1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኢትዮጵያ እና የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች በተራዘመ የብድር አቅርቦት የመጀመሪያ ግምገማ ተስማሙ

Eshete Bekele
ቅዳሜ፣ መስከረም 18 2017

በሐምሌ በጸደቀው እና ኢትዮጵያ 3.4 ቢሊዮን ዶላር በምትበደርበት የተራዘመ የብድር አቅርቦት የመጀመሪያ ግምገማ የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች እና የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ተስማምተዋል። የአይኤምኤፍ ባለሙያዎች ቡድን መሪ “በገበያ ወደሚወሰን የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሽግግርን ጨምሮ የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በጥሩ ሁኔታ እየተካሔደ ነው” ብለዋል

https://p.dw.com/p/4lC5j
አዲስ አበባ
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባልደረቦች “ከባንኮች እና የግል ኩባንያዎች ጋር ጭምር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።”ምስል Eshete Bekele/DW

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ባለፈው ሐምሌ በጸደቀው የተራዘመ የብድር አቅርቦት መርሐ-ግብር የመጀመሪያ ግምገማ ከሥምምነት ላይ ደረሱ። ሁለቱ ወገኖች ከሥምምነት የደረሱት በአልቫሮ ፒሪስ የሚመራ የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ቡድን ወደ አዲስ አበባ አቅንቶ ከመስከረም 7 እስከ 16 ቀን 2017 ከተደረገ ግምገማ በኋላ ነው።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ቆይታቸው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ፣ ምክትላቸው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ እና ሌሎች ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መገናኘታቸውን ቡድኑን የመሩት አልቫሮ ፒሪስ ትላንት አርብ መስከረም 17 ቀን 2017 ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባልደረቦች “ከባንኮች እና የግል ኩባንያዎች ጋር ጭምር ውጤታማ ውይይት አድርገዋል።”

“በገበያ ወደሚወሰን የውጭ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ሽግግርን ጨምሮ የኢትዮጵያ የኤኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በጥሩ ሁኔታ እየተካሔደ ነው” ብለዋል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ሎጎ
የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ሥምምነት በመጪዎቹ ሣምንታት መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ባደረገው አበዳሪ ተቋም አስተዳደር እና የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ መጽደቅ ይኖርበታል።ምስል Maksym Yemelyanov/Zoonar/picture alliance

በውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ላይ የተደረገው ለውጥ በመደበኛው እና በተለምዶ ጥቁር እየተባለ በሚጠራው የትይዩ ገበያ መካከል ያለውን ልዩነት “በከፍተኛ ሁኔታ አጥብቦታል” ያሉት ፒሪስ በአጠቃላይ የሀገሪቱ ኤኮኖሚ ላይ የፈጠረው “ትንሽ ረብሻ” እንደሆነ ገልጸዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት በዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ ብድር እና ድጋፍ  የኤኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ማድረግ ሲጀምር የብር የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ተዳክሟል።

የውጪ ምንዛሪ ግብይት በገበያው አቅርቦት እና ፍላጎት እንዲከወን ከመወሰኑ በፊት አንድ የአሜሪካ ዶላር በባንኮች ከ58 ብር ከ50 ሳንቲም ገደማ ይመነዘር ነበር። የባንኮች አማካኝ ዕለታዊ የምንዛሪ ተመን ወደ 119 ብር ከ76 ሣንቲም እንዳሻቀበ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ያሳያል።

የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ
የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ቆይታቸው የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ፣ ምክትላቸው ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ፣ የብሔራዊ ባንክ ገዥ ማሞ እስመለዓለም ምህረቱ እና ሌሎች ከፍተኛ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት መገናኘታቸውን ቡድኑን የመሩት አልቫሮ ፒሪስ አስታውቀዋል።ምስል CC BY 2.0/U.S. Institute of Peace

አዲስ አበባ ደርሶ ወደ ዋሽንግተን የተመለሰውን የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ቡድን የመሩት አልቫሮ ፒሪስ “አዲሱ የምንዛሪ ተመን ሥርዓት ከዚህ ቀደም ይታይ የነበረውን ከፍተኛ የውጪ ምንዛሪ እጥረት በመቅረፍ ኤኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ ተጋርጦበት የነበረውን ትልቅ እንቅፋት እያስወገደ ነው” ብለዋል።

የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት ባለሙያዎች ሥምምነት በመጪዎቹ ሣምንታት መቀመጫውን በዋሽንግተን ዲሲ ባደረገው አበዳሪ ተቋም አስተዳደር እና የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ መጽደቅ ይኖርበታል።

የዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ ግምገማ ሲጠናቀቅ ኢትዮጵያ ከተበደረችው 3.4 ቢሊዮን ዶላር ውስጥ 345 ሚሊዮን ዶላር ገደማ ይለቀቅላታል። ቦርዱ የተራዘመ የብድር አቅርቦት የተባለውን መርሐ-ግብር ባለፈው ሐምሌ 22 ቀን 2016 ሲያጸድቅ ወዲያውኑ አንድ ቢሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ መንግሥት መልቀቁ አይዘነጋም።