1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ፣ እንደገና ድርቅ

ሰኞ፣ የካቲት 14 2014

በ1977 ድርቅና ረሐብ-ሰበብ ደርግን ሲወቅሱ፣ ሲከሱ፣ ሲያወግዙ የነበሩት ኃይላት የአዲስ አበባና የአስመራ አብያተ መንግስታትን ከያዙ በኋላም፣ ተደጋጋሚ ረሐብ ነበር።በ1985 እና በ1992 የደረሰዉ  በ10 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንን ለረሐብ አጋልጧል።

https://p.dw.com/p/47NRr
Flash-Galerie 60 Jahre Genfer Flüchtlingskonvention
ምስል WFP/Rose Ogola7/picture alliance/dpa

የድርቅና የረሐብ ዑደት እንዲያበቃ የሚፈልግ አለ ይሆን?

 

አርዶ ሐሰን ከሞት የተረፉ ፍየልና በጎችዋን እየነዳች፣ አራት ልጆችዋን አስከትላ፣ ነባር አካባቢዋን ጥላ ቀብሪ ዳሕር አጠገብ ደሳ ቀልሳለች።«ዝናብ ካልሰጠን ምን እንሆናለን?» ትጠይቃለች።ከብቶቹ ገሚሱ ታመዋል-ሁሉም ተርበዋል።ልጆቹ ደክመዋል።ድርቅ።ኢትዮጵያ።በ1965-እና 66 እንዲያ ነበር።በ1977 ሚሊዮኖች አለቁ።በ1985ና በ1992ም ብዙ ሚሊዮኖች ተራቡ።ዛሬም የከብት ሐብቷ እየረገፈ፣ ሕጻናትዋ እየተራቡ፣ 6.8 ሚሊዮን ዜጋዋ ምፅዋት እየተጠበቀ ነዉ።የድርቅ-ረሐብ ልመና አዙሪት፣ ያፍታ ቅኝታችን ትኩረት ነዉ።አብራችሁን ቆዩ።

                               

የዛሬ 3 ዓመት ግድም የኢትዮጵያ ባለስልጣናትን ቅንጡ መኪኖችን እናግዳለን ሲባል ሰምተን ነበር።ዛሬ የኢትዮጵያ ሹማምት ካንዱ ክልል ርዕሠ-ከተማ ወደ ሌላዉ ለመጓዝ ትልቁ፣ፈጣኑ፣ ይታገዳል ተብሎ የነበረዉ ምቹ መኪና አልመች ብሏቸዉ ልዩ የኮንትራት አዉሮፕላን ያዛሉ ማለትን ሰማን።ዕዉነት ይሆን? «እሳት በሌለበት አይጤስም» ብለን የሆነዉን እናዉሳ።

ወይዘሮ አርዶ ሐሰን ሞትን ሽሽት ከትዉልድ መንደሯ ብዙ ኪሎ ሜትሮች በዕግሯ ተጉዞ ቀብሪ ዳሕር አጠገብ ደርሳለች።ሰባ ከብቶችዋ፣ በጣሙን 4 ልጆችዋን ማትረፍ አለማትረፏን ግን ለፈጣሪ ከመስጠት ባለፍ እርግጠኛ አይደለችም።«በጣም ተጨንቄያለሁ።የሚበላና የሚጠጣ ምንም የለኝም።ቀጥሎ የሚሆነዉን አላዉቅም።በጣም የሚያሳስበኝ የልጆቼ ጉዳይ ነዉ።ልጆቼ እየተራቡ ነዉ።»

Äthiopien Hungersnot in Tigray
ምስል Million Haileselassie/DW

መስከረም 1 1967 በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የተራጨዉ የዮናታን ዲምብልቢ ፊልም ንጉሠ ነገስት አፄ ኃይለ ስላሴ ለልደታቸዉ ከዉጪ ያስመጡትን ኬክ ከሚያሳየዉ ፊልም ጋር የተቀናበረ  ነበር።

ንጉሱ አንዴ ለልደታቸዉ ዉድ ኬክ ሲቆርሱ፣ ሌላ ጊዜ ለሞተ-ዉሻቸዉ የዕብነ በረድ መቃብር ሲያሳንፁ፣ ሌላ ጊዜ መሳፍንቱና መኳንንቱ ሲንደላቀቁ ሕዝብ መራቡ ያስቆጣዉ ኢትዮጵያዊ ለገዢዎቹ የሚራራ ልብ አልነበረዉም።

ጋዜጠኛ ዲምብልቢ «ድብቁ ረሐብ» ያለዉ መቅሰፍት ከበሽታ ጋር ተዳብሎ አንድ መቶ ሺሕ ያሕል ሰዉ ገድሏል።ከ2500 ሺሕ በላይ አስርቧል።በመቶ ሺሕ የሚቆጠር አፈናቅሏል።ረሐቡ እንደ አልጋወራሽም፣ እንደ ንጉሠ፣ እንደ ንጉሠ-ነገሥትም ለ58 ዘመን ኢትዮጵያን የገዙትን አፄ ኃይለ ሥልሳን ከስልጣን ለማስወገድ አንዱ ምክንያት ሆነ።የቀድሞዉ የኢትዮጵያ የርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚያ ኮሚሽነር ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ያስታዉሳሉ።

 

ድርቅና ረሐቡ በኢትዮጵያዉያን ዘንድ ያሳደረዉ ንዴትና ቁጭት ጳዉሎስ ኞኞና ብጤዎቹን ብዕራቸዉን አስቀምጠዉ የልመና ኮሮጆ ሲያነሳሳ፣ የብርሐኑ ዘሪሁን ድርሰት፣ የፀጋዬ ገብረ መድሕን ቅኔ ይፈስ፣ የነ ጥላሁን ገሠሠ ሙዚቃን ያንቆረቁር ገባ።

                             

የፖለቲካ ለዉጥ ግርግር ፣ የተራዉ ሕዝብ ሐዘኔታ፤ የጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ ገጣሚ፣ ሙዚቀኞቹ ቁጭት ከአፍላ የአብዮት-አድሐሮት፣ ከሰሜን፣ከሁሉም በላይ ከምሥራቅ ጦርነት ጋር ተዳምሮ የፈጠረዉ ሆይ-ሆይታ ገለል-ቀለል-ከፈል ከማለቱ ኢትዮጵያ በሌላ ድርቅ ተመታች።በሌላ ረሐብ ተቃወሰች።1977።የከፋ ነበር።

አንዳድ ዘገቦች እንደሚጠቁሙት ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጋ ሰዉ በረሐብና ረሐብ በሚያስከትለዉ በሽታ ሞቷል።ከ6 ሚሊዮን የሚበልጥ ሕዝብ ተርቧል።ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ረሐብ እንደገና ፖለቲካዊ ሆነ ይላሉ።

Äthiopien Somali Region | Dürre, Trockenheit | tote Tiere
ምስል Maria Gerth/DW

ይኸኛዉ ሻለቃ ዳዊት እንደሚሉት ፖለቲካዊ የሆነዉ እንደ 1965-66ቱ ኢትዮጵያ ዉስጥ ብቻ አልነበረም።የምሥራቅ-ምዕራቦች ኃያላን መሻኮቻም ጭምር ሆነ እንጂ።

 ከኤርትራ እስከ ኦጋዴን፣ ከትግራይ እስከ እስከ ቦረና ሕዝብ ሲራብ ኢትዮጵያ ጦርነት ላይ ነበረች።የመንግስት ጦርና የያኔዎቹ የኤርትራ፣ የትግራይና የሌሎች አካባቢዎች ነፃ አዉጪዎች የሚያደርጉት ዉጊያ የሺዎችን ሕይወት፣ የሚሊዮኖችን ሐብት ንብረት ያጠፋ-ያጋይ ነበር።ጦርነቱ በረሐብ ለተጎዳዉ ሕዝብ ርዳታ እንዳይደርስ እንቅፋትም ነበር።

ለ1965-66ቱ ረሐብ  አፄ ኃይለ ስላሴንና አገዛዛቸዉን ተጠያቂ ያደረገዉ ደርግ ለ1977ቱ ድርቅና ረሐብ ተወቃሽ ተከሳሽ ሆነ።በተለይ ረሐቡ በጠናበት ወቅት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ፓርቲን (ኢሠፓን) ለመመስረት ይጣጣር የነበረዉ ደርግ፣ የመሰብሰቢያ አዳራሽ አስገንብቷል፣ 3 መቶ ሺሕ ዶላር የሚያወጣ ዉስኪ ከዉጪ አስመጥቷል የሚለዉ ወቀሳና ትችት ሶሻሊስታዊዉን ሥርዓት ለማሳጣት ለሚፈልጉ ኃይላት ስብ የፕሮፓጋንዳ ቀለብ ነበር የሆነዉ።እንደገና ሻለቃ ዳዊት።

                                    

የዋሽግተን-ለንደን፣ የኦታዋ-ቦን-ሮም መሪዎች ሕዝባቸዉ ኢትዮጵያን እንዲረዳ  ተማፀኑ።የእነ መሐመድ ዓሚን ካሜራዎች ኢትዮጵያ ላይ አነጣጠሩ፣የእነ ቦብ ጊልዶፍ፣ የእነ ቦኖ Do they know it is Christmas፣ የእነ ማይክል ጃክሰን፣ የነ ሊዮንድ ሪቼ፣ የነስቲቭ ወንደር----የብዙዎች WE ARE THE WORLD ሙዚቃ ፈሰሰ።ርዳታዉም ጎረፈ።ድርቅና ረሐቡ ግን እያሰለሰ ቀጠለ።በ1977 ድርቅና ረሐብ-ሰበብ ደርግን ሲወቅሱ፣ ሲከሱ፣ ሲያወግዙ የነበሩት ኃይላት የአዲስ አበባና የአስመራ አብያተ መንግስታትን ከያዙ በኋላም፣ ተደጋጋሚ ረሐብ ነበር።በ1985 እና በ1992፣ በ2003 የደረሰዉ  ድርቅ በ10 ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያንን ለረሐብ አጋልጧል።

የቀድሞ ወቃሽ፣ ከሳሽ አዉጋዞች በዘመናቸዉ ለደረሰዉ ተመሳሳይ ችግር ፈጥነዉ መልስ አለመስጣቸዉ እንዳስተዛዘበ፣ በተራቸዉ እንደተወቀሱ፣ እንደተወገዙ ከረሐብተኛዉ ሕዝብ በቀሙት ሐብት አንዴ ከቀድሞ ወዳጆቻቸዉ ከኤርትራ ገዢዎች ጋር፣ ሌላ ጊዜ «አማፂ» ካሏቸዉ ኃይላት ጋር ሲዋጉ መቶ ሺዎችን አስፈጅተዉ ሲንደላቀቁ ኖረዉ ሄዱ።

Äthiopien | Dürre in Borena
ምስል Firaol Wako/PHD

ሌሎች መጡ።

ኢትዮጵያ ግን ዛሬም ጦርነት ላይ ናት።ኢትዮጵያዉያን ዛሬም ለረሐብ ተጋልጠዋል።የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለዉ ኢትዮጵያን፣ ሶማሊያንና ኬንያን በመታዉ ድርቅ 13 ሚሊዮን ሕዝብ ለረሐብ ተጋልጧል።ከግማሽ የሚበልጠዉ ኢትዮጵያዊ ነዉ።6.8 ሚሊዮን።ቦረና፣ ደቡብ ኦሞ፣አጋዴንና ሌሎችም አካባቢዎች የሕዝቡ ሕልዉና መሰረት የሆኑት ከብቶች እየረገፉ ነዉ።

በኢትዮጵያ የተባበሩት መንግስታት የሕፃናት መርጃ ድርጅት (UNICEF) ተጠሪ ጊያንፍራንኮ ሮቲግሊያኖ እንደሚሉት ከብቶች ሞቱ ማለት ሕፃናት ወተት አጡ ማለት ነዉ።

                        

«እንስሳት ሞቱ ማለት፣ የሚሞቱት እንስሳቱ ብቻ አይደሉም።ከእንስሳቶቹ ጋር የቤተሰቡ ደሕንነት፣ ጤናም ይሞታል።ሕፃናት ወተት፣ ሥጋና የመሳሰሉትን ምግቦች አጡ ማለት ነዉ።ሁሉም ሲደመር ለሕፃናቱ በጣም መጥፎ ነገር ነዉ።»

መጥፎ ነዉ።40 ከመቶ የሚሆኑት ኢትዮጵያዉያን ሕፃናት በምግብ እጥረት ይሰቃያሉ።ከ30 ከመቶ የሚበልጡት ክብደታቸዉ በእድሜያቸዉ ከሚጠበቀዉ በጣም ያነሰ ነዉ።

ዛሬ ሕፃናት ለሞት የተጋለጡባቸዉ፣ ከብቶች የሚረግፉባቸዉ፣ አዋቂዎች ርዳታ የሚጠይቁባቸዉ አካባቢዎች ዝናብ ካጡ ዘንድሮ ሶስተኛ ዓመታቸዉ።

                                  

«አሁን ሶማሌ ክልል ያለዉ ድርቅ በጣም አሳሳቢ ነዉ።የጀመረዉ ለተከታታይ ሁለት ዓመታት ዝናብ ከጠፋ በኋላ በ2021 ነዉ።አሁን ለክልሉ (ሕዝብ) በጣም አሳሳቢ ነዉ።እንስሳት እየሞቱ ነዉ።»

ይላሉ በሶማሌ ክልል የዓለም ምግብና የእርሻ ድርጅት (FAO) ተጠሪ ጠይብ ሸሪፍ ኑር።

ኢትዮጵያ ዉስጥ ዝናብ አልጣለም ማለት ድርቅ፣ በዉጤም ረሐብ ተቃረበ ማለት ነዉ።ዝንብ ከመሳቱ በተጨማሪ የአንበጣ መንጋም ብቅብቅ ያለ ሰብል፣ ዛፍና ሳርን አጥፍቶታል።የቀድሞዉ የርዳታ ማስተባበሪያና ማቋቋሚ ኮሚሽን የቅድመ-ማስጠንቀቂያ የሚባለዉን ስልትና አሰራር ሥራ ላይ ካወለ ሻለቃ ዳዊት እንደሚሉት ከ35 ዓመት በልጦታል።

Flash-Galerie Somalische Flüchtlinge im Lager Dolo Ado Äthiopien
ምስል DW

ድርቅ እንደሚከሰት እየታወቀ የከብት ሐብትንና ሕዝብን ማዳን ያልተቻለበት ምክንያት በያሳዝን እንኳን ሊያጠያይቅ ይገባል።ሻለቃ ዳዊት «ፖለቲካ» ይሉታል።

ዘመን ሔደ-ዘመን መጣ።የፖለቲካ ሥርዓት ተለዋወጠ።ኢትዮጵያ ግን የድርቅና የረሐብ አብነት እንደሆነች ቀጥላለች።ከየዘመኑ ጦርነት፣ ከረሐብና መቅሰፍት ተርፎ ማዕበልን ሲያነብ፣ ራብ ስንት ቀን ይፈጃልን ሲቀኝ፣ ዋይ ዋይ ሲሉን ሲያዜም፣ WE are the Worldን ሲደምጥ ያደገዉ ትዉልድ ዛሬም የወገኖቹን የገጠጠ አፅም፣ የፈጠጠ ዓይን፣የሰለለ አካል ከማየት ሌላ-ሌላ ለማየት አልታደለም።ከድረሱልኝ ተማፅኖ፣ ከዋይታ-ሲቃ ሌላ-ሌላ መስማት አልቻለም።

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ