1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የዐቢይ የወደብ መሻት ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች ተቃውሞ ቢገጥመውም አላፈገፈጉም

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ ኅዳር 5 2016

ኢትዮጵያ ለወደብ ኪራይ በዓመት 1.6 ቢሊዮን ዶላር ገደማ ታወጣለች። ሀገሪቱ የሱዳን እና የሶማሊላንድ ወደቦችን በአማራጭነት የምትጠቀም ቢሆንም ከ90 በመቶ በላይ የገቢ ወጪ ንግዷ የሚከወነው በጅቡቲ በኩል ነው። ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል የሚለው የዐቢይ አቋም ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ተቃውሞ ቢገጥመውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን አላፈገፈጉም

https://p.dw.com/p/4Yqcp
Dschibuti Hafen
ምስል DW/J. Jeffrey

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ዐቢይ አሕመድ የኢትዮጵያ የወደብ ጥያቄ በውይይት መፍትሔ ያገኛል የሚል አቋም አላቸው

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል በሚል አቋማቸው እንደጸኑ ነው። ጉዳዩ ከኢትዮጵያ ጎረቤቶች ተቃውሞ ቢገጥመውም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ “የምንወረው የለም። የምንወጋው የለም። በጥያቄው ግን አናፍርም” ሲሉ ተደምጠዋል። ይኸ አቋማቸው ግን አነጋጋሪ እንደሆነ ግን አላጡትም።  “ወደብን በሚመለከት ብዙ አይነት ንግግሮች፣ ትንበያዎች፣ ሴራዎች፣ ትንተናዎች ተደርገዋል” ያሉት ዐቢይ ማክሰኞ ሕዳር 4 ቀን 2016 በነበረው የምክር ቤቱ ውሎ በጉዳዩ ላይ የመንግሥታቸውን አቋም ዘርዘር አድርገው አቅርበዋል።

በቀይ ባሕር በኩል ኢትዮጵያ ወደብ ልታገኝ ይገባል የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሐሳብ ከአፍሪካ ቀንድ ሀገራት አዎንታዊ ምላሽ አላገኘም። የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ምላሽ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለብልጽግና ፓርቲ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሰጡት ማብራሪያ ከአንድ ወር ገደማ በፊት ለመንግሥት ቅርበት ባላቸው የቴሌቭዥን ጣቢያዎች ከተላለፈ በኋላ ነበር።

ዐቢይ በማብራሪያቸው የሶማሌ ላንድ ዘይላ ወደብ፣ የጅቡቲ ወደብ ፣ በኤርትራ የሚገኙት የአዶሊስ፣ የምጽዋ እና የአሰብ ወደቦች አማራጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ተናግረዋል። ኤርትራ እና ጅቡቲን ጨምሮ የኢትዮጵያ ፍላጎት ሊመለከታቸው የሚችል የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት በዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን በኩል አሊያም በቀድሞው ትዊተር በአሁኑ ኤክስ ምላሽ ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ እና ጅቡቲ “ሁልጊዜም ጠንካራ ወዳጅነት” እንዳላቸው የገለጹት የፕሬዝደንት ኢስማኢል ኦማር ጉሌሕ ከፍተኛ አማካሪ አሌክሲስ ሞሐመድ “ነገር ግን ጅቡቲ ሉዓላዊ መሆኗ መታወቅ አለበት። የግዛት አንድነታችን ዛሬም ይሁን ነገ ጥያቄ ውስጥ አይገባም” ብለዋል።

የጅቡቲ ፕሬዝደንት ኢስማኢል ኦማር ጉሌሕ
የጅቡቲው የፕሬዝደንት ኢስማኢል ኦማር ጉሌሕ ከፍተኛ አማካሪ አሌክሲስ ሞሐመድ “ጅቡቲ ሉዓላዊ መሆኗ መታወቅ አለበት። የግዛት አንድነታችን ዛሬም ይሁን ነገ ጥያቄ ውስጥ አይገባም” ብለዋልምስል Picture-allaince/dpa/J. Warnand

ኤርትራ በቀጥታ የኢትዮጵያን መንግሥት አሊያም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድን በስም ባትጠቅስም በወደብ ጉዳይ ላይ የሚደረጉ ንግግሮች “ብዙ እና ከመጠን በላይ” መሆናቸውን ገልጻለች። “ጉዳዩ ሁሉንም የሚመለከታቸው ታዛቢዎች ግራ አጋብቷል”ያለው የኤርትራ መንግሥት ውይይት ለማድረግ ፈቃደኛ እንዳልሆነ ጥቆማ ሰጥቷል። የሶማሊያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሊ ኦማር በበኩላቸው የሀገራቸው ሉዓላዊነት እና የግዛት አንድነት ለውይይት የሚቀርብ እንዳልሆነ ለብሎምበርግ ተናግረዋል። 

የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት ምላሽ አሉታዊ ቢሆንም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግን ኢትዮጵያ ወደብ ያስፈልጋታል ከሚል አቋማቸው ፈቅ አላሉም። የዐቢይ አንዱ መከራከሪያ በጅቡቲ የጦር ሠፈር ባላቸው ልዕለ ኃያላን መካከል ሊፈጠር የሚችል ግጭት የሚያሳድረው ተጽዕኖ ነው።

“የዚህ አካባቢ ጂዖ ፖለቲካ ተበላሸ” ያሉት ዐቢይ “ትላልቆቹ ሀገራት አንዳንዴ ሲጨቃጨቁ፤ በሚዲያ ሲጣሉ እኛ እንደነግጣለን” ሲሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል። “ትላልቆቹ ቢጣሉ ጅቡቲ ላይ ካምፕ ስላላቸው ድንገት ቢታኮሱ የእኛ ቦቴዎች ነዳጅ ሊያመጡ አይችሉም” ሲሉ ሊፈጠር የሚችለውን ተጽዕኖ አስረድተዋል።  

ከ90 በመቶ በላይ የኢትዮጵያ የወጪ እና የገቢ ንግድ የሚከወነው በጅቡቲ ወደብ በኩል ነው። አገሪቱ የሱዳን እና የበርበራ ወደቦችን በአማራጭነት ብትጠቀምም ከጅቡቲ ወደብ ጥገኝነት እምብዛም አተላቀቀችም። በኢትዮጵያ ማሪታይም ባለስልጣን መረጃ መሠረት በየዓመቱ ለወደብ ኪራይ 1.6 ቢሊዮን ዶላር ታወጣለች።

የኢትዮጵያ መንግሥት አማራጭ ከማፈላለግ ባሻገር ለወደብ ችግር መፍትሔ መሻት የጀመረው ዐቢይ ወደ ሥልጣን ከመምጣታቸው በፊት ነው። ከስድስት ዓመታት በፊት ኢትዮጵያ የበርበራ ወደብን ለማልማት ከሶማሌ ላንድ እና የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች ንብረት የሆነው ዱባይ የወደቦች አስተዳደር ኩባንያ (DP World) ጋር ሽርክና ገብታ ነበር።  አቶ አሕመድ ሽዴ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሳሉ በየካቲት 2010 በዱባይ የፈረሙት ሥምምነት የበርበራን ወደብ 19 በመቶ ድርሻ ለኢትዮጵያ የሚሰጥ ነበር።

በጅቡቲ የጦር ሠፈር ያላቸው ሀገራት
ዐቢይ አሕመድ በጅቡቲ የጦር ሠፈር ባላቸው ቻይና፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ጃፓን እና አሜሪካን በመሣሰሉ ሀገራት መካከል ግጭት ቢፈጠር በጅቡቲ ወደብ ጥገኛ በሆነችው ኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል።

ዐቢይ በመጋቢት 2010 በጠቅላይ ሚኒስትርነት ቃለ-መሐላ ፈጽመው በሚያዝያ ወደ ጅቡቲ ሲያቀኑ መንግሥታቸው በሽርክና ወደብ ለማልማት ጥያቄ አቅርቦ አዎንታዊ ምላሽ እንዳገኘ ተገልጾ ነበር። ሁለቱም ጥረቶች ግን ኢትዮጵያን ወደ ባሕር አላስጠጓትም።

የአሰብ እና የምጽዋ ወደቦች ባለቤት የነበረችው ኢትዮጵያ ከባሕር የራቀችው ከ32 ዓመታት ገደማ በፊት ኤርትራ ነጻነቷን ስታውጅ ነው። በደቡባዊ ኤርትራ ከጅቡቲ ድንበር በ55 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘው የአሰብ ወደብ እስከ 70 በመቶ የኢትዮጵያ የገቢ እና ወጪ ንግድ የሚከወንበት ነበር።

ኤርትራ ነጻነቷን ካወጀች በኋላ ከኢትዮጵያ ያላት ግንኙነት ጦርነት እና ውዝግብ ተጭኖት አሰብን እንደ ጅቡቲ ወደብ በኪራይ እንኳ በቅጡ መጠቀም አልቻለችም። ኢትዮጵያ የአሰብ ወደብን መጠቀም ያቆመችው ከኤርትራ ጋር ባደረገችው ደም አፋሳሽ ጦርነት ምክንያት ነበር።

የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ “ከዘለቄታው አንጻር ምንም እንኳን በአሰብ መጠቀም እኛን ምንም እንኳን የኤርትራን ያህል የሚጠቅመን ቢሆንም አሁን ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር በአሰብ ወደብ መጠቀም ከእኛ ይልቅ ይበልጥ የኤርትራን መንግሥት ይጠቅማል” በሚል አመክንዮ መንግሥታቸው እርምጃውን እንደወሰደ ተናግረው ነበር። መለስ “ወቅቱ ሲደርስ፣ ጠቃሚ እና አስፈላጊ ነው ብለን የምናይበት ደረጃ ላይ ስንሆን እናነሳዋለን” ይበሉ እንጂ እርሳቸው በሥልጣን ላይ በቆዩባቸው ዓመታትም ሆነ መሪነቱን ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲረከቡ ኢትዮጵያ አሰብን የምትጠቀምበት መንገድ አላገኘችም። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት
ኢትዮጵያ ወደብ ማግኘት አለባት የሚል አቋም ያላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ “የምንወረው የለም። የምንወጋው የለም። በጥያቄው ግን አናፍርም” ሲሉ ተደምጠዋል።ምስል AP/picture alliance

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሥልጣን ይዘው ኢትዮጵያ እና ኤርትራ እርቅ ሲያወርዱ መንግሥታቸው የአሰብን ወደብ ለመጠቀም በ2.8 ቢሊዮን ብር የመንገድ ግንባታ ሲያከናውን ቆይቷል። ዐቢይ በኤርትራ የአሰብ እና የምጽዋ፣ በኬንያ የላሙ እንዲሁም የጅቡቲ ወደቦችን በጎበኙባቸው ወቅቶች ጉዳዩን ማንሳታቸውን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል። “ይኸ ጉዳይ ሁሌ ያስጨንቀኛል” ያሉት ዐቢይ “ያልተነጋገርኩበት፣ ያልጠየኩበት ጊዜ የለም” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደጋግመው ጉዳዩ ችግር ሊያመጣ እንደሚችል ሲናገሩ ይደመጣል። ለዚህም የሀገሪቱን የሕዝብ ቁጥር እና የኤኮኖሚ ዕድገት በማሳያነት ይጠቅሳሉ። ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ “ኤኮኖሚ እያደገ፤ የሕዝብ ብዛት እያደገ በዚያ ልክ ደግሞ ወሳኝ የኤኮኖሚ አውድ የሆነው ነገር እያነሰ ከሔደ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ችግር ያመጣብናል” ሲሉ ተደምጠዋል።

ዐቢይ በውይይት ኢትዮጵያ ወደብ ታገኛለች የሚል እምነት ያላቸው ይመስላል። “እንወያይበት እና እንመካከርበት እና በቢዝነስ ሕግ እንስራው ነው” የሚል ምክረ-ሐሳብ አላቸው። “ቀይ ባሕር ያስፈልገናል፤ ጠቃሚ ነው የማይል ዓለም አለ እንዴ?” ሲሉ የጠየቁት ዐቢይ “ከምሥራቅ ጫፍ፤ ከምዕራብ ጫፍ ያስፈልጋል ብለው እኮ እዚህ አሉ ሠፈራችን። ምነው እኛ ስንፈልገው ነውር ሆነ?” ሲሉ ነቅፈዋል። ዐቢይ ቀይ ባሕርን “ብቸኛ መተንፈሻችን” ሲሉ ገልጸውታል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “በቢዝነስ ሕግ የማያወላዳ ምርጫ እንፈልጋለን” ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል።

ዐቢይ ኢትዮጵያ የወደብ ባለቤት መሆን ካልቻለች ሕገ-ወጥ የሰዎች ስደት ሊባባስ እንደሚችል ጭምር ሥጋት አላቸው። የኢትዮጵያ ጎረቤቶች ጉዳዩን “በከፋ ከማየት ይልቅ” ለውይይት እንዲዘጋጁም ጥሪ አቅርበዋል። “አንድ ቀን የሆነ ነገር ተፈጥሮ ልጆቻችን መድሐኒት አጥተው አይናችን እያየ እንዳይሞቱብን እንሰጋለን” ያሉት ዐቢይ “መፍትሔ እናዘጋጅ ሲባል ከጦርነት፣ ከግጭት፣ ከወረራ ከሉዓላዊነት ጋር መያያዝ የለበትም” ሲሉ በአጽንዖት ተናግረዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ማንንም አንወርም፤ የመውረር ፍላጎት የለንም” ሲሉ የመንግሥታቸውን አቋም አሳውቀዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ በአስመራ
የኢትዮጵያ መንግሥት ከኤርትራ ያለው ግንኙነት የመቀዛቀዝ አዝማሚያ ባሳየበት ወቅት ዐቢይ የሚያቀነቅኑት የወደብ ጉዳይ ሌላ ጦርነት እንዳይቀሰቅስ አስግቷል። ምስል Yemane G. Meskel/Minister of Information

የዐቢይ ማረጋገጫ የወደብ ጥያቄ ሲያነሱ ወትሮም መረጋጋት በራቀው የአፍሪካ ቀንድ ጉዳዩ ሌላ ጦርነት ሊቀሰቅስ ይችላል የሚል ሥጋት ለተጫናቸው የተሰጠ ምላሽ ይመስላል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉዳዩን ያነሱት የትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎችን ባዳረሰው ጦርነት ከኢትዮጵያ መንግሥት ጎን ቆማ ከተዋጋችው ኤርትራ ጋር ያላቸው ግንኙነት የመሻከር አዝማሚያ ባሳየበት ወቅት መሆኑ ደግሞ ሥጋቱ ጠንከር እንዲል አድርጎታል። ዐቢይ ግን ደግመው ደጋግመው መንግሥታቸው ወደ ግጭት የመግባት ፍላጎት እንደሌለው ሲናገሩ ተደምጧል።

“ኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ፣ ወደ ሶማሊያ፣ ወደ ጅቡቲ፣ ወደ ኬንያ ወይም ወደ ሌሎች ጎረቤቶቻችን አንድ ጥይት የመተኮስ ፍላጎት የላትም፤ በሉዓላዊነታቸው ጥያቄ የላትም” ያሉት ዐቢይ ወደብ ለማግኘት መንግሥታቸው ከኢትዮጵያ አየር መንገድ እና ከታላቁ የኅዳሴ ግድብ ድርሻ ለመስጠት ፈቃደኛ መሆኑን ጥቆማ ሰጥተዋል። “በአፍሪካ ምርጥ አየር መንገድ አለን። እሱን እንጋራ እና ውሀ አጋሩን። በአፍሪካ አንደኛውን ግድብ ገንብተናል። እሱን እንጋራ እና አጋሩን፣ እናንተም የኤኮኖሚ ችግር አለባችሁ እኛም ችግር አለብን ተያይዘን እንደግ ነው ያልንው” በማለት የመንግሥታቸውን አቋም አስረድተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ከጎረቤት ሀገራት “የሆነ ኃይል ተነስቶ ኢትዮጵያን ሊመታ ይችላል” የሚል ሥጋት የላቸውም። መንግሥታቸው ኢትዮጵያን “የመታደግ ከበቂ በላይ አቅም” እንዳለውም ገልጸዋል። ከአሜሪካ፣ ቻይና እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር በጉዳዩ ላይ ለመነጋገር ፈቃደኛ እንደሆኑ የገለጹት ዐቢይ “ኢትዮጵያ ያልተገባ ጥያቄ ከሕግ ውጪ፣ ከቢዝነስ ውጪ፣ ሰላም ከሚያረጋግጥ መንገድ ውጪ ጠይቃ ከሆነ ያነጋግሩን እና እረፉ ይበሉን፤ እንተወዋለን” ብለዋል።

እሸቴ በቀለ

ታምራት ዲንሳ