1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እናት ፓርቲ የሰላም ስምምነቱ ለፓርላማ እንዲቀርብ ጠየቀ

ሐሙስ፣ ኅዳር 1 2015

ስምምነቱ ሕጋዊ እውቅና ማግኘት ያለበት በፓርላማው ነው የሚለው እናት ፓርቲ ከመተግበሩ በፊት በፓርላማው ለውይይት እንዲቀርብ ጠይቋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ዮናስ ቢርመታ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲከሰት አሥፈፃሚ አካላት ፈጣን ምላሽና ውሳኔ መስጠት የሚችሉበት በቂ የሕግ መሠረትም አላቸው ብለዋል።

https://p.dw.com/p/4JJdD
Äthiopien | PK Friedensgespräche | Redwan Hussien und Getachew Reda
ምስል Siphiwe Sibeko/REUTERS

እናት ፓርቲ የሰላም ስምምነቱ ለፓርላማ እንዲቀርብ ጠየቀ

በፌዴራል መንግሥት እና በሕወሓት መካከል የተፈረመው የሰላም ስምምነት "ወደ ትግበራ ከመግባቱ በፊት በፓርላማው ለውይይት እንዲቀርብና ምክር ቤቱ እንዲያጸድቀው" ሲል እናት ፓርቲ ጠየቀ።ፓርቲው ባወጣው መግለጫ "የሰላም ስምምነቱ በጎ ጅምር ሆኖ ሳለ ሕዝብ ስለ ሂደቱ በግልጽ እንዲያውቅ አለመደረጉ ያሳስባል" ብሏል። ጉዳዩ ለሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ይቅረብ የሚለው ጥያቄ ከሕግ አንፃር እንዴት እንደሚታይ የጠየቅናቸው አንድ የሕግ ባለሙያ "እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲከሰት የመንግሥት  አሥፈፃሚ አካላት ፈጣን ምላሽ እና ውሳኔ መስጠት የሚችሉበት በቂ የሕግ መሠረትም አላቸው ሲሉ መልሰዋል።ሰሎሞን ሙጬ ከአዲስ አበባ ዝርዝሩን ልኮልናል።
እናት ፓርቲ ለሁለት ዓመታት "ኢትዮጵያን በእጅጉ ያደቀቀው" ሲል የገለፀው እና ዘርፈ ብዙ ገዳት ያደረሰው ጦርነት በስምምነት መቋጨቱ በተለይ በጦርነቱ ቀጣና ውስጥ ላሉት ወገኖች ከፍ ያለ ትርጉም አለው ብሏል።
ፓርቲው "በድርድሩ የጦርነቱ ቀጥተኛ ሰለባ የሆኑት የአማራ እና የአፋር ማኅበረሰቦች አለመወከላቸው እንዲሁም የትግራይ ማኅበረሰብም በሕወሓት ብቻ ተወክሎ ድርድሩ መካሄዱ እንዲመጣ የተፈለገውን ዘላቂ ሰላም ለማረጋገጥ አዳጋች ያደርገዋል የሚል ከፍተኛ ሥጋት አለኝ" ብሏል።
የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ያየህ አስማረን ስለ መግለጫው ተጨማሪ ማብራሪያ ጠይቀናቸዋል።
"በድርድሩ የተሳተፉት ብልጽግና ፓርቲ እና ሕወሓት ናቸው። በጦርነቱ የተጎዳው ማሕበረሰብ ደግሞ እንደ አጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ነው። በቀጥታ የተጎዱት ደግሞ የትግራይ፣ የአማራ እና የአፋር ሕዝቦች ናቸው። ስለዚህ ከፓርቲ በላይ በቀጥታ የጦርነቱ ገፈት ቀማሽ ስለሆኑ እና የሚነሱም አወዛጋቢ ጉዳዮች ስላሉ የእነሱን ፍላጎት ሊያንፀባርቅ በሚችል መልኩ ከፓርቲ ውጪ በሆኑ ሰዎች መወከል አለባቸው" ብለዋል። 

መኢአድ፣ኢህአፓና እናት ፓርቲ ገዥው ፓርቲ ህዝብን ለአደጋ እያጋለጠ ነው ሲሉ ከሰሱ

እናት ፓርቲ "የድርድሩ ስምምነት ወደ ትግበራ ከመግባቱ በፊት በፓርላማው ለውይይት እንዲቀርብና ምክር ቤቱ እንዲያጸድቀው" በማለትም ጠይቋል።"የድርድር ስምምነቱ ሕጋዊ እውቅና ማግኘት ያለበት በፓርላማው ነው" በማለት የፓርቲው የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የፓርቲያቸውን አቋም ገልፀዋል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕግ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ዮናስ ቢርመታ የሰላም ስምምነቱ ለሕዝብ እንደራሴዎች ቀድሞ ቀርቦ ይሁንታ ሊያገኝ ይገባል የሚለው ምልከታ ከሕግ አንፃር እንዴት ይታያል ስንል ጠይቀናቸዋል።
"እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲከሰት የመንግሥት አካል ውሳኔ ለመስጠት ሰፊ ጊዜ ስለሌለው ያንን ላያደርግ ይችላል። አሥፈፃሚ አካላት ፈጣን ምላሽ እና ውሳኔ መስጠት የሚችሉበት በቂ የሕግ መሠረትም አላቸው" የሚል ምላሽ ሰጥተዋል።ይህ ሲባል ግን ጥያቄው የተገቢነት ጭብጥ የለውም ማለት እንዳልሆነ ያብራሩት የሕግ ባለሙያው ይህ አለመሆኑ አሸባሪ ተብሎ የተፈረጀው አካል ከድርጊቱ ለመራቅ ከሚሰጠው ዋስትና እና ሕዝቡ ካለበት ችግር አንፃር መታየት እንዳለበት አመልክተዋል። 

ለሁለት ዓመታት ደም ያፋሰሰው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ በዝግ ለአሥር ቀናት ንግግር እና ድርድር ከተደረገበት በኋላ ጥቅምት 23 ቀን 2015 ዓ. ም በሰላም ስምምነት ፊርማ ተቋጭቷል። በሁለቱ ኃይሎች የትምምን ጭብጦች አተገባበር ዙሪያ የሚደረጉ ውይይቶችም ቀጥለዋል።

ሰሎሞን ሙጬ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ