አብዲራሕማን ሞሐመድ አብዱላሒ የሶማሊላንድ ፕሬዝደንት ሆነው ዛሬ ሐሙስ ቃለ መሀላ ፈጸሙ። ኢሮ በሚል ቅጽል ስማቸው የሚታወቁት የተቃዋሚው ዋዳኒ ፓርቲ መሪ የራስ ገዟ ሶማሌላንድ 6ኛ ፕሬዝደንት ሆነዋል። የ69 ዓመቱ አብዲራሕማን ሞሐመድ አብዱላሒ ከዚህ ቀደም የሶማሌላንድ ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ የነበሩ ናቸው።
አብዲራሕማን ሞሐመድ አብዱላሒ ሥልጣኑን የጨበጡት ባለፈው ሕዳር በተካሔደ ምርጫ ካሸነፉ በኋላ ነው። በምርጫው ከተሰጡ ድምጾች ሞሐመድ አብዱላሒ 64% በማግኘት አሸንፈዋል። ዛሬ ሥልጣናቸውን ያስረከቡት ሙሴ ቢሒ አብዲ በአንጻሩ ያገኙት ድምጽ 35% ነበር።
ዛሬ በሶማሌላንድ ዋና ከተማ በተካሔደው የሥልጣን ርክክብ ሥነ-ሥርዓት የኢትዮጵያ የቀድሞ ርዕሠ-ብሔር ሙላቱ ተሾመ እና የሶማሊ ክልል ፕሬዝዳት ሙስጠፋ ሙሀመድ መገኘታቸውን ሰለሞን ሙጬ ከሐርጌሳ ዘግቧል።
አዲሱ ፕሬዝደንት ሥልጣን የተረከቡት ሶማሌላንድ ዕውቅና ለማግኘት የቀድሞው ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር የተፈራረሙት ሥምምነት ጥያቄ ውስጥ በወደቀበት ወቅት ነው። ኢሮ በምረጡኝ ዘመቻው ወቅት በአፍሪካ ቀንድ ቀጠና ውጥረት የፈጠረውን የመግባቢያ ሥምምነት ፓርቲያቸው እንደሚገመግም ገልጸው ነበር።
ከዓመት በፊት የተፈረመው “የአጋርነት እና የትብብር የመግባቢያ ሥምምነት” ኢትዮጵያ ለሶማሌላንድ እውቅና እንደምትሰጥ የቀድሞው ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሒ አብዲ ተናግረው ነበር። በምላሹ ኢትዮጵያ በሶማሌላንድ ጠረፍ ለወታደራዊ የጦር ሠፈር የሚሆን 20 ኪሎ ሜትር የሚሰፋ የባሕር ዳርቻ በ50 ዓመት ኪራይ እንደምታገኝ ተገልጾ ነበር።
በኢትዮጵያ እና በሶማሊያ መካከል ኃይለኛ መቃቃር የፈጠረው ሥምምነት እስካሁን ተግባራዊ አልሆነም። በቱርክ አሸማጋይነት ልዩነቶቻቸውን ለመፍታት ውይይት ሲያደርጉ የቆዩት ኢትዮጵያ እና ሶማሊያ በመጪው የካቲት ቴክኒካዊ ውይይት ድርድር ለማድረግ መስማማታቸውን አስታውቀዋል።