1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

አደጋ የተጋረጠበት የባቢሌ ዝኆኖች መጠለያ መካነ-አራዊት

ማክሰኞ፣ ኅዳር 13 2015

ከተቋቋመ ከዐምሳ ዓመታት በላይ እድሜን ያስቆጠረው የባቢሌ ዝኆኖች መጠለያ መካነ-አራዊት ኅልውናን እየፈተነ የሚገኘው ሕገወጥ የመሬት ወረራ መፍትሄ አለማግኘቱ ተገለጠ። መካነ-አራዊት ማለትም ፓርኩ የሚገኝባቸው የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ለችግሩ ተጨባጭ ርምጃ አለመውሰዳቸው በመካነ አራዊቱ የሚገኙ ዝኆኖችን ኑሮ አስቸጋሪ ማድረጉንም ተናግረዋል።

https://p.dw.com/p/4Ju8w
Babile Elephant sanctuary Park
ምስል Mesay Teklu/DW

ዘንድሮ 5 ሰዎች በዝኆኖች 2 ዝኆኖች በሰዎች ተገድለዋል

ከተቋቋመ ከዐምሳ ዓመታት በላይ እድሜን ያስቆጠረው የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ መካነ-አራዊት ኅልውናን እየፈተነ የሚገኘው ሕገወጥ የመሬት ወረራ መፍትሄ አለማግኘቱ ተገለጠ። መካነ-አራዊት ማለትም ፓርኩ የሚገኝባቸው የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልሎች ለችግሩ ተጨባጭ ርምጃ አለመውሰዳቸው በመካነ አራዊቱ የሚገኙ ዝኆኖችን ኑሮ አስቸጋሪ ማድረጉንም ተናግረዋል። በአካባቢው እየተስፋፋ ከመጣው እርሻ ጋር በተያያዘ ዘንድሮ ብቻ አምስት ሰዎች በዝኆች ሕይወታቸውን ሲያጡ ሁለት ዝኆኖች በሰዎች መገደላቸው ተገልጿል።

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ፓርክ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አደም መሀመድ ለዶይቼ ቬሌ (DW)እንደተናገሩት ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በፓርኩ እየተስፋፋ በመጣው ሕገወጥ ሰፈራ የፓርኩ ኅልውና አደጋ ውስጥ ገብቷል። ፓርኩ በሚገኝባቸው የኦሮሚያ እና ሶማሌ ክልል "ታች ያለው መዋቅር"  ባሏቸው አካላት ኅብረተሰቡ መሬቱን በወረራ እንዲይዝ የመግፋት ድርጊት መኖሩንም ጠቅሰዋል።

Babile Elephant sanctuary Park
ዝኆኖች በባቢሌ መካነ-አራዊት ጫካ ውስጥምስል Mesay Teklu/DW

በፓርኩ የመሬት ወረራ መስፋፋቱን ተከትሎ "ራስምታት" ሆኗል ባሉት "የሰው እና የዝሆን ግጭት" በሰው እና በዝሆኑ ላይ ጉዳት መድረሱን ኃላፊው አስረድተዋል። ፓርኩ ባሉበት መሰል ችግሮች ሳቢያ ዝሆኖች ተረጋግተው መቀመጥ እንዳልቻሉ የሚናገሩት አቶ አደም ይህም በቱሪስት ፍሰቱ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩን ጠቁመዋል።

የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ በሰዎች ተወሯል

ላለፉት ሃያ ሦስት አመታት በፓርኩ የስካውት ስራ ላይ ተሰማርተው ጥበቃ እና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን ሲሰሩ መቆየያቸውን የሚናገሩት አቶ አሊ ዶል የዝሆኖችን ኅልውና አሳሳቢነት በማንሳት መፍትሄን እንደሚናፍቁ ተናግረዋል። ችግሩን በተመለከተ በርካታ ውይይቶች መካሄዳቸውን ያነሱት ኃላፊው ወደ ተግባር የተሸጋገረ ስራ አለመኖሩን በማንሳት "ከንግግር ያለፈ ተግባር"  ያስፈልጋል ብለዋል።

በቅርቡ የሀረማያ ዩኒቨርሲቲ የፓርኩን ችግሮች ለመፍታት የሚያስችሉ ስራዎች ለመስራት እንቅስቃሴ መጀመሩን ያነሱት የባቢሌ የዝሆኖች መጠለያ ፓርክ ኃላፊ አቶ አደም የፌደራል እና ፓርኩ የሚገኝባቸው ሁለቱ ክልል መሪዎች እገዛ ከታከለበት ችግሩ መፍትሄ ያገኛል የሚል ተስፋ ማሳደሩን ተናግረዋል።

Babile Elephant sanctuary Park
የባቢሌ መካነ-አራዊት ጫካ ውስጥ ዝኆኖች ከርቀት ይታያሉምስል Mesay Teklu/DW

የባቢሌ መካነ አራዊት አጠቃላይ ሁኔታ

የባቢሌ ዝሆኖች መጠለያ ፓርክ ከሃምሳ አመታት በፊት በቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ የተመሰረተ ሲሆን 6982 ኪሎ ሜትር ስኩዌር የቆዳ ስፋት ያለውና በኦርሚያ እና በሶማሌ ክልል መካከል የሚገኝ ነው።

በመጠለያው እስካሁን በተደረጉ ጥናቶች ዝሆኖችን ጨምሮ ከ31 በላይ የጡት አጥቢ ዝርያዎች ፣ ከ225 በላይ የተለያዩ አህዋፋት ዝርያዎች እና ከሶስት መቶ ሃያ በላይ የተለያዩ የእፅዋት ዝርያዎች በፓርኩ ተመዝግበው እንደሚገኙ ከፓርኩ ፅ/ቤት ያገኘነው መረጃ  ያመለክታል።

መሳይ ተክሉ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ