1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከራያ አላማጣና ሌሎች ወረዳዎች ብዙ ህዝብ እየተፈናቀለ ነው

ሰኞ፣ ሚያዝያ 14 2016

ሰሞኑን በራያ አላማጣና አካባቢው ከተፈጠረው የሰላም መደፍረስ ጋር በተያያዘ የተፈናቀሉ ነዋሪዎች አሁንም ህብረተሰቡ ከሚያደርግላቸው ድጋፍ ውጪ ድጋፍ እንዳላገኙ አመለከቱ።

https://p.dw.com/p/4f2hb
Äthiopien Binnenflüchtlinge Waghemira
የዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ተፈናቃዮች ምስል Waghemira communication

ኦቻ ከ29ሺህ በላይ ሰዎች መፈናቀላቸውን አመልክቷል

በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ አቅራቢያ በተዘጋፈጀው የመጠለያ ጣቢያ 39 ሺህ ተፈናቃዮች የተመዘገቡ ሲሆን በዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሐሙሲት በተባለ አካባቢ ደግሞ 8 ሺህ ያህል ተፈናቃዮች በአንድ ትምህርት ቤት መጠለላቸው ታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ከ29ሺህ በላይ ሰዎች ከራያ አላማጣና አካባቢዎች መፈናቀላቸውን አመልክቷል፡፡  

በሰሜን ወሎ ዞን ቆቦ ከተማ በተዘጋጀ የመጠለያ ጣቢያ ከደረሱ ተፈናቃዮች መካከል አንዷ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት ከየትኛውም የእርዳታ ሰጪ ተቋም እስካሁን የደረሰላቸው እርዳታ የለም። የአካባቢው ነዋሪዎች አሰባስበው ያመጡት ዱቄትም በአካባቢው በሚጥለው ዝናብ ምክንያት ለብልሽት ተጋልጦብናል ብለዋል፡፡

ሌላ በመጠለያ ጣቢያው ያሉ ተፈናቃይም «በከባድ ዝናብ እየተጠቃን ነው ተገቢ ድጋፍና እርዳታም አልቀረበልንም» ብለዋል፡፡

የትግራይ እና አማራ አዋሳኝ አካባቢዎችን ግጭት ውስጥ ያስገባ ውዝግብ

ከተለያዩ የባላ፣ ወፍላ፣ አላማጣና ኮረም አካባቢዎች ተፈናቅለው በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሐሙሲት በተባለች ከተማ በአንድ ትምህርት ቤት ከተጠለሉ ነዋሪዎች መካከል አንዱ እንደገለጡልን ደግሞ የአካባቢው አስተዳደር የተቻለውን ድጋፍ አድርጎልናል ሲሉ ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፣ በትምህርት ቤቱ 8 ሺህ ያክል ተፈናቃዮች እንደሚኖሩም አመልክተዋል፡፡

Äthiopien Binnenflüchtlinge Waghemira
በዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ሐሙሲት በተባለ አካባቢ 8 ሺህ ያህል ተፈናቃዮች በአንድ ትምህርት ቤት መጠለላቸው ታውቋል፡፡ ምስል Waghemira communication

የሰሜን ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ባለሙያ አቶ እንድሪስ አህመድ  ሰሞኑን በራያ አለማጣ አካባቢ በተቀሰቀሰ ከ6 ወረዳዎች የተፋናቀሉ ከ39ሺህ 600 በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቆቦ መድረሳቸውን አስረድተዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ ቆቦ እስከደረሱበት ያለፈው ሳምንት መጀመሪያ ድረስ ምንም እርዳታ ለተፈናቃዮቹ እንዳልደረሰም አቶ እንድሪስ አልክተዋል፡፡

አማራ ክልል በረሀብ ሰዎች መሞታቸውን ተፈናቃዮች ተናገሩ

በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ቢሮ (ኦቻ) ሰሞኑን ባወጣው መግለጫ  ከ29 ሺህ በላይ ሰዎች ከራያ አላማጣና አካባቢዎች መፈናቀላቸውን አመልክቷል፡፡ ተፈናቃዮቹ በሰቆጣና ኮቦ ከተሞች እንደሚገኙም አስታውቋል፡፡ ኦቻ በመግለጫው የንፁህ መጠጥ ውሀ፣ የምግብ፣ የመጠለያ ችግሮች በተፈናቃዮቹ ዘንድ እንደሚታይ አመልክቶ፣ሁሉን አቀፍ ድጋፍ ያስፈልጋልም ብሏል፣ ተፈናቃዮቹ የአካባቢው ማህበተሰብ ከሚያደርግላቸው ድጋፍ ውጪ ምንም እርዳታ እንዳልደረሳቸው ጠቁሟል፡፡

ከብሔረሰብ አስተዳደሩ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ ሊሳካ አልቻለም፡፡ አገር በቀል እርዳታ ሰጪዎች፣ ዓለም አቀፍ ረጂ ተቋማት፣ መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት የእርዳታ እጃቸውን ለተፈናቃዮቹ ነገ ዛሬ ሳይሉ እንዲለግሱ አቶ እንድሪስ ጠይቀዋል፡፡

ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል ያደረግነው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪ ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካም፡፡

ዓለምነው መኮንን
ልደት አበበ
አዜብ ታደሰ