1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከ163 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የኅዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት ጀመረ

እሑድ፣ የካቲት 13 2014

ከአስራ አንድ አመታት በፊት የተጀመረውና ከ163 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ 375 ሜጋዋት ኃይል ማመንጨት ጀመረ። ግንባታው ከ84% በላይ በደረሰው ግድብ "ግርጌና ቀኝ በሚገኙ ሁለት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የታቀፉ" አስራ ሶስት ተርባይኖች ሲኖሩት ሲጠናቀቅ 5 ሺሕ 150 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል

https://p.dw.com/p/47JS2
ETHIOPIA-EGYPT-SUDAN-DAM-ELECTRICITY
ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

ከ163 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት እና ለግንባታ አስራ አንድ አመታት ገደማ የወሰደው ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት ጀመረ። ግድቡ ከሚኖሩት አስራ ሶስት ተርባይኖች መካከል አንዱ ዛሬ 375 ሜጋ ዋት ኃይል በይፋ ማመንጨት ጀምሯል። 

ግድቡ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ለማብሰር በጉባ በተዘጋጀ መርሐ-ግብር ላይ የተገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ምዕራባውያን ከተለመደው የውኃ ፖለቲካ ተላቀው በአዲስ የትብብር መንፈስ ከኢትዮጵያ ጋር እንዲሰሩ ጥሪ አቅርበዋል። 

በጥብቅ የደህንነት ጥበቃ በተካሔደው መርሐ-ግብር የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ እና የቀድሞው ፕሬዝደንት ሙላቱ ተሾመን ጨምሮ የክልል ርዕሳነ-መስተዳድሮች እና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች ተገኝተዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ ባደረጉት ንግግር ቀዳማዊ ኃይለስላሴ እና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊን ጨምሮ ሐሳብ ከማመንጨት እስከ ግንባታ ተሳትፎ የነበራቸውን የሀገሪቱን መሪዎች ፤ ሕዝቡን እና በግንባታ ውስጥ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ድርሻ የነበራቸውን አካላትን አመስግነዋል።

መጋቢት 24 ቀን 2003 ግንባታው የተጀመረው ይኸ ግድብ ላለፉት አመታት በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል የውዝግብ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። የግድቡ ውኃ ኃይል አመንጭቶ ተፈጥሯዊ ፍሰቱን እንደሚቀጥል የተናገሩት ዐቢይ "የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መንግሥት ውኃውን ገድበው የግብጽ እና የሱዳንን ሕዝብ የማስራብ እና የማስጠማት ፍላጎት እንደሌላቸው" በተግባር መታየቱን አስረድተዋል። 

ETHIOPIA-EGYPT-SUDAN-DAM-ELECTRICITY
"ያለ አግባብ" የተጓተተውን የግንባታ ሒደት ለማስተካከል "ፕሮጀክቱን በበላይነት ከሚመራው ቦርድ አንስቶ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራር እና በፕሮጀክቱ አመራር ላይ ለውጥ" መደረጉን አቶ ክፍሌ ተናግረዋል።ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

"በከፍተኛ ቦታ ላይ የምንገኝ፤ ከፍተኛ የዝናብ መጠን የምናገኝ እና ብዙ ወራጅ ውኃ ያለን አገር በመሆናችን በርከት ያሉ ግድቦች ገንብተን ለእኛም ለሌሎች አገራትም የሚተርፍ ኢነርጂ ማምረት፤ መሸጥ የምንችል ስለሆንን የምዕራቡ ዓለም እና ገንዘብ ያላቸው አገራት አሁን ያለውን የውኃ ፖለቲካ መልክ ቀይረው ከእኛ ጋር በትብብር አዳዲስ ፕሮጀክቶች በመስራት ለእኛም ከድህነት መውጫ፤ ከጭለማ መውጫ ለእነሱም ከጋዝ ብከላ መከላከያ እንዲሆናቸው በቀና እና በአዲስ መንገድ በትብብር መንፈስ እንድንሰራ" የሚል ጥሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አቅርበዋል። 

ታላቁ የኢትዮጵያ ኅዳሴ ግድብ ግንባታው በተጀመረ በአራት አመታት ውስጥ ኃይል ያመነጫል የሚል ዕቅድ ነበር። ይሁንና ኃይል የማመንጨት ሥራው "በግንባታው ሒደት ባጋጠሙ መሰናክሎች የተነሳ" መዘግየቱን የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሖሮ ተናግረዋል። ሙሉ ግንባታው በአንድ ኩባንያ እንዲከናወን በታኅሳስ 2003 ዓ.ም ውል ተፈርሞ እንደነበር ያስታወሱት አቶ ክፍሌ "ቢሆንም መንግሥት ኮንትራቱ ለሁለት እንዲከፈል እና የጄኔሬተር፣ ተርባይን እና የውኃ ማስተላለፊያ የመቆጣጠሪያ በሮች ፍብረካ እና ገጠማ ሥራዎች በአገር ውስጥ ኮንትራክተር በሜቴክ እንዲሰራ መወሰኑ በፕሮጀክቱ የጊዜ ሰሌዳ ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ እና ማጓተት ፈጥሯል" ሲሉ ተናግረዋል። 

ETHIOPIA-EGYPT-SUDAN-DAM-ELECTRICITY
የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሁለት ትላልቅ ግድቦች አሉት። ግድቡ በሚጠናቀቅበት ወቅት 17 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ይይዛል።ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

"ያለ አግባብ" የተጓተተውን የግንባታ ሒደት ለማስተካከል "ፕሮጀክቱን በበላይነት ከሚመራው ቦርድ አንስቶ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አመራር እና በፕሮጀክቱ አመራር ላይ ለውጥ" መደረጉን አቶ ክፍሌ ተናግረዋል። ከዚህ በተጨማሪ የግድቡን የኤሌክትሮ ሜካኒካል እና የስቲል ስትራክቸር ሥራዎች ሲያከናውን ለነበረው የብረታ ብረት እና ኢንጂኔሪንግ ኮርፖሬሽን (የቀድሞው ሜቴክ) የተሰጠውን ውል በማቋረጥ "በዘርፉ ልምድ ባላቸው ኮንትራክተሮች" በመተካት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "ፕሮጀክቱን ታድገውታል" ሲሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል። 

የግድቡ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በአስራ ሶስት ተርባይኖች 5 ሺሕ 150 ሜጋዋት የኤሌክትሪክ ኃይል የማመንጨት አቅም ይኖረዋል። ግንባታውን ለማጠናቀቅ "አሁን ባለው ሁኔታ ከሁለት አመት ተኩል እስከ ሶስት አመታት ሊፈጅ እንደሚችል" ዋና ሥራ አስኪያጁ ለብሔራዊው የቴሌቭዥን ጣቢያ ተናግረዋል።

ግንባታው ከ84 በመቶ በላይ የደረሰው እና እስካሁን ከ163 ቢሊዮን ብር በላይ የወጣበት ፕሮጀክት የኮቪድ-19 ያሳደረውን ተጽዕኖ ጨምሮ አቶ ክፍሌ እንደተናገሩት "አሁንም ቢሆን በተግዳሮቶች የተሞላ" ነው። ዋና ሥራ አስኪያጁ "በተለይ በተልዕኮ በሚደረግ ጦርነት ፕሮጀክቱን ለማሰናከል የሚደረገው ጥረት ቀላል ፈተና አልነበረም፤ አይደለምም" ሲሉ ተደምጠዋል። 

ETHIOPIA-SUDAN-EGYPT-DAM-ELECTRICITY
መጋቢት 24 ቀን 2003 ግንባታው የተጀመረው ይኸ ግድብ ላለፉት አመታት በኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ መካከል የውዝግብ ምንጭ ሆኖ ቆይቷል። ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሁለት ትላልቅ ግድቦች አሉት። ግድቡ በሚጠናቀቅበት ወቅት 17 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውኃ ይይዛል። ከግድቡ ወደኋላ እስከ 240 ኪሎ ሜትር የሚደርስ ርዝመት ይኖረዋል። በውስጡ ብዙ ደሴቶች እንደሚፈጠሩ የተናገሩት የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሖሮ ከኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት ባሻገር ለአሣ ምርት፣ ለመዝናኛ፣ ለቱሪዝም እና ለመጓጓዣ አገልግሎት የመዋል ከፍተኛ እድል እንዳለው ገልጸዋል። 

በአሁኑ ወቅት ከፕሮጀክቱ ሰባት ሺሕ ሰራተኞች ወደ 500 የሚጠጉት ከአርባ አገራት የተውጣጡ የውጪ አገር ዜጎች ተሳታፊ መሆናቸውን በዛሬው መርሐ-ግብር ላይ በሥራ አስኪያጁ ተገልጿል። "ግንባታው ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ወቅት ከ10 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ተሳትፈውበታል" ሲሉ ዋና ሥራ አስኪያጁ ክፍሌ ሖሮ ተናግረዋል። 

አስራ ሶስቱ ተርባይኖቹ "በግድቡ ግርጌ እና ቀኝ በሚገኙ ሁለት የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች የታቀፉ" መሆናቸውን የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ሥራ አስኪያጅ ክፍሌ ሖሮ በዛሬው የምረቃ መርሐ-ግብር ላይ ተናግረዋል። ሥራ አስኪያጁ እንዳሉት ከዋናው የኃይል ማስተላለፊያ ጋር በ500 ኪሎ ቮልት እና 400 ኪሎ ቮልት ተገናኝተዋል። 

ታምራት ዲንሳ

እሸቴ በቀለ