1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

እርዳው ነጋሽ ሚኮ «መንጅክሶ ጸዴ» እስከ ጀርመንዋ ኮሎኝ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 1 2015

አቶ እርዳው ሁለት ፕሮጀክቶች ነበሯቸው።የመጀመሪያው ዘመዶቻቸው ከሀገራቸው እንዳይሰደዱ ባያሉበት ራሳቸውን የማስቻል ፕሮጀክት ነበር። ሁለተኛው ፕሮጀክት ደግሞ የወጡበትን ማኅበረሰብ የሚረዱበት ፕሮጀክት ነው። በትውልድ አካባቢያቸው ባካሄዱት በሁለተኛው ፕሮጀክት የአካባቢው ተማሪዎች መምህራንና ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ሆነዋል።

https://p.dw.com/p/4I3TE
በጀርመኑ የዞነንብሉመን ማኅበር በተበረከተው በፀሀይ ብርሃን በሚሰራ መብራት ተማሪዎች በማታ ማጥናት ይቻላል።
የመንጂስኮ ተማሪዎች በፀሐይ ብርሃን የሚሰራ የሚያጠኑበት መብራት ይዘውምስል Erdaw Negash Miko

እርዳው ነጋሽ ሚኮ፤ከኢትዮጵያዋ የገጠር ከተማ «መንጅክሶ ጸዴ» እስከ ጀርመንዋ ኮሎኝ

በሙያቸው መካኒካል መሐንዲስ ቢሆኑም በዚህ ማዕረግ መጠራት አይፈልጉም። ከዚያ ይልቅ ለወጡበት ማኅበረሰብ ባደረጉት መልካም ሥራ ቢነሱ ይመርጣሉ።  የምዕራብ ጀርመንዋ የኮሎኝ ከተማ ነዋሪ የሆኑት በጎ አድራጊው በዚሁ ከተማ በሚገኘው ፎርድ በተባለው ታዋቂ የአሜሪካን የመኪና ኩባንያ ለ30 ዓመታት አገልግለዋል። ኮሎኝ ከሚገኙ ወዳጆቻቸው ጋር ከጥቂት ዓመታት  በፊት በመሰረቱት ማኅበር አማካይነት ደግሞ፣ በትውልድ መንደራቸው «መንጅክሶ ፀዴ» እና 18 ኪሎሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው «ጨፌ ዶንሳ» ከተማ ትምህርት ቤቶችን አስገንብተዋል፤ ለተማሪዎችም የደንብ ልብስን ጨምሮ የተለያዩ ቁሳቁሶችን በመለገስ ለአስተማሪዎችም በትምህርት ቤት አቅራቢያ መኖሪያ ቤት በመስራት ትልቁን ምኞታቸውን ማሳካት ችለዋል። እርዳው ነጋሽ ሚኮ ይባላሉ። የአንደኛ ደረጃ ትምሕርታቸውን ከትውልድ መንደራቸው በቅርብ ርቀት ላይ በምትገኘው ጨፌዶንሳ በተባለችው የገጠር ከተማ ነው የተማሩት። ጨፌዶንሳ በሰንዳፋና በደብረ ዘይት መካከል የሚገኝ ከተማ ነው። አቶ  እርዳው እስከ ስምንተኛ ክፍል ጨፌዶንሳ ሲማሩ 18 ኪሎሜትር መጓዝ ነበረባቸው። ስምንተኛ ክፍልን ሲያጠናቅቁ ወላጆቻቸው ትምሕርቱ ይብቃህ ሲሏቸው ፣ጠፍተው ወደ አዲስ አበባ ሄዱ ።አዲስ አበባ ግን የሚያስጠጋቸው አልነበረም።
እድል ቀንቷቸው ምሥራቅ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ገቡ። አነስተኛ ስራ መኖሪያም አገኙ። ምሥራቅ አጠቃላይ እስከ አስረኛ ክፍል ከተማሩ በኋላ ጥሩ ውጤት አምጥተው ተግባረ እድ የቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ትምሕርት ቤት ገቡ።ትምህርታቸውን በከፍተኛ ውጤት በማጠናቀቃቸው  የነጻ ትምሕርት እድል አግኝተው የዛሬ 41 ዓመት ጀርመን መጡ።
ላይፕሲሽ በተባለችው የምሥራቅ ጀርመን ከተማ መካኒካል ምህንድስና ተማሩ በዚሁ የትምሕርት ዘርፍ ከፍተኛ ትምሕርታቸውን መቀጠል ቢፈልጉም ሳይሳካላቸው ቀረና ወደ ምሥራቅ በርሊን ከዚያም አሁን ወደ ሚኖሩባት ኮሎኝ ከተማ ገቡ። በዚያም ጀርመንና አሜሪካ ጥገኝነት ጠይቀው ፤የጀርመኑ ሲዘገይ የአሜሪካኑ ተሳክቶ ዳላስ ቴክሳስ ሄዱ።ዳላስ እየተማሩ እየሰሩም ሳለ የደረሳቸው አንድ ደብዳቤ  ሃሳባቸውን አስቀየረ። 
የልጆቻቸው እናትም ከጀርመን ዳላስ ተክትለዋቸው መጡ።ሆኖም እዚያ መቆየት ስላልፈለጉ ጀርመን መመለሳቸው ግድ ሆነ። ከተመለሱ በኋላም በቴክኒክ ሞያ ሰልጥነው ፎርድ ኩባንያ መስራት ጀመሩ።ጡረታ እስከወጡበት ጊዜ ድረስ ለ30 ዓመታት አገልግለዋል።አቶ እርዳው እንደሚሉት ሁለት ፕሮጀክቶች ነበሯቸው የመጀመሪያው ፕሮጀክታቸው  ለቤተሰባቸው ያዘጋጁት ፕሮጀክት ነበር።ዘመዶቻቸው ከሀገራቸው እንዳይሰደዱ ባያሉበት ራሳቸውን የማስቻል ፕሮጀክት ነበር። ይህን ያደረግኩበት ምክንያት አለኝ ይላሉ።  
አንደኛው ፕሮጀክት ካለቀ በኋላ ደግሞ የወጡበትን ማኅበረሰብ ወደ ሚረዱት ወደ ሁለተኛው ፕሮጀክት ፊታቸውን አዞሩ። ከፍጻሜ ያደረሱት ይህ ፕሮጀክት እጅግ የረኩበት መሆኑን ይናገራሉ።በትውልድ አካባቢያቸው ባካሄዱት በዚህ ፕሮጀክት ተማሪዎች መምህራንና ኅብረተሰቡ ተጠቃሚ ሆኗል።  

ግንባታው የተጠናቀቀው የመንጂስካ አንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት
በበጎ አድራጊው በዞነን ብሉመን ማኅበር እርዳታ የተሰራው የመንጂስካ አንደኛ ደረጃ ትምሕርት ቤት ምስል Erdaw Negash Miko
ማኅበሩ በመንጂክሶ ትምሕርት ቤት  አስገንብቷል።
አቶ እርዳው ነጋሽ ሚኮና የድርጅታቸው የዞነንብሉመን ማኅበር አባላት በመንጂክሶ ጸዴ ምስል Erdaw Negash Miko

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ