1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከህወሓት የሰላም ጥሪ በኋላ የተከሰተው የአየር ድብደባ

ማክሰኞ፣ መስከረም 3 2015

የትግራይ ኃይሎች ዛሬ መስከረም 03 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠዋት የኢትዮጵያ መንግሥት በክልሉ መዲና መቀለ ከተማ አዲስ የአየር ጥቃት ፈጽሟል ሲሉ አመለከቱ። ዛሬ ተከስቷል የተባለው የአየር ጥቃቱ ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው ህወሓት በጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተ አስቸኳይ ግጭት የማቆም ጥሪ ባስተላለፈ በሶስተኛ ቀኑ መሆኑ ነው፡፡

https://p.dw.com/p/4Gmyw
Civil society in Tigray, Ethiopia, 18.08.2022
ምስል Million Hailesilassie/DW

«የድሮን ጥቃቱ መቀሌ ላይ ነዉ ተብሎዋል»

የትግራይ ኃይሎች ዛሬ መስከረም 03 ቀን 2015 ዓ.ም. ጠዋት የኢትዮጵያ መንግሥት በክልሉ መዲና መቀለ ከተማ አዲስ የአየር ጥቃት ፈጽሟል ሲሉ አመለከቱ። ዛሬ ተከስቷል የተባለው የአየር ጥቃቱ ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ የሚገኘው ህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) በጋራ ስምምነት ላይ የተመሰረተ አስቸኳይ ግጭት የማቆም ጥሪ ባስተላለፈ በሦስተኛ ቀኑ መሆኑ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ስለ ጦርነት የማቆም ጥሪም ሆነ ስለቀረበበት የድሮን ጥቃት ክስ አስካሁን የሰጠው ምላሽ አልተሰማም። የህዝባዊ ወያኔ ኃርነት ትግራይ (ህወሓት) ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳ ዛሬ ጠዋት በቲዊተር ገጻቸው በጻፉት መረጃ እንዳመለከቱት፤ የመቀሌው የድሮን ጥቃቱ ኢላማ ያደረገው የመቀለ ዩኒቨርስቲ አዲ ሓቂ ካምፓስ ነው። አቶ ጌታቸው በቲዊተር ጽሁፋቸው ለጥቃቱ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንግስታትን ነው የወቀሱዋቸው፡፡ ሁለቱ መንግስታት ሰላማዊ ዜጎችን አንኳን ያልለየ “የበቀል እርምጃ ወስደዋል” ይላል የቃል አቀባዩ መረጃ፡፡

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት ስለ ጦርነት የማቆም ጥሪም ሆነ ስለቀረበበት የድሮን ጥቃት ክስ አስካሁን የሰጠው ምላሽ አልተሰማም። ዶይቼ ቬለም ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት እና ለመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገለግሎት ሚኒስቴር የስራ ኃላፊዎች የእጅ ስልክ ላይ በመደወል አስተያየታቸውን ለማካተት ያደረገው ጥረት እስካሁን አልተሳካም፡፡

የዛሬው የአየር ጥቃት የተፈጸመው ትግራይ ክልልን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ህወሓት ከትናንት በስቲያ መስከረም 01 ቀን 2015 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ አስቸኳይ የተውክስ አቁም ስምምነት እንዲደረግና በአፍሪካ ህብረት መርህ ስር የተጀመረውን የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነትን በሰላም የመቋጨት ሂደቱን እንደሚቀበል ይፋ ባደረገበት በሶስተኛ ቀን መሆኑ ነው፡፡

የህወሓቱን የተኩስ አቁምና የሰላም ድርድር ጥሪው በአፍሪካ ህብረት፣ በተባበሩት መንግስታት፣ በዩናይትድ ስቴትስ፣ በአውሮፓ ህብረት እና በሌሎችም ዓለማቀፍ ማህበረሰብ ዘንድ ወዲያውኑ ነበር አዎንታዊ ምላሽ ያገኘው፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ግን በዚህም ላይ ዝምታውን የመረጠ መስሏል፡፡

የትግራይ ክልላዊ መንግስት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ እና በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ሰላማዊ ድርድር እንዲካሄድ ባለፈው እሁድ የጠየቀው የሰላም ድርድር፤ በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ለሶስተኛ ጊዜ ያገረሸው ጦርነት ከተከፈተ ከሶስት ሳምንታት በኋላ ነው፡፡

በእርግጥ ከተፋላሚዎቹ የአምስት ወራት የተናጥል የተኩስ አቁም እወጃ በኋላ ነሃሴ 17 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ ለተቀሰቀሰው ሶስተኛ ዙር ደም አፋሳሽ ጦርነት፤ የፌዴራል መንግስት ህወሓትን በጦር ቀስቃሽነት ስከስ፤ የትግራይ ኃይሎች በበኩላቸው መንግስት በተለያዩ ግንባሮች ጦርነት ከፍቶብናል በማለት ሲወዛገቡ ቆይተዋል፡፡

ባለፈው ቅዳሜ ጳጉሜን 05 የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መለእክተኛውን የስራ ጊዜ ያራዘመው የአፍሪካ ህብረት በህብረቱ ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በኩል የትግራይ ኃይሎች ያቀረቡትን በአፍሪካ ህብረት የሰላም ድርድር ጥላ ስር ለምክክር ለመቀመጠ ዝግጁ እንደሆኑ መግለፃቸውን አበጀ ብለው ነበር፡፡

እንደ ተመድ ያሉ ተቀዋማትም ተመሳሳይ አቋማቸውን አንጸባርው አጋጣሚውን በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት መልካም ሲሉ አሞካሽተውታል፡፡ ከኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት 22 ወራት የዘለቀ ደም አፋሳሽ ውጊያ የገጠሙት የትግራይ ኃይሎች ከዚህ ቀደም በኦባሳንጆ እና በህብረቱ ስር በሚደረገው የአደራዳሪነት ሚና ላይ እምነት እንደሌላቸው በተደጋጋሚ አንስተው ዛሬ ስልጣናቸውን ለአዲሱ ተመራጭ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ ያስረከቡት የቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ እንዲያሸማግላቸው ሃሳብ ማቅረባቸው ይታወሳል።

ከህወሓት ጋር የሚደረገው ድርድር በአፍሪካ ኅብረት የአደራዳሪነት ሚና ብቻ ሊደረግ እንደሚገባ አቋሙን በተደጋጋሚ ሲገልጽ የቆየው የኢትዮጵያ ፌዴራል መንግሥት፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን በሰብሳቢነት የሚመሩት እና ሰባት አባላት ያሉት ተደራዳሪ ቡድንን ይፋ ያደረገው በሰኔ ወር 2014 ዓ.ም. ነበር። ይህንኑን ተከትሎም የፌዴራል መንግስት ከህወሓት ጋር “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የትም ለመደራደር ዝግጁ ነኝ” ማለቱ አይዘነጋም፡፡

የህወሓት የወታደራዊ ክንፉ ከፍተኛ ባለስልጣን ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይ እና የሲቪል አመራሩ ከፍተኛ ባለስልጣን አቶ ጌታቸው ረዳ የተካተቱበት የትግራይ ኃይሎች የተደራዳሪ ቡድን አባላት ማንነት ለመጀመሪያ ጊዜ በይፋ የተገለጸው በአሁኑ መስከረም 01 ቀን 2015 ዓ.ም. መግለጫው ነው፡፡  

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ