ከባድ አካል ጉዳተኛ ልጅን የምትንከባከበዋ ወጣት
ዓርብ፣ ግንቦት 9 2016ብዙውን ጊዜ ወደ አረብ ሀገራት ለሥራ የሚሄዱ ሴት ኢትዮጵያውያን በቤት ፅዳት ወይም ምግብ አብሳይነት ስራ ተቀጥረው እንደሚሰሩ ይናገራሉ። ወጣት ትዕግሥት ግን ከዚህ ከበድ ላለ ስራ ወስናለች። ትዕግሥት 27 አመቷ ነው። የክፍለ ሀገር ልጅ ናት። ከስድስት ዓመት በፊት ለስራ ወደ ዱባይ ስትሄድ በቤት ሰራተኝነት ነበር። ኃላም ስራዋን ለመቀየር ተገደደች። እሷም አዲሱን ስራ የተቀበለችው እዛው ዱባይ እንድትቆይ እና ገንዘብ ለማግኘት ስትል ነው። « የሚያመው ልጅ ነው የምንከባከበው። በራሱ በሰው እገዛ ነው። በራሱ የሚያደርገው ምንም ነገር የለም» የምትለው ወጣት 24 ሰዓት ውሎዋ ከታማሚው የ29 ዓመት ወጣት ጋር እንደሆነ ገልፃልናለች። ይህ የስነ ልቦና ጉዳት መፍጠሩ አይቀሬ ነው። « እሱ በተኛ ሰዓት መተኛት ሲነቃ መንቃት አለብኝ ትላለች» ይህንንም ስራ የምትሰራው ኢትዮጵያ ያለው ቤተሰቦቻን ለመርዳት ያላት አማራጭ ይህ ብቻ ስለሆነ ነው።
የስራው ክብደት
የትዕግሥትን ሥራ ከባድ የሚያደርገው ሌላው ነገር የምትንከባከበው ልጅ መናገርም ሆነ መስማት አለመቻሉ ነው። ስለ በሽታው ምንነትም ይሁን ከታመመ ስንት ጊዜ እንደሆነው አታውቅም። « አይናገርም። አይንቀሳቀስም። ምንም ነገር አይልም። አይተናኮልም። ግን ድምፁ ይረብሻል። ይጮኻል።»ትዕግሥትን እንደ ስሟ ትዕግስተኛ ያደረጋት ነገር ምን ይሆን? እሷ እንደምትለው ኢትዮጵያ ትምህርት ቤት እያለች በበጎ ፍቃደኝነት ቀይ መስቀል ውስጥ በፈረቃ ታግዝ የነበረው ስራ ብዙ አስተምሯታል። « ታማሚዎች ሲደውሉ አካባቢያቸውን በመጠየቅ ርዳታ እንሰጣለን። ቀይ መስቀሉ እኛን የመጀመርያ ርዳታ እንዴት መስጠት እንዳለብን ያሰለጥነናል። » ይህም ስልጣና አሁን የምትሰራው ስራ እንዳይከብዳት ረድቷታል። ለእሷ ፈተና የሆነባት ነገር የፆታ ልዩነታቸው ነበር።
ሥራውን እንዴት አገኘች?
ሥራው ከባድ ሆኖም ትዕግሥት ሌሎችን መርዳት መቻሏ ያስደስታታል። ቀጣሪዎቿንም ማሳመን ችላለች። « እዚህ ቤት ፅዳት ስሰራ ልጁ በጣም ያሳዝነኝ ስለነበር በመኃል እየሄድኩ አየዋለሁ። የምትይዘውን ልጅ አግዛለሁ። እና ያን ያን በማየት ነው ወደዚህ ስራ ያሸጋሸጉኝ። » ትላለች። ወደ ዱባይ ከሄደች አምስት ዓመት የሆናት ትዕግሥት በመሀል ወደ ኢትዮጵያ ተመልሳ ነበር። ይሁንና ነገሮች ስላልተስተካከሉላት ለመመለስ ግድ ብሏታል። « ከደሀ ቤተሰብ ነኝ። እህትም ወንድምም አሉኝ። የተሻለ ህይወት አይደለም የምንኖረው እና ለዛ ነው።» ቤተሰቦቿም ስለምትሰራው ስራ ያውቃሉ።
ትዕግሥትን የህይወት ተሞክሮዋ ያስተማራት ነገር
« ዐረብ አገር ሲባል ቀለል ያለ ስራ እንጂ እንዲህ አይነት ስራ የምንሰራ አይመስለንም። ከሀገር ስንወጣ ማንኛውንም ከባባድ ነገሮች ለመቀበል ዝግጁ መሆን አለብን። ካለበለዚያ በጣም ነው የሚጨንቀው ፤ የሚከብደውም። » የምትለው ትዕግሥት አሁን የምትሰራውን ስራ «ባይመቻትም» አዕምሮዋ መቀበል ግድ ይለዋል። ይህንን ስራ ለምን ያህል ጊዜ መስራት እንደምትችል አታውቅም። ለጊዜው ቀጣሪዎቿ እስካረዘሙላት ድረስ እዛው ለመቆየት ወስናለች። « የተሻለ ነገር ባገኝ አይዙኝም። » ስትል ቀጣሪዎቿ በፈለገችው ጊዜ እንደሚያሰናብቷት ፍቃደኛ መሆናቸውን ትገልፃለች።
ትዕግሥት ኢትዮጵያ እስከ 10ኛ ክፍል ድረስ ተምራለች። «ውጤት ሳይመጣልኝ ሲቀር ነው የተሰደድኩት» የምትለው ወጣት ምናልባት የበለጠ «ትምህርቴ ላይ አተኩሬ ቢሆን ኖሮ» ብላ የሚፀፅታት ነገር ይኖር ይሆን? ወይስ የተቻላትን ሁሉ አድርጋለች? እሷ ሁሉን አድርጌያለሁ ትላለች። እድሉን ብታገኝ በትምህርት የተደገፈ ርዳታ አግኝታ ወደፊት በዚህ የሙያ ዘርፍ ማገልገል ብትችል ምኞቷ ነው።
ልደት አበበ
ታምራት ዲንሳ