1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እየጨመረ የመጣው የሳይበር ጥቃት በኢትዮጵያ

ረቡዕ፣ ሰኔ 7 2015

ካስፐርስኪ የተባለው ዓለም አቀፍ የጥናት ቡድን በቅርቡ ባወጣው መረጃ እንደሚያሳየው በጎርጎሪያኑ 2023 ዓ/ም ብቻ በኢትዮጵያ ወደ 18,000 የሚጠጉ የሳይበር ጥቃቶች በተለያዩ ድርጅቶች ተፈፅሟል። DW ያነጋገራቸው የሳይበር ደህንነት ባለሙያ እንደገለፁት ለጥቃቱ በእውቀት ላይ ያልተመሰረተ የዲጂታል አጠቃቀም ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል።

https://p.dw.com/p/4SZaP
Symbolbild Cyber Attack Cyber Security
ምስል Marko Lukunic/Pixsell/picture alliance

በአንድ ዓመት ብቻ ከ18,000 በላይ የሳይበር ጥቃቶች ተፈፅመዋል


የካስፐርስኪ  የተባለው ዓለም አቀፍ የጥናት ቡድን በቅርቡ ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ የሳይበር ጥቃት እየጨመረ መጥቷል።የጥናት ቡድኑ መረጃ እንደሚያሳየው በጎርጎሪያኑ 2023 ዓ/ም  ብቻ በኢትዮጵያ ወደ 18,000 የሚጠጉ የሳይበር ጥቃቶች በተለያዩ ድርጅቶች ተፈፅሟል።የዛሬው የሳይንስ እና ቴክኖሎጅ ዝግጅት በጥቃቱ መጨመር ምክንያቶች እና መፍትሄዎች ላይ  ያተኩራል። 
የመረጃ  ቴክኖሎጂ በአሁኑ ወቅት በዓለም ላይ በእያንዳንዱ ዘርፍ ቁልፍ ሚና የሚጫወት ቴክኖሎጂ ሆኗል።ይህ ቴክኖሎጂ በአንድ ሀገር የኢኮኖሚ እድገት እና ድህነት ቅነሳ፣በትምህርት በጤና እና በሌሎች ዘርፎች የሚያሳድረው ተጽዕኖ ቀላል አይደለም።ከዚህ አንፃር ሀገራት ለመረጃ ቴክኖሎጂ የሚሰጡት ትኩረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። እንደ ሌሎቹ የዓለም ሀገራት ሁሉ በኢትዮጵያም የመረጃ ቴክኖሎጂ እና በመረጃ ቴክኖሎጂ ላይ የተመሰረቱ  አገልግሎቶችን ለማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እድገት አጋዥ አድርጎ የመጠቀም ጅምሮች አሉ።
በዚያው መጠን ግን በመረጃ ላይ የሚሰነዘረው የሳይበር ጥቃት በኢትዮጵያ እያደገ መሆኑ ይነገራል። በመረጃ ቴክኖሎጂ ላይ ያተኮረው ካስፐርስኪ የተባለው ዓለም አቀፍ የጥናት ቡድን በቅርቡ ያወጣው መረጃም ይህንኑ ያመለክታል።በአንድ የግል ባንክ ውስጥ የሳይቨር ሴኩሪቲ ማናጀር ሆነው የሚሰሩት  የሳይበር ደህንነት ባለሙያው አቶ ብሩክ ወርቁ ከሳይበር ምህዳሩ መስፋት ጋር ተያይዞ ጥቃቱ የሚጠበቅ ነው ይላሉ። 
ዓለም አቀፍ የጥናት ቡድኑ  ባወጣው መረጃ በኢትዮጵያ  በጎርጎሪያኑ 2023 ዓ/ም በተለይም ሚያዚያ እና ግንቦት  ወሮች የገንዘብ እና የሀይል መስጫ ተቋማትን ጨምሮ  ቢያንስ በ10 የመንግስት ተቋማት የበይነመረብ  አገልግሎቶች ላይ  ያነጣጠረ ጥቃት ተፈፅሟል።
ከመለስተኛ እስከ ከፍተኛ የሳይበር ጥቃት ፈፃሚ ወንጀለኛ  ቡድኖች ድረስ ባለፉት ጥቂት አመታት ሀገሪቱ ላይ ያነጣጠረ የሳይበር ጥቃቶችን ለበርካታ ጊዜያት መከሰታቸውን የገለፀው የጥናት ቡድኑ ፤ ከነዚህም ውስጥ ጥቂቶቹ አካባቢያዊ  ሲሆኑ አንዳንዶቹ ጥቃቶች ደግሞ ዓለም አቀፋዊ ናቸው ብሏል።
የካስፐርስኪ መረጃ እንደሚያሳየው በዚህ መልኩ  በጎርጎሪያኑ 2023 ዓ/ም ብቻ በኢትዮጵያ ወደ 18,000 የሚጠጉ የሳይበር ጥቃቶች እና 30,000 የሚሆኑ መረጃን በመያዣነት በመጠቀም የገንዘብ ቤዛ የሚጠይቁ በእንግሊዥናው / Ransomware/ተፈፅሟል።የሳይበር ደህንነት ባለሙያው አቶ ብሩክ እንደሚሉት ለጥቃቱ ተጋላጭ ከሚያደርጉ ምክንያቶች መካከል  በእውቀት ላይ ያልተመሰረተ የዲጂታል አጠቃቀም ቀዳሚውን ድርሻ ይይዛል።
ሌላው «ፊሽንግ» የሚባለው የጥቃት አይነት ሲሆን፤ የሚያጓጉ እና የሚያማልሉ ስዕሎችን ወይም መልዕክቶችን ከአባሪዎች ጋር በመላክ ተጠቃሚዎች በሚከፍቱበት ጊዜ ለሳይበር ጥቃት የሚያጋልጡ አደገኛ ሶፍትዌሮችን ወደ ስማርት ስልኮች እና ኮምፒዩተሮች በመላክ የሚደርስ ጥቃት ነው። ከዚህ በተጨማሪ በኮምፒዩተሮች ላይ የሚገጠሙ የዩኤስቢ ገመዶች እና ያልዘመኑ ሶፍትዌሮችም ለጥቃት ያጋልጣሉ።
በሌላ በኩል ላለፉት አራት ወራት በኢትዮጵያ እንደ ፌስቡክ እና ቲክቶክ ላሉ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የበይነመረብ ክልከላ መደረጉን ተከትሎ እንደ ቩፔኤን ያሉ አማራጮችን መጠቀም እየተለመደ መጥቷል።እንደ ባለሙያው ይህም  የሳይበር ጥቃት ተጋላጭነትን ይጨምራል።
እነዚህ ጥቃቶች በሳይበር ምህዳር ውስጥ ያሉ አገልግሎቶችን በሙሉ ችግር ላይ የሚጥሉ ሲሆን፤ በድርጅቶችም ሆነ በግለሰቦች ላይ አገልግሎትን ለተወሰኑ ጊዚያት ማስተጓጎል፣ ደንበኞችን ከአገልግሎት ማገድ ወይም መቆለፍ ፣መረጃ ማጥፋት እና መመንተፍ፣ ወይም በስማቸው ሌላ አካል እንዲጠቀም ማድረግን ጨምሮ በርካታ ወንጀሎች ይፈፀማሉ።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በኢትዮጵያ የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚዎች ከ60 ሚሊዮን በላይ  የኢንተርኔት ተደራሽነት ደግሞ ወደ 30 በመቶ ማደጉን ከሀገሪቱ የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሚወጡ መረጃዎች ያሳያሉ።ምንም እንኳ  ከ110 ሚሊዮን በላይ ለሚሆነው የሀገሪቱ ህዝብ በቂ ባይሆንም ፤ በዚህ መልኩ የበይነመረብ ግንኙነትን፣ ፍጥነትን እና ተደራሽነትን ለመጨመር ከሚደረገው ጥረት እና ውጥን ትይዩ በይነመረብ ላይ የተመሰረቱ ግብይቶች፣ የገንዘብ ዝውውር የባንክ እና ሌሎች አገልግሎቶችም  እየጨመሩ መጥተዋል። የጥቃቱ መጠንም ከእነዚህ  ዲጂታል አገልግሎቶች መጨመር  ጋር እያደገ የሚሄድ ሲሆን  ያንን የሚመጥን የዲጂታል እውቀት አብሮ ካላደገ ደግሞ ጥቃቱ የሚያመጣው  ጉዳትም በዚያው መጠን  ሊጨምር እንደሚችል ባለሙያው ገልፀዋል። 
ስለሆነም ችግሩን ለመቀነስ ብሎም ለመከላከል በግለሰብ ደረጃ የዲጅታል አጠቃቀም እውቀትን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።ድርጅቶችም የታወቁ እና የዘመኑ ሶፍትዌሮችን መጠቀም ለሰራተኞቻቸው በየ ጊዜው ስልጠና መስጠት መፍትሄዎች መሆናቸውን ባለሙያው መክረዋል።በሀገር አቀፍ ደረጃም የሳይበር ደህንነት ማዕቀፎችን በማዘጋጄት የሳይበር ጥቃትን አስቀድሞ መተንበይ እና መከላከል የሚቻልበትን ዘዴ መፍጠር እንደሚያስፈልግ አቶ ብሩክ አመልክተዋል።
በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ በተደረገው የበይነመረብ ክልክላ የተነሳ  ቪፒኤንን ከመጠቀም ጋር ተያይዞ የሚመጣውን የመረጃ ስርቆት ተጋላጭነትን በተመለከተ የሀገሪቱን ትልቁን የበይነመረብ አገልግሎት አቅራቢ ድርጅት ኢትዮ   ቴሌኮምን ለማነጋገር  ቀጠሮ ብንይዝም ባለመሳካቱ ምላሻቸውን ማካተት አልተቻለም።

 Biruk Worku ,Cyber Security Analyst
አቶ ብሩክ ወርቁ የሳይበር ደህንነት ባለሙያምስል Privat
Illustration | VPN
ምስል Rafael Henrique/ZUMAPRESS/picture alliance
Symbolbild l Darknet l Kriminalität l Cyber l Hacking
ምስል Silas Stein/imago images

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ታምራት ዲንሳ