1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እያነጋገረ ያለው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ

ሰኞ፣ ግንቦት 26 2016

ኢትዮጵያውያን ከሀገር እንዳይወጡ የማገድ ሥልጣንን ከፍርድ ቤት ለኢሚግሬሽን [አገልግሎት] የበላይ ኃላፊ የሚሰጥ የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክት ቤት ቀረበ። የአዋጁ ማሻሻያ የመዘዋወር ነፃነትን ለማስከበር እና ለኢትዮጵያውያን እና ለውጭ ሀገር ዜጎች የኢሚግሬሽን አገልግሎቶችን በተሻለ ጥራትና ቅልጥፍና ለመስጠት ታልሞ መሆኑ ተገልጿል።

https://p.dw.com/p/4ga7w
 የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎትምስል Solomon Muche/DW

እያነጋገረ ያለው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ

እያነጋገረ ያለው የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ

ኢትዮጵያውያን ከሀገር እንዳይወጡ የማገድ ሥልጣንን ከፍርድ ቤት ለኢሚግሬሽን [አገልግሎት] የበላይ ኃላፊ የሚሰጥ የአዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ለሕዝብ ተወካዮች ምክት ቤት ቀረበ። የአዋጁ ማሻሻያ የመዘዋወር ነፃነትን ለማስከበር እና ለኢትዮጵያውያን እና ለውጭ ሀገር ዜጎች የኢሚግሬሽን አገልግሎቶችን በተሻለ ጥራትና ቅልጥፍና ለመስጠት ታልሞ መሆኑ ተገልጿል።

የመዘዋወር ነፃነት በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት "ገደብ ሊጣልበት የማይችል" መብት መሆኑን የጠቀሱት የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጠበቃ አምሃ መኮንን፤ ማሻሻያው ሕግ ሆኖ ይወጣል ብለው እንደማያምኑ ገልፀዋል። ለዚህ ምክንያት ያሉት አደገኛ ያሉት ይህ ማሻሻያ "በቀጥታ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ድርጊት ነው የሚሆነው" የሚለው ነው።

 

የአዋጁ ማሻሻያ ረቂቅ ሕግ ላይ የተካተቱ አዳዲስ ድንጋጌዎች

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ ከጊዜ ለውጥ ጋር የመጡ ለውጦችን ለማስተናገድ፣ የተቀናጀ የድንበር ቁጥጥር አስተዳደር እንዲኖር እና በአዋጁ አፈፃፀም በተግባር የታዩ የተባሉ ችግሮችን ለመፍታት ታልሞ መዘጋጀቱ በማብራሪያው ላይ ተጠቅሷል።

ተቋሙን ከኢሚግሬሽን ባለሥልጣን አገልግሎት ወደሚል ስያሜ የሚለውጠው ረቂቅ ሕግ ከኢትዮጵያ እንዳይወጡ ስለሚታገዱ ሰዎች የያዘው ድንጋጌ ብዙዎችን አሳስቧል።

ማንኛውም ሰው ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ሊታገድ የሚችለው በፍርድ ቤት ሲታዘዝ ብቻ እንደሆነ ነባሩ አዋጅ የደነገገ ሲሆን ተሻሽሎ የቀረበው ግን የፍርድ ቤት ብቸኛ ሥልጣን የሆነውን ይህንን የማድረግ አቅም የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የበላይ ኃላፊ ለሚሆኑ ተሿሚም የሚሰጥ ነው።

የሕግ ባለሙያዎች ለሰብዓዊ መብት ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ ጠበቃ አምሃ መኮንን "ይህንን ለማድረግ መሞከሩ ራሱ አደገኛ ነው" ይላሉ።

"በሕገ መንግሥቱ [የኢፌዴሪ] መሠረታዊ መብቶች ውስጥ የተካተተውን የመዘዋወር ነፃነት በአስፈፃሚው አካል ውሳኔ ለመገደብ ሥልጣን በሚሰጥ ሁኔታ ሕጉን ለማሻሻል መሞከሩ ራሱ በጣም አደገኛ አካሄድ ነው" 

የኢትዮጵያ አየር መንገድ
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ምስል Solomon Muchie/DW

 

ዜጎች ከሀገር እንዳይወጡ ሊታገዱ የሚችሉበት ሁኔታ

ረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ ማንኛዉም ሰዉ ከኢትዮጵያ እንዳይወጣ ሊታገድ የሚችለዉ በፍርድ ቤት ሲታዘዝ እንደሆነ የተቀመጠ ቢሆንም ከፍርድ ቤት የእግድ ትዕዛዝ እስኪገኝ ድረስ በብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደረሱ ወይም ሊያደርሱ የሚችሉ ሰዎች ከሀገር እየወጡ ከተጠያቂነት እያመለጡ በብሔራዊ ጥቅም እና ደህንነት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ በመሆኑ፤ እንዲህ ያለው ሁኔታ በሚኖርበት ወቅት የአገልግሎቱ ዋና ዳይሬክተር ከሚያገኘው መረጃ በመነሳት ማንኛውንም ሰው ከሀገር እንዳይወጣ ማገድ እንዲችል መፈቀዱን፤ ሆኖም ያለአግባብ የሰዎች የመንቀሳቀስ መብት እንዳይገድብ በፍርድ ቤት እንዲጸድቅ የሚያስገድድ ድንጋጌ መቀመጡን ያትታል። 

ማሻሻያው ይፀድቃል የሚል እምነት እንደሌላቸው የተናገሩት ጠበቃና የሕግ ባለሙያው አምሃ መኮንን፤ ሁኔታው "በቀጥታ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ድርጊት ነው" ብለዋል።

"ይሄ ሕግ ሕግ ሆኖ ይወጣል ብየ አላስብም። ምክንያቱም በቀጥታ ሕገ መንግሥቱን የሚፃረር ድርጊት ነው የሚሆነው። ምክንያቱም እንደ አንድ የመንግሥት አካል ሕግ አውጪውም ራሱ ሕገ መንግሥቱን የማስከበር እና ለሕገ መንግሥቱ ተገዢ የመሆን ኃላፊነት አለበት - ፓርላማው ራሱ" 

አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፍያ
አዲስ አበባ ቦሌ አየር ማረፍያ ምስል Solomon Muche/DW

 

ረቂቅ ማሻሻያ አዋጁ ምን ሊያስከትል ይችላል?

ስማቸውንም ድምፃቸውንም እንዳንጠቀም የገለፁ አንድ ግለሰብ ይህ ማሻሻያ "ሰዎችን ለእንግልት፣ ለመጉላላት እና ለሙስና የሚያጋልጥ" መሆኑን ጠቅሰዋል። "መማረር እና መጉላላት ብሎም የውጪ ንግድ እንቅስቃሴን እንዳይገታ" ም ሥጋታውን ጠቅሰዋል።

በማሻሻያው አገልግሎቱ መመሪያ የማውጣት ሥልጣንም እንዲኖረው ተደርጓል፡፡ ማሻሻያው የሙስና ድርጊትን ሊያባብስ እንደሚችል የገለፁት የሕግ ባለሙያው፣ "በግለሰቦች ላይ ያልተፈለገ ጫና የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል። መንግሥት ይህንን ማሻሻያ ሊያደርግ ያሰበበት ዋነኛው ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችልም ጠይቀናቸዋል።

"ግጭቶችን በማስተባበር፣ በማበረታታት፣ መረጃ በመስጠት የሚያግዙ፣ በሞራልም የቁሳዊም ድጋፍ የሚያደርጉ ኃይሎች በተለያየ አካባቢዎች አሉ ተብሎ በመንግሥት ይታመናል። በዚህ መልክ የሚጠረጠሩ ግለሰቦችን እንቅስቃሴ በመገደብ በሀገር ውስጥ ተጠያቂ እንዲሆኑ ለማድረግ ያስችላል ተብሎ ሊሆን ይችላል ብየ ነው የምገምተው" በማለት መልሰዋል።

የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት አዋጅ ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ በሕገ ወጥ መንገድ በኢትዮጵያ የሚኖሩ የውጭ ሀገር ዜጎች ላይም አስተዳደራዊ ቅጣት የመጣል ሥልጣንን ለኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት የሚሰጥ ነው።

ሰለሞን ሙጬ 

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሠ