሰዎች መውጫ በማጣት በውኃ ተከበው ይገኛሉ። በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀብራራው ተክሌ ዛሬ ለዶቼ ቬሌ «DW» እንደገለጹት ጎርፉ ነዋሪዎችን እያፈናቀለ የሚገኘው ከባለፈው ሐሙስ ጀምሮ ነው።

https://p.dw.com/p/3h5fY
Äthiopien SNNPR Region Omo Fluß Überschwemmungen
ምስል DW/S. Wegayehu

የኦሞ ወንዝ ከ3ዐ ዓመታት ወዲህ ሲሞላ ለመጀመርያ ጊዜ ነዉ

በደቡብ ክልል ዳሰነች ወረዳ የኦሞ ወንዝ ሞልቶ ባስከተለው ጎርፍ ከ15 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን አፈናቀለ። ከሁለት ሺህ የሚልቁ ተጨማሪ ሰዎች መውጫ በማጣት በውኃ ተከበው እንደሚገኙ የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታወቀዋል። በደቡብ ኦሞ ዞን የዳሰነች ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ቀብራራው ተክሌ ዛሬ ለዶቼ ቬሌ «DW» እንደገለጹት ጉርፉ ነዋሪዎችን እያፈናቀለ የሚገኘው ከባለፈው ሐሙስ ጀምሮ ነው።

ዋና አስተዳዳሪው በማያያዝም «የኦሞ ወንዝ ከመጠን በላይ በመሙላት ለወትሮው ይፈስበት የነበረውን ጎርጅ ሰብሮ ግራና ቀኝ በመውጣት ነዋሪዎች ወደሚገኙባቸው ቀበሌያት እየገባ ይገኛል። አሁን ባለው ሁኔታ በወረዳው ከሚገኙት 4ዐ ቀበሌያት 28ቱ ሙሉ በሙሉ በውኃ ተጥለቅልቀዋል። እስከአሁን ከ15 ሺህ በላይ ሰዎችንና 97 ሺ የሚጠጉ የቤት እንስሳት ወደ ደረቃማ መሬቶች አጓጉዘናል። ይሁን እንጂ 2ሺህ የሚጠጉ ነዋሪዎች አሁንም በውኃ ተከበው ይገኛሉ። እነኚህ ነዋሪዎች የሚገኙባቸው ቀበሌያት ከወረዳው ማዕከል ርቀት ያላቸውና ለጀልባዎች አመቺ ባለመሆናቸው አማራጭ የማጓጓዣ ድጋፍ እንዲደረግ ለደቡብ ኦሞ ዞን ጥያቄ አቅርበናል»ብለዋል።

የደቡብ ኦሞ ዞን መስተዳድር የመንግሥት ኮሚኒዮኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ለማ የኦሞ ወንዝ ከ3ዐ ዓመታት ወዲህ በእዚህን ያህል መጠን ሞልቶ የታየበት ጊዜ አለመኖሩን ተናግረዋል። ጎርፉ እያስከተለ የሚገኘው የጉዳት መጠን ስፋት እንዳለው የጠቀሱት የመምሪያው ኃላፊ እስከአሁን ከተፈናቀሉት 15 ሺህ ያህል ሰዎች በተጨማሪ በ 870 ሄክታር መሬት ላይ የነበሩ የተለያዩ ሰብሎችን አውድሟል ብለዋል።

በተጨማሪም በ11 ትምህርት ቤቶች ፣ በ2 የአርብቶ አደር ማሠልጠኛ ማዕከላት ፣ በ3 የሰዎችና በ2 የእንስሳት ጤና ኬላዎች ላይ ጉዳት ሲያደርስ 28 የውኃ መሳቢያ ሞተሮችን ይዞ መሄዱን አቶ መላኩ አብራርተዋል። በአሁኑ ወቅት በውኃ ተከበው የሚገኙ ከ2ሺህ በላይ ነዋሪዎችን እንደ ሄልኮፕተር ባሉ አማራጮች ሊወጡ የሚችሉበት ሁኔታ እንዲመቻች ለደቡብ ክልል የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ማሳወቃቸውን ነው የመምሪያ ኃላፊው የተናገሩት።

ዶቼ ቬሌ «DW» ያነጋገራቸው የደቡብ ክልል የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ጋንታ ጋሩማ በዳሰነች ወረዳ በጎርፍ ለተፍናቀሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች በክልሉና በፌዴራሉ መንግሥት በኩል ለዕለት ደራሽ የሚውሉ ድጋፎች በመጓጓዝ ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል። አቶ ጋንታ አያይዘውም «በአሁኑ ወቅት በክልሉ የተለያዩ ቢሮዎች የተውጣጣ ቡድን በስፍራው ይገኛል። ይህ ቡድን በውኃ ተከበው ያልወጡ ሰዎችን ማጓጓዝ የሚቻልበትን አማራጭ ለይቶ ባቀረበው መሠረት ነዋሪዎቹን የማውጣቱ ሥራ በፍጥነት ይከናወናል» ብለዋል።

የኢትዮጰያ ብሔራዊ ሜትሮዎሎጂ ኤጀንሲ ባቀረበው ዕለታዊ የአየር ትንበያ በተጨማሪ የግልገል ግቤ 3 የሀይል ማመንጫ ግድብ ውኃ እንደሚያስተነፍስ ሲገልጽና ሲያስጠነቅቅ እንደነበር መረጃ አልነበራችሁም ውይ ? አሁን በወንዙ ሙላት ሰዎች መፈናቀላቸው ለጉዳዩ በቂ ትኩረት አለመስጠታችሁንና አለመዘጋጀታችሁን አያመለክትም ወይ ? ሲል ዶቼ ቬሌ «DW» የደቡብ ኦሞ ዞን የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ መላኩ ለማን ጠይቋል። አቶ መላኩም በምላሻቸው « የአርብቶ አደር ኑሮ የተበታተነ በመሆኑ ሥራዎችን በታሰበው ልክ ለማከናወን የራሱ አሉታዊ ተጽዕኖዎች አሉት። ያም ሆኖ ማስጠንቀቂያው ከደረሰን ጊዜ ጀምሮ በሠራናቸው ሥራዎች በሰዎች ሕይወት ላይ ምንም ጉዳት ሳይደርስ ነዋሪዎችን ወደ ደረቃማ መሬት ለማጓጓዝ ችለናል። ይህ ባይሆን ኖሮ ከፍተኛ የሰብአዊና ቁሳዊ ጉዳት በደረሰ ነበር» ብለዋል።

ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ