1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አዲሱ የአልዛይመር መድሃኒት

ማክሰኞ፣ የካቲት 14 2015

የህክምና ሳይንስ ተመራማሪዎች ላለፉት 50 ዓመታት ለአልዛይመር ወይም ለመርሳት በሽታ መድሃኒት ለማግኜት በርካታ ምርምሮችን አድርገዋል።በቅርቡ ግን ለመጀመሪያ ጊዜ በሽታውን ያክማል የተባለ መድሃኒት በምርምር መገኘቱን ይፋ አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/4MNsd
Krankheit Epilepsie l Stärkster Kernspintomograph Europas getestet
ምስል Jens Wolf/dpa/picture-alliance

መድሃኒቱ በበሽታው የመጀመሪያ ደረጃ ላይ የሚወሰድ ነው

 
የአልዛይመር ወይም የመርሳት በሽታ በዓለም ዙሪያ ሚሊዮኖችን የሚያጠቃ በሽታ ነው።የሰዎች አማካኝ የመኖሪያ ዕድሜ እየጨመረ ሲመጣ  ደግሞ ይህ ቁጥር  ይጨምራል ተብሎ እንደሚጠበቅ መረጃዎች ያሳያሉ። ያም ሆኖ በሽታው  ከታወቀ ከጎርጎሪያኑ 1906 ዓ/ም ጀምሮ, እስካሁን ምንም አይነት ውጤታማ ሕክምና አልተገኘለትም። በቅርቡ ግን ይህንን ታሪክ የሚለውጥ እና ተስፋ ሰጭ  የተባለ አዲስ መድሃኒት ለመጀመሪያ ጊዜ መገኘቱን ተመራማሪዎች ገልፀዋል። 
ኢሳይ እና ባዮገን በተሰኙ  ሁለት የአሜሪካ የመድሃኒት አምራች ኩባንያዎች የተሰራውን እና «ለካነማብ»/lecanemab/ ወይም በገበያ ስሙ ለኬምቢ /Leqembi/ በመባል የሚጠራውን ይህንን መድሃኒት ትልቅ ስኬት ነው ይሉታል።የብሪታኒያ የዴሜንሽያ ተቋም  ተመራማሪ የሆኑት ባርት ዲ ስትሮፐር። 
«ይህ ትልቅ ስኬት ነው። እናም የመጀመሪያው ነው።ይህ በደረጃ 3 ክሊኒካዊ ሙከራ የተረጋገጠ ውጤት ያለው የመጀመሪያ ሙከራ ነው። እኔ እንደማስበው ሳይንሱ አስቸጋሪ ነው።ስለዚህ ይህ በር የሚከፍት ትልቅ ምዕራፍ ነው እላለሁ።»
በጀርመን የፍራዎንሆፈር የምርምር ተቋም  የአልዛይመር ተመራማሪ የሆኑት ስቴፋን ሺሊንግ እንደገለፁት «አሚሎይድ» የተባለው ፕሮቲን በአንጎል ውስጥ መከማቸት  ለአልዛይመር በሽታ ዋና ምክንያት ነው።«አሚሎይድ» በአንጎል ነርቭ ህዋሳት መካከል ባለው ክፍተት ውስጥ የሚከማች እና የአልዛይመር መለያ ምልክት የሆኑ ልዩ ግድግዳዎችን የሚፈጥር ፕሮቲን ነው።
በዚህ የተነሳ የአልዛይመር ተመራማሪዎች ላለፉት 50  ዓመታት በአንጎል ውስጥ «አሚሎይድ»ን የሚቀንሱ የሕክምና ዘዴዎችን ሲፈልጉ ቆይተዋል። 

US-Arzneimittelbehörde lässt Alzheimer-Medikament Aducanumab zu
ምስል David A. White/Biogen/AP/dpa/picture alliance

ለዚህ ይረዳ ዘንድም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለተለያዩ በሽታዎች ጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የበሽታ መከላከያ ማሻሻልን እንደ ሕክምና የሚጠቀመው «ኢሚኖቴራፒ» የተባለው የህክምና ዘዴ ለአዲሱ ግኝት ጥቅም ላይ ዉሏል ይላሉ።
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ የሥነ-አዕምሮ ትምህርት ክፍል ሀላፊ እና የሪኔሳንት/Renascent/ የአዕምሮ ጤና እና የሱስ ማገገሚያ ማዕከል መስራች  የሆኑት ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ።
በዚህ መንገድም ለመጀመሪያ ጊዜ የመርሳት በሽታ ስጋትን ለመቀነስ የሚረዳ ለካነማብ የተባለ መድሃኒት መገኘቱን ባለፈው ታህሳስ ተመራማሪዎቹ ገልፀዋል።

Professor Solomon Tefera
ፕሮፌሰር ሰለሞን ተፈራ የሥነ አዕምሮ ሰፔሻሊስት ምስል Privat

ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት አልዛይመር በዘር የሚተላለፍ በሽታ ሲሆን፤ «አሚሎይድ ቤታ» በመባል የሚታወቀው መደበኛ የአንጎል ፕሮቲን የሰዎች ዕድሜ እየገፉ ሲሄድ ብዙውን ጊዜ አሚኖፕሮቲን ወይም አሚሎይድ ወደሚባሉ ጎጅ ቅሬቶች ይቀየር እና በአንጎል ውስጥ ይከማቻሉ።ይህ የጎጅ ህዋሳት ክምችት የነርቭ ህዋሳትን በመግደል እና የአንጎልን ስራ በማደናቀፍ የማስታወስ እና የማገናዘብ ችሎታን ያሳጣል። ፕሮፌሰር ሰለሞን እንደሚሉት  የአዲሱ መድሃኒት ስራም  ሰውነት እነዚህን ንጣፎች እንዲያጸዳ መርዳት ነው። 

Alzheimer-Medikament
ምስል National Institute on Aging, NIH/AP/picture alliance

ይህ መድሃኒት በአንጎል ውስጥ ከሚገኙ አሚሎይድ ፕሮቲኖች ጋር በመጣበቅ በሽታ ተከላካይ ሕዋሳት ንጣፎችን እንዲያፈርሱ ያነሳሳል። በዚህ ሁኔታም የነርቭ ህዋሳትን በመግደል  የአንጎልን ስራ የሚያደናቅፉ ንጣፎችን በማፅዳት የማስታወስ ችግርን ይቀንሳል። በአሁኑ ጊዜ የአልዛይመር በሽታ ላለባቸው ሰዎች ምልክቶቹን ለመቆጣጠር የሚረዱ ሌሎች መድኃኒቶች እንደሚሰጡ የሚገልፁት ፕሮፌሰሩ ነገር ግን አንዳቸውም የበሽታውን ሂደት አይለውጡትም።ከዚህ አንፃር አዲሱ ህክምና ለየት ያለ ነው ይላሉ።
በዚህ የተነሳ  አዲሱ መድሀኒት ሌካነማብ፤ ቀላል የአልዛይመር በሽታ ላለባቸው እና በበሽታው ሳቢያ መለስተኛ የግንዛቤ ችግር ላጋጠማቸው ሰዎች ተስፋ አሳይቷል። ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት ለ18 ወራት በደረጃ 3 በተደረገ ሙከራ መድኃኒቱ የመጀመሪያ ደረጃ  የአልዛይመር በሽታ ላለባቸው ሰዎች ችግሩን በ27 በመቶ እንዲቀንስ አድርጓል።
በጎርጎሪያኑ መጋቢት 2019 ዓ/ም በተጀመረው በዚህ ምርምር 2000 የሚጠጉ  የአልዛይመር በሽታ ያለባቸውን በጎ ፈቃደኞች በሙከራው ተሳትፈዋል። 
የብሪታኒያው ተመራማሪ ደ ስትሮፐር እንዳሉት በለካነማብ በተደረገ ሕክምና በወራት ጊዜ ውስጥ ከአንጎል ውስጥ የተከማቸ የአሚሎይድ ፕሮቲንን በግልፅ እንደሚያስወግድ በሙሉ የሙከራ መረጃው ተረጋግጧል።በሌሎች የአልዛይመር በሽታ ምልክቶች ላይም ጠቃሚ ተጽእኖ እንዳለው አሳይቷል።

US-Arzneibehörde vergibt Zulassung für Alzheimer-Medikament
ምስል Eisai/AP/dpa/picture alliance

ያም ሆኖ መድሃኒቱ ውስኑነቶች እንዳሉት ፕሮፌሰር ሰለሞን ያስረዳሉ።
በሌላ በኩል ይህ መድሃኒት የሚሰራው በሽታው መጀመሪያ ደረጃ ላይ እያለ ሲወሰድ በመሆኑ፤ ብዙ ሰዎች የመጠቀም እድል ሊያጡ ይችላሉ የሚል ስጋትም አሳድሯል። ምክንያቱም ህክምናውን ለመውሰድ  በምርመራ አስቀድሞ በሽታውን ማረጋገጥ ይጠይቃል።ይህ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የኢኮኖሚ አቅማቸው ዝቅተኛ በሆኑ ሀገራት የምርመራ መሳሪያዎችን ማግኘት አስቸጋሪ ነው።መድሃኒቱም በዋጋ ደረጃም ውድ ነው።ከዚህ በተጨማሪ ስለበሽታው በቂ የግንዛቤ አለመኖር እና በሽታው ሲከሰት በጊዜ ወደ ጤና ተቋማት አለመምጣትም ሌላው ችግር ነው።
በአሜሪካ የመድሃኒት ቁጥጥር ባለሙያዎች ፍተሻ ሲደረግበት የቆየው ይህ መድሃኒት በጎርጎሪያኑ ጥር  6 ቀን  2023 ዓ/ም የአሜሪካ  የምግብ እና የመድኃኒት አስተዳደር (ኤፍዲኤ) በመጀመሪያ ደረጃ  ላሉ ታካሚዎች መድሃኒቱ እንዲሰጥ አጽድቋል። በአውሮፓም ግምገማ እንዲካሄድበት ኩባንያዎቹ ለአውሮፓ የመድሃኒት ቁጥጥር ማመልከቻ ማቀረባቸው ታውቋል።እናም  ሙሉ ፈቃድ ካገኜ  መድሃኒቱ በቅርቡ ጥቅም ላይ ይውላል ተብሎ ይጠበቃል።
በአልዛይመር ላይ የሚካሄዱ ሳይንሳዊ ምርምሮችን የሚደግፈው ብራይት ፎከስ ፋውንዴሽን መረጃ እንደሚያመለክተው  በዓለም ላይ ከ50 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በአልዛይመር ተጎጅ ሆነዋል።ይህ አሃዝም በ2050ም ወደ 139 ሚሊየን እንደሚደርስ ይገመታል። ከዚህ አኳያ ምንም እንኳ ውሱንንት እና የጎንዮሽ ጉዳቶች እንዳሉት ቢነገርም የአዲሱን መድሃኒት ለገበያ መቅረብም ሆነ በመድሃኒቱ  ዙሪያ የሚደረጉ ተጨማሪ ምርምሮችን ሚሊዮኖች በተስፋ የሚጠብቁት ነው። 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።
ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሰ